ዋዛና ቁም ነገር
1. አገርም ጐረቤትም እየረዳኝ
በአንድ አካባቢ አንድ በስተእርጅና ዘመናቸው ቆንጆ ወጣት ሴት ያገቡ አዛውንት እየሸመገሉ ሔዱና ዕድሜያቸው 105 ሞላ፡፡ በአንጻሩ ሚስት እየቆነጀች፣ እያማረባት መጣ፤ አዛውንቱ ዕድሜያቸው እየገፋ ቢመጣም ሚስት ግን ልጅ መውለድዋን አላቆመችም፡፡
የአካባቢው ሰው ግን ሚስት ጐረቤትዋ ከሆነ አንድ ጐረምሳ ጋር ሥውር ወዳጅነት መፍጠርዋን ከመጠርጠር አልፎ ሁኔታውን በግልጽ ያውቅ ነበር፡፡ አንድ ቀን ከአካባቢው ነዋሪዎች አንዱ አዛውንቱ ዘንድ ሔዶ፡-
‹‹አባት ለመሆኑ ይህን ያህል ዕድሜ ከሆነዎት በኋላ እንዴት ነው የሚወልዱት?›› አላቸው፤ ሽማግሌው የሰውየው ጥያቄ ከምን ጋር የተያያዘ እንደሆነ ገብቷቸው ኖሮ፡-
‹‹መቼም አገርም ጐረቤትም እየረዳኝ›› ብለው መለሱለት አሉ፡፡
- ካሕሣይ ገ/እግዚአብሔር፣ ‹ኅብረ-ብዕር›› (1998)
2. እሱማ እኔም ነበረኝ
አንድ ደጃዝማችና አንድ ቀኛዝማች ከሌሎች ሹማምንቶች ጋር በመሆን ድግስ ላይ ይበላሉ፣ ይጠጣሉ፡፡ በመካከሉ ቀኛዝማቹ ውኃ ሽንታቸውን ለመክፈል ፈልገው አሽከራቸውን መክፈያ እንዲያመጣላቸው ያዙታል፡፡አሽከሩም በታዘዘው መሠረት መክፈያውን ይዞ ከተፍ አለ፡፡ ይሁንና ቀኛዝማች ሽንተቸውን ለመሽናት ቢፈልጉም ፈሳቸው አብሮ መጣሁ መጣሁ እያለ አላሸና አላቸው፡፡ ከዚያ አምልጦኝ ሰው ፊት ከምዋረድ ብቆይ ይሻላል በሚል፡-
‹‹በል አንሳ›› ብለው መክፈያውን ወደዛ ገፋ ከማድረጋቸው አጠገባቸው የነበሩ ጓደኛቸው (ደጃዝማቹ)፡-
‹‹አንተ እምቢ ካልህ እኔ ልሞክር›› አሉና ሽንታቸውን መሽናተ ሲጀምሩ አምልጦአቸው አንድ ሁለቴ ቷ…ቷ አደረጉ፡፡ በዚህን ጊዜ ከሚያመልጠኝ ይቅርብኝ ብለው የተቀመጡት ቀኛዘማች፡-
‹‹አዬ ደጃዝማች ሌላ ታመጣለህ ብዬ ነው እንጂ እሱማ እኔም ነበረኝ›› አሉ ይባላል፡፡
- ካሕሣይ ገ/እግዚአብሔር፣ ‹‹ኅብረ-ብዕር›› (1998)
source: http://www.ethiopianreporter.com/index.php/other-sections/2012-12-14-13-20-52/zinnik/item/502-በመቀሌ-ዩኒቨርሲቲ-ዋና-ካምፓስ-ተማሪዎች-የኢትዮጵያንና-የዛምቢያን-እግር-ኳስ-ጨዋታ-ሲመለከቱ
No comments:
Post a Comment