Sunday, December 16, 2012

ልዋጭ፣ ልዋጭ፣ልዋጭ! ልዋጭ፣ልዋጭ፣ልዋጭ!





ዕለተ እሑድ፣ ታሕሳስ ሰባት ቀን 2005 ዓ.ም፤ገና ሶስት ሰዓት አልሆነም፡፡ ሰውዬው ልዋጭ፣ ልዋጭ፣ልዋጭ!ልዋጭ፣ ልዋጭ፣ልዋጭ!  እያለ እየደጋገመ ሲጮህ ይሰማኛል፤ ፍጥነቱ ይገርማል…ጀት አታውቁም? ጀት ነው!የምን መንቀራፈፍ? ሁሉ ነገራችን እደዚህ ፈጣን ቢሆን የድህነት ተምሳሌት አንሆንም ነበር፡፡

ድሮ ቆ…ራ…ሎ፣ቆ…ራ…ሎ፣ቆ…ራ…ሎ እያሉ ሲጣሩ ነበር የምሰማው፡፡ የጣር አይሉት ሌላ ብቻ የሆነ የታፈነ፣ሙትቻና ቃና የሌለው ድምፅ ነብር የሚያሰሙት፡፡ “ድምፅህ/ድምፅሽ ቅላፄ ለውም” ነው ያለው የኢትዮጵያ አይዶል ዳኛ? ልክ እንደዛው ድምፃቸው ”ቅላፄ“ ይጎድለው ነብር፡፡ለዛውም በጣም ድክሞ ወይም ዘገምተኛ ነገር፡፡ያው ሁለቱም የሚፈልጉት አሮጌውን እቃ በአዲስ ለመለወጥ ቢሆንም የድሮዎቹ አጠራር ግን እጅ እጅ ይላል፡፡ እጅ እጅ የማይል አሮጌ ነገር ምን አለ?ንጉሳዊው መንግስት እጅ እጅ ሲል “በትራስ ታፍኖ”ተገደለና በሊቀምንበሩ ወንበር ስር ተቀበረ…እንዳይነሳ እኮ ነው፡፡ጓድ ሊቀመንበርም አንድ በርትና እንድ ሰው እስኪቀር ድረስ ለመዋጋት ቢፎክሩም ፉከራው ሲደብራቸው ጊዜ ጥለውት ላሽ አሉና ሳያስቡት ወደ ድርሰት ዓለም ጭልጥ… ይሞታል እንዴ፡፡ ወጣትነት ራሱ ሲያረጅ ያረጃል፡፡ ወደድንም ጠላንም አሮጌ ነገር ያስጠላልና ሁሌም አዲስ ነገር ፍለጋ እንኳትናለን፡፡ በአሁኑ ጊዜ እንኳን ቀርፋፋ አጠራር ቀርፋፋ ዕድገትም አይበጅም፡፡ ለዛም ነው ሃገራችን ከድህነት አረንቋ ለመመንጨቅ በ“ደብል ድጅት“ ወይም በባለሁለት አሃዝ እየተወነጨፈች ያለችው፡፡ ስለዚህ ቆ…ራ…ሎ፣ቆ…ራ…ሎ፣ቆ…ራ…ሎ እያሉ የጣር ድምፅ ከማሰማት ይልቅ ልዋጭ፣ ልዋጭ፣ልዋጭ! ማለት ይሻላል፡፡ ምን ይሻላል ብቻ? ጀት የሆነ አጠራር ነው እንጂ፡፡ ይህ ነው ለውጥ ማለት፡፡ በእርግጥ“አዲስ ንጉስ እንጂ ለውጥ መቸ መጣ“ እያሉ ለሚዘፍኑ ሰዎች ለጊዜው ላይዋጥላቸው ይችላል፡፡ነገር ግን ባይዋጥላቸውም ለውጥ የማይለውጠው ነገር ስለማይኖር ሳይወዱ በግዳቸው ይውጧታል፡፡ካለሆነም ለውጡ ይለውጣቸዋል፡፡ ነብሳቸውን ይማረውና ንጉሱ ከእግዚሔር የተላኩ ፍፁም መሪ እንደነበሩ በግብዝነት ይለፍፉ ነበር… ››ንጉስ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ” እያሉ፡፡ ለውጥ ግን የማይ ለውጠው ነገር የለም፡፡ ህዝብ ባይከሳቸውም መንጌ አስሯቿል፤ በመጨረሻም የሆነው ሁኗል፡ሰማዩም ቢሆን በአየር ብክለት እየታረሰ ይገኛል፡፡ 


‹‹ወይ ጊዜ፣ ጊዜ መስታወት ስንቱን አየነበት›› አለች ዘፋኟ፡፡አዎ፣ ጊዜ ከመስታወትም በላይ ነው፤አይዝግም፣አይሰበርም፣አይደበዝዝም፡፡ ለባለ ጊዜው ብዙ ነገር ያሳያል፡፡አንዱዓለም ኪዳኔ የተባለ ገጣሚ ደግሞ ስለጊዜ የሚከተለውን ስንኝ ቋጥሯል፡፡

‹‹አንዱን እየጣለ ሌላውን ሊያነሳ
የመጣውን ሊያነግስ ነባሩን ሊያስረሳ
ጊዜ ፈጣን ባቡር ሄደ እየከነፈ
በየፌርማታው ላይ ሰው እያራገፈ፡፡›› 

ጊዜ ሃይለኛ ነው፡፡ አሮጌ እቃ ብቻ አይደለም በየፌርማታው ላይ የሚያራግፈው አሮጌ ሰውም ጭምር እንጂ፡፡ ስንት ጉረኞችን እያነሳ ይጥላል እባካቹህ? አፄ ንጉሰ ነገስት(ኮተት ላለማብዛት ሙሉ ስማቸውን እንሆ፤ ግን አደራ በቅንፉ ውስጥ እንዳንቀር፡ ሞአ አንበሳ ዘ እምነገደ ይሁዳ፣ ግርማዊ ቀደማዊ አፄ  ኃይለ ስላሴ፣ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ)፣ ጓድ ሊቀ መንበር፣ብፃይ መለስ፣ጋዳፊ፣ሳዳም፣ቢንላደን… አረ ስንቱን?ሌላው ቀርቶ ቆሼ ሰፈርም ታሪክ ሊሆን ነው… በሌላ ቆሼ ተቀይሯል፡፡ ምክንያቱም የማይለወጥ ነገር ካለ ራሱ “ለውጥ“ ብቻ ነው ተብለዋላ፡፡እናማ ሁሉም ነገር መለወጥ አለበት፡፡ ድህነቱ፣ኋላ ቀርነቱ፣ሙስናው፣ አምባገነኑ(በተለይ አሜሪካ!)፣መሃይምነቱ፣ስደቱ፣ ጥላቻው፣የትራንስፖርት እጥረት፣ የመብራት፣የውሃና የስልክ መቆራረጡ…ሁሉም አርጅቷል፤ እጅ እጅ ብሏል፡፡ ስለዚህ አሮጌውን(እጅ እጅ ያለውን)በሰላም፣በፍቅር በእድገትና በጋራ ብልፅግና ለመለወጥ አብረን… ልዋጭ፣ልዋጭ፣ልዋጭ!ልዋጭ፣ልዋጭ፣ልዋጭ!ልዋጭ፣ልዋጭ፣ልዋጭ!እነበል፤የማይለወጥ ነገር የለምና፡፡

No comments:

Post a Comment