አሁን ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ተኩል ሁነዋል፡፡ዛሬም ልክ እንደ ትናንቱ መብራት የለም፡፡ ዕድሜ ለላፕቶፔ
በስዋ መብራት እየታገዝኩ የሀው እየጻፍኩኝ ነው፡፡ አዲስ አባባ መኖር ከጀመርኩ አምስት ዓመታት አስቆጥሬያለሁ፡፡ እንደውም
ሶስት ወራትም እንደዘበት አፈትልከዋል፡፡ በነዚህ አምስት ዓመታት አምስት ዋና ዋና ችግሮችን አስተውያለሁ፤ እስካሁንም መፍተሔ ሳይበጅላቸው
ነዋሪውን ህዝብ እየተፈታተኑት ይገኛሉ፡፡
1.የቤት ክራይ ዋጋ ከልክ በላይ መናር
አንደኛውና
በጣም አስቸጋሪው ነገር የቤት ክራይ ከልክ በላይ መወደድ ነው፡፡ የቤት ክራይ ዋጋ በየዓመቱ እየናረ ይገኛል፡፡ በቃ ዓመት በመጣ
ቁጥር የቤት ክራይና የዕድሜ ጭማሪ አለ፡፡ የምሰራበት መስራያቤትና ያከራዪኝ ሰዎች አንድ መስለው ይታዪኛል፡፡ መስራያቤቱ የደሞዝ
ጭማሪ ካደረገ አከራዮቼም ተመጣጣኝ የሆነ የቤት ክራይ ይጨምሩብኛል፡፡ልክ ተመካክረው የወሰኑት ይመስላ፡፡መንግስት እያሳየ የሚነጥቀኝ
መስሎ ይሰማኛል፡፡ ፡፡ በየወሩ ከደሞዜ ሰላሳ አምስት ፐርሰንት ግብር
የቆርጣል፤ ለያንዳዱን የምገዛው እቃ ወይም ግልጋሎት ደግሞ ከትክክለኛ
ዋጋው በተጨማሪ አስራምስት ፐርሰንት የስከፍለኛል፡፡ ከቀሪዋ ደሞዜ ሃምሳ ፐርሰንትዋን ለቤት ከራይ አስረክብና ይህች ወር ተሎ እንድታልፍልኝ
ለፈጣሪ እየጸይየኩኝ አሳልፋታለሁ፡፡የቤት ክራይ ችግር እንዲህ የሚፈታተነኝ በላጤነቴ ነው።እንዛ ልጆች ወልደው ለማስተማር የደረሱት
ወገኖችስ ምን ዓይነት ንሮ እየኖሩ ይሆን?እነዛ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ወገኖችስ እንዴት ይሆን የሚኖሩት? በጣም በጣም የሚያሳስበው
ድግሞ ለወደፊትም ተስፋ የለለው ነገር መሆኑን ሳስብ ነው። ይህን ተስፋ የለሽ ሂይወት ራስ ምታት፣ቁርጠት፣ፍልጠት፣ ቁርጥማት… እንዴ!መኖር
በሽታ ሁኗል፤ልክ እንደ ኤድስ ፈውስ የሌለው ፡፡መንግስት ግን ሁሌም እንደ ለፈፈ ነው፤ ስለየጋራ መኖርያ ቤቶችን ይደሰኩራል፣ ስለ40/60
ያለው ምኞት የናገራል ግን ምኞት በተግባር ካልተደገፈ ያው ምኞት ነው፡፡የህልም እንጀራ ነው፡፡ አዎ ጸሐዪ መንግስታችን በምኞት
ብቻ የህልም እንጀራ እየመገበን የገኛል፡፡
2.የትራንስፖርት ዕጥረት
የተራነስፖርትና
ተጉዋዥ አለመመጣጠን ሌላው ፈታኝ ችግር መሆኑን ይፋ ከሆነ ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡አዲስ አበባ ለንደኔ ዓይነቱ ከሰኞ እስከ ዓርብ
ጥዋትና ማታ ታክሲና አውቶብስ የሚጠቀሙ ሰዎች ሲበዛ ፈታኝ ሆናለች፡፡ታክሲ ለማግኘት ጥዋትና ማታ ብያንስ ለአስራ አምስት ደቂቃ
መሰለፍ የግድ ይላል፡፡ አረ እንደውም ታክሲ አስከባሪ በሌሉበት አከባቢስ ጉልበተኞች ከተሳፈሩ በሁዋላ ትርፍ ከተገኘ እንጂ መጋፋቱ
በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ከስንት ወረፋ በሁዋላ ቢሮ ስትደርስ የሚያጋጥምህ የአለቆች ግልምጫ አይጣል ነው፡፡ መንግስት ግን ለዚህ
ችግርም ትኩረት የሰጠው አይመስልም፡፡ከዘላቂው መፍትሔ ጎንለጎን የተለያዪ
ጊዜያዊ መፍተሔዎችን ከማበጀት ይልቅ ብያንስ ሁለት ዓመት ወይም ከዚያበላይ ሊወስድ ሚችል የቀላል ባቡር የመስመር ዝርጋታን መጠናቅቅ
እየጠበቀ ይገኛል፡፡ የህ ግን ችግሩን ያባብሰው እንደሆነ እንጂ ከስረመሰረቱ ሊቀርፈው አይችልም፡፡ ምክንያቱም ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ
የሚኖረው የተጠቃሚ ህዝብ ብዛት በጣም ይጨምራል እንጂ አይቀንስም።እንዲህ ከሆነ ታድያ ዕድሜ ልካችን እየተሰለፍን እንደንኖር ተፈርዶብናል
ማለት ነው፡፡እሺ የባቡር መስመር ዝርጋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ችግሩ ሙሉ ለሙሉ የሚፈታስ ቢሆን ህዝቡ እስከዛ ድረስ ምንያህል ቢታገስ
ነው እጁና እግሩን አጣጥፎ ሊጠብቅ የሚችለው?
3.
የውሃ ችግር
ከአንደኛ
ክፍል ጀምሮ ነብር ስለውሃ ጥቅም ብዙ ሲባል ትዝ የሚለኝ፡፡ውሃ ሂይወት ነው፣ምግብ ነው፣መድሃኒት ነው፣የንፅህና ማስጠበቅያ ነው፣
ሁሉም ነገር ነው… ተደጋግሞ ሲነገር መስማት የተለመደ ነው፡፡መሪዎቻችን ግን ይህን ነገር የረሱት ይመስላል፡፡ ለነሱ ውሃ ማለት
ሻወር መውሰድ እንጂ ገላ መታጠብና መጠጣት አይደለም፡፡በነሱ ባኞ ቤት ውሃ አይጠፋም፤ስለሆነም በገላቸው ላይ ያለው የሳሙና አረፋ
ሳይፀዳ ውሃ ጠፍቶባቸው አያውቅም።ዓይናቸው ውስጥ ሳሙና ገብቶ እንደ እሳት አይለበልባቸውም።ለነሱ ውሃ ማለት ስብሰባ ላይ ሲቀመጡ
በፕላስቲክ ታሽጎ ከፊትለፊታቸው የሚቀመጥ ጌጣ ጌጥ ብቻ ነው፡፡ እነሱ የተለያዪ ውድ የውጪ ሃገር መጠጦች እያቀያየሩ ስለሚጎነጩ
ውሃ ኖረም አለኖረም ደንታቸው አይደለም፡፡ውሃ የመጠጣት ልምድ ቢኖራቸውም እንኳ በፕላስቲክ ታሸገ ሃይላንድ፣ዬስ፣ኩል እነዚህ ባይኖሩም
በዋሪት የተጣራ ንፁህ ውሃ አያጡም።የሃያ ሊትር የሚዝ ጀሪካን ተሸክመው ከሰፈር ሰፈር አይንከራተቱም።ውሃ ችግር ይዋል ይደር የማይባል
አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን አይገባቸውም፡፡ የአዲስ አበባ የዓመታት የውሃ እጥረት አለመፈታቱ የዚህ ባህሪያቸው ማረጋገጫ ነው፡፡በተጠየቁ
ቁጥር የሚስጥዋት ምላሻ አንድና አንድ ብቻ ናት…“የውሃ ችግር ከስረ መሰረቱ ለመቅረፍ ፕሮጀክት ነድፈን እየተንቀሳቀስን ነው“…አራት
ነጥብ፡፡ፕሮጀክቱ ግን አንድም እየተሰራ አይደለም አልያም እየገነቡ እያፈረሱት ሳይሆን አይቀርም መቸም አያልቅም፡፡ ጅብ በልቶት
ከሆነም ሲጮህ አይሰማም፡፡
4.የመብራት መቆራረጥ
አገራችን
የኤሌትሪክ ሀይል ማመጫ ፕሮጀክቶችን አስመርቃለች እያስመቀችም ነው፡፡ የህዳሴው ግድብ ጨምሮ በግንባታ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችም አሉ፡፡አዲስ
አበባ ግን አሁንም በመብራት እጦት ገሃንም መምስልዋ አልቀረም፡፡ ፕሮጀክቶቻችን አዲስ አበባን በጨለማ ላይ ትተው ጁብትን በቅናሽ
ዋጋ እያበሩ ይገኛሉ፡፡ ከንያና ሱዳንም በጉጉት እየጠበቁ ነው፡፡ተርፎን ወደጎረቤት ሃገሮች ብንልክ መልካም ነበር… ሃገራችን የውጭ
ምንዛሪ ማግኘትዋ እሰየው ነው፡፡ማንኛውም ዜጋ የሚኮራበት መሆኑን አያጠራጥርም፡፡ ነገር ግን እኛ በጨለማ ተውጠን መሆን የለበትም፡፡እንዴ!
መብራት የሌለበት ከተማኮ ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ አውሬው ይቀርና ሕግ ስከባሪውም አውሬ ሁኖ ቢበላን ማንም
ሃይ ሊለው አይችልም፡፡ታድያ እኛ ጅብ ከበላን በሁዋላ የሚመጣው የውጭ ምንዛሪ ምን ያድርግልናል?ምን ያህልስ አዋጪ ነው? መብራት
በጠፋ ቁጥር ለጀነሬተሮች የሚወጣው ነዳጅ እኮ በዶላር ተገዝቶ ነው ከውጭ የምናስገባው።ወይስ ያሉን ፋብሪካዎች ጥቂት ስለሆኑና ህዝቡም
በጨለማ መኖር ለምዶታል ብለው ስላሰቡ ነው?ይህማ መሆን የለበትም፤በማንኛውም መልኩ አሳማኝ አይደለም፡፡ ሌላ ምክንያት መኖር አለበት…
የሙሰኞች ኪስ እንዳይ ጎድል!
5.የንሮ ውድነት
የንሮ
ውድነት እንደ ፈለገው እየፈነጨብን ይገኛል፡፡ሁሌም ወደላይ የወነጨፋል ላይ ደርሶ ግን መሬት ላይ ሲፈጠፈጥ አይታይም፡፡የመሬት የስህበት
ሃይል ለንሮ ውድነት ምኑም አይደለም፡፡ በቃ እንደምትሃተኛ “አከሮባቲስት” ሰማይ ላይ የከረባበታል።የኛ ገላ እንደ መዝለያ ስፕሪንግ
እየተጠቀመ፡፡ለገዢዎቻችን ግን ይህ ነገር መዝናኛ እንጂ ችግር አይደለም።አዎ ለነሱ የዕድገት ምልክት ነው፡፡ ለዛም ይመስላል ዘላቂ
መፍተሔ ስያፈላልጉለት የማይታየው፡፡ ብቻ ግን አንድ ቁጥር አለች፤ አለቆቻችን ሁሌም እይደጋገሙ ያነሱዋታል… አስራ አንድ ቁጥር፡፡
በየዓመቱ በአስራ አንድ ፐርሰንት እናድጋለን… እሰየው እንደግ! ግን፣ ነገር ግን በንሮ ውድነት ከማለቃችን በፊት እድገቱ ሊደርስልን
ይገባል፡፡ከተቻለም አብሮን ይደግ… አብሮ ማደግ ለማንም አይጎዳም፡፡ ወይስ እንደ አዲስ አበባ ህንፃዎች አንጋጠን እስክንመለከተው
ድረስ ነው?
እነዚህ
ከላይ የተዘረዘሩት ችግሮች ትንፋሽ የማጣት ያህል አስጨናቂ ናቸው።ለመሪዎቻችን ግን ምንም ማለት አይደሉም።ለምን? ምክንያቱም እነሱ
ቤት ተከራይተው አያውቁም።ብዙ ምርጥ ቬላ ቤቶች አሉ፤ባንዱ ላይ ተንፈላስሰው ይኖራሉ።በነዚህ ቬላ ቤቶች የውሃና መብራት አገልግሎት
ሃያ አራት ሰዓት ነው።የትራነስፖርት ችግረስ እንዴት ይወቁት?በዓለም አሉ የሚባሉ እጅግ ዘመናዊ የመኪና ሞዴሎች ከፈለጉ ከነአሽከርካሪያቸው
ጋር ይሰጣቸዋል።የንሮ ውድነትም ምንም ማለት አይደለም።ምስኪን ወገናችን በሚከፍለው ግብር ተንደላቀው የኖሩበታል፤ውጪ ሃገር ይማራሉ
ይዝናናሉ…ከልጆቻቸው ጋር።
ግን
ይህን ሁሉ ችግርና ግፍ ካለ የአዲስ አበባ ጎደናዎች ለምን እንደ ሌሎቹ የዓለም ጎደናዎች(ጣሕሪሪ ስኩዌረ፣ዎል ስትሪት፣ባአጠቃላይ
የዓረቦችና ምዕራባውያን ጎደናዎች)በስላማዊ ሰልፈኞች ሲጨናነቁ ለምን አይታይም?የፅንፈኛ ድያስፖራ መፈክሮችስ ለምን እንደጉም በነው ቀሩ?
ምክንያቱም
የኢትዮጵያ ህዝብ ብዙ ችግሮችን አይተዋል አሳልፈዋል… ሰው ሰራሽና ተፈጥራዊ ችግሮች፡፡ድርቅና ድህነት እንደ መገለጫው እስኪ ቆጠሩ
ድረስ ተደጋግመውበታል፡፡ እናቶች ለመሃንነት እስኪ ሳሉ ድረስ በጦርነት ምክንያት ብዙ ወገኖቹን አጥተዋል፡፡ዕብሪተኛ የውጪ ወራሪዎችን
ለመመከትና ዳር ድንበሩን ለማስከበር ብዙ ደምተዋል፣በስልጣን ሽኩቻም እርሰ በርሱ ሲተራረድ ንሮዋል፡፡ብዙ ግፍና ጭቆናም ደርሶበታል፤
በደምብ አርጎም ያውቃል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ንጉሳዊውን ምንግስት ለመገርሰስ ሰላማዊ ሰልፎችን አካሂደዋል፡፡ ግን ምን አገኝ?ምንስ አተረፈ? ህዝቡ ሲተርት “በዕንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ” ወይም ”ከድጥ ወደማጥ”እንደሚለው ሰላማዊው ትግሉ በደርጋውያን አምባገነኖች ተጠልፎ
እሳት ሁኖ ፈጀው፣ የነበረውን ሁሉ አሳጣው፡፡ የ97ቱ የቅንጅቶች ”ሰላማዊ ሰልፍም” ሌላ ሙሉ በሙሉ ባልዳነው በሰላው ላይ ስንጥር
ጨመረበት እንጂ ምንም አልፈየደለትም፡፡ ስለዚህም ነው ”ከማየውቁት መልአክ …” በማለት ቤቱን ዘግቶ ዝም ያለው፡፡ ዳሩ ዝም ያለ
ይምሰል እንጂ ውስጡ ሸፍተዋል… አገር ጥሎ ኮብልለዋል፡፡
ብዙ
ወገኖችም አገራቸውን ጥለው ተሰደዋል፤ብዙዎች ደግሞ ያሰቡበት ቦታ ሳይደርሱ ያለቀባሪ በረሃ ላይ ወድቀው ቀርተዋል፡፡ስደት አሁንም
ቀጥለዋል…የቀናው በቦሌ ከላለለት ደግሞ በኮንተይነር ታሽጎ በሁሉም ያገራችን አቅጣጫዎች አገሩን ጥሎ እየሸሸ ይገኛል፡፡ የህ ራሱን
ቻለ ሰላማዊ ሰልፍ ነው ማለት እንችላለን፡፡
ለዚህም
ነው ከላይ የተዘረዘሩ አንኩዋር አንኩዋር ችግሮችን በትዕግስት እያሳለፋችው የሚገኘው፡፡ አዎ ለሰላም ሲባል ነው ረሃብና ቆፈን፣የውሃ፣
የመብራትና የትራንሰፖርት እጥረቶች ሲፈራረቁበት ጥርሱን ነክሶ ”እምምምም“ እያለ ነገን በተስፋ የሚጠባበቀው፡፡ያረገዘው ችጋር አልወለድም
ብሎት ”እምምምም!“ እያለ ይገኛል… ሌት ተቀን ያምጣል፡፡ግን በምጥ ንሮ እስከ መቼ?
የታገሰውን
ያህል፣የናፈቀውንና የተመኘውን ያህል ኩፉውን ሁሉ ያርቅለት፤ሰላም፣ፈቅር፣እድገትና ብልፅግና ይዝነብበት… ለታጋሹ ህዝባችን፣ በመላው
ዓለም ለተዘራው ወገናችን፡፡
ሰላም!
No comments:
Post a Comment