Monday, February 18, 2013

የኢፈዲሪ መከላከያ ሰራዊ ቀን አከባበር እና ሃገራዊ ፋይዳው













ባለፈው ሳምንት(የካቲት አንድ እስከ ሰባት 2005 ዓ.ም) የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ቀን በመስቀል አደባባይና በእግዚቢሽን ማዕከል ‹‹ህገ መንግስታዊ ታማኝነታችንና ህዝባዊ ባህሪያችን እንደተጠበቀ ይቀጥላል›› በሚል መፈክር ሲከበር በዓለም የሰው ሂይወትና ንብረት በማውደም የሚታወቁት የተለያዩ ዓይነት የጦር መሳርያዎች ለህዝእይታ ክፍት ሁነው ሲጎበኙ ከርሟል፡፡ ብዙ ወገኖች ከመሳርያዎቹ ጋር ተቃቀፈውና በታንኮቹላይ ወጥተው ፎቶ ሲነሱ ነበር ፡፡እኔ ግን አላደረግኩትም፤ ከነዚያ ነፍሰ በላ መሳርያዎች ጋር ፎቶ መነሳት ይቀርና ድጋሚ ባጠገባቸውን ለማለፍም አልሻም፡፡ 
 




የሆነ ሁኖ ግን የተለያዩ አውዳሚ የጦር መሳርያዎች አፈሙዛቸውን ወደ ቤተ መንግስቱ አቅጣጫ ወድረው ሰንብቷል፡፡የፍልውሃና የአራት ኪሎ መሪዎቻችን ግን የህን ያህል ደፋሮች ናቸው ማለት ነው?የድሮዎቹ የጦር መሳርያዎች አብዛኛወቹ ራሽያ ሰራሽ ሲሆኑ በደቡብ ኮርያና በቻይና የተፈበረኩም የገኙበታል፡፡አሁን ግን እነዚያ መሳርያዎች በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ስር የሚተዳደረው ጋፋት አርማመንት እንዲስቱሪ እየሰተሩ ይገኛሉ፡፡በመከላከያ የምህንድስና ኮሌጅም ከመለዋወጫ እስከ ቀላልና ከባድ መሳርያዎች በመሰራት ላይ ናቸው፡፡አረ እንደውም እውነት ያድርገውና ሰው አልባ የውግያ በራሪ መሳርያዎችም(ደሮን) በነዚህ ተቋማት መሰራታቸውን ተነግሮናል፡፡



የሃገራችን የመከላከያ ሰራዊት በእውቀትና በዘመናዊ ትጥቅ ወደፊት እየገሰገሰ መሆኑን ብዙ ወገኖችን እስደምሟል፤ እስደስቷልም፡፡ለወደፊትም መከላከያችን የሃገራችን ዕድገትና ትራነስፎርሞሽን እንዲፋጠን ድርሻውን እንደሚወጣ ያላቸው እምነት ሲገልፁ ተሰምቷል፡፡አገራችን ኢትዮጵያ መቸም ቢሆን በማያነቀላፉ ታሪካዊ ጠላቶቻችን የተከበበች መሆኗን አያካድም፡፡እናም ዘርፈ ብዙ በሆነ ዕድገት ወደ ፊት መራመድ ብቻ ሳይሆን ከተቻለ መብረር ብትችልም ደስታውን አንችለውም፡፡

 
ይህ ነገር ግን በተግባር እንጂ በወሬ መሆን የለበትም፡፡እንድያውም ምንም ዓይነት ትዓምር ብንሰራም ይህን ያህል ማራገቡ አስፈላጊ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡በአሁኑ ጊዜ የመከላከያ ሰራዊታችን በጅማሮ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ጅማሮውም ‹‹ የሚያበረታታ ነው›› ማለት እንችላለን( ኢህዴግ አባባል ተውሰን)፡፡ ነገር ግን እንኳንስ በቴክኖሉጂ ‹ሀ…ሁ› ደረጃ ላይ ሁነን ይቅርና በጠፈር ምርምርና በኒኩለር ቴክኖለጂ በከፍተኛው እርከን ላይ ብንደርስም ለማንም መናገር ያለብን አይመስለኝም፡፡ምን ያስፈልጋል? ጊዜው ሲደርስ በንፈፅመው ተግባር እናስመሰክር የለም እንዴ፡፡

እስራኤላውያን በዓለም አለ የሚባል የውግያ ቴክኖሎጂ ባለቤት መሆናቸውን ይታወቃል፡፡ነገር ግን አንድም ቀን እንኳን ሰላላቸው የጦር መሳርያ ዓይነትና የሰራዊታቸው ብቃት ትንፊሽ በለው አያውቁም፡፡እንሱ ማንነታቸውን የሚያስመሰክሩት በዓውደ ውግያ ብቻ ነው፡፡ባለፈው ጊዜ(ጥቅምት 2005 ዓ.ም) ከሐማስ ታጣቂዎች ጋር ባደረጉት ጦርነት እስራኤላውያን ዓለምን ጉድ ያሰኘ የፀረ ሚሳይል ሚሳይል ባለቤት መሆናቸውን በተግባር አስመስከሯል፡፡‹‹የሚያደርገውን የሚያውቅ ልጅ ለእናቱ አይናገርም›› ማለት ይህ ነው፡፡

እናም የባለፈው ሳምንቱ የመከላከያ ሰራዊታችን በል ሳይሉት ራስን ለጠላት የማጋለጥ ዘመቻ አልተዋጠልኝም፡፡ልክ እንደ እስራኤል የመከላከያ ሰራዊት በተግባር ብቻ ተፈትኖ የስመሰከረ እንዲሆን ለሰራዊታችን እምመኝለት፡፡አሁን ግን የሆነ ጉራ ብጤ የተቀላቀለበት የፈሪዎች አጉል ፉከራ መስሎ ተሰምቶኛል፡፡ ልማታዊነትም ሆነ ወታደራዊ ብቃት በዓውደ ውግያ እንጂ በዓውደ ራኢ ይለካል የሚል እምነት ይለኝም፡፡ጉራ እንድም የፍራቻ ምልክት ነው…ለውድቀት የሚዳርግ፡፡አልያም አጉል ትዕቢት ነው፡፡ፈረንጆች ‹‹Pride comes before a fall…ትዕቢት ውድቀትን ትቀድማለች›› የሚል አባባል አላቸው፡፡ስለሆነም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በአጉል ጉራ ወይም ትዕቢት ተወጥረን ጠላቶቻችንን እኛን ቀደመው እንዲገኙ እየረዳናቸው እንዳይሆን የሚል ሰጋት አድሮብኛል፡፡



ዓለማችን ብዙ ትዕቢተኛ አምባገነኖችን በየጊዜው አስተናግዳለች፡፡ከነዚህ ዓለማችን የፈራቻቸው ነፍሰ በላ ጭራቆች እነ ሂትለር፣ሳዳም ሁሴን፣ጋዳፊና መሶሎኒ ይገኙበታል፡፡የነዚህ ሰዎች ኢሰብኣዊ ግፍ፣ እብሪትና ባዶ ፉከራ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ አሟሟታቸውም እንዲሁ በጣም ይመሳሰላሉ፡፡

አዶልፍ ሂትለር በዓለማችን በጭካኔው ተወዳዳሪ እንደማይገኝለት ይነገራል፡፡ያየሚመካበት ጭራቅ ሰራዊቱ አርካሪውን ተሰባብሮ እንደ ጉም ሲበን ግን የጠላቶቹን ፊት ማይት ስላልደፈረና የእጁን እንዳያገኝ ሰለፈራ ራሱን አጠፋ፡፡በሰላም እጁን ቢሰጥ የሚጠብቀው ያውቅ ነበርና፡፡

ሳደም ሁሴንም እንዲሁ ርህራሄ አልባ ጭራቅ ነበር ይባላል፡፡ምዕራባውያን ሐያላን መጣን መጣን እያሉ ልያስፈራሩት ሲሞክሩ‹‹ኑ! ነገር ግን ኢራቅ ወስጥ ሰምጣችሁ ትቀራላችሁ››እያለ ሲፎክርበትና ሲመካበት የነበረው ጅምላ ጨራሽ መሳርያው ግን እንደ አይጥ ከጉድጓድ ወደ ጉድጓድ ከመሽሎክሎክ አልታደገውም፡፡እድውም ጉድጓድም ምስጢሩን ሊደብቅለት አልፈለገም መሰል ለነዚያ በህልሙና በውኑ እየመጡ የሚያስበረግጉት ምዕራባውያን ጠላቶቹን አሳልፎ ሰጠው፡፡ አሜሪካኖች ከተደበቀበት ጉድጓድ ቆፍረው በማውጣት ሱሙኒ በማታወጣ ገመድ አንጠልጥለው ሲገድሉት የተመለከተው የዓለም ህዝብ የሆሊውድ ፊልም የሚመለከት ነበር የመሰለው፡፡

በደናግላን አጃቢዎቹና ቄንጠኛ አለባበሱ የሚታወቀው የኮለኔል ጋዳፊ እብሪት ከእብሪትም በላይ እንደነበረ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ጋዳፊ የሊቢያ ፈጣሪ፣ባለቤትና ንጉስ መሆኑን ብቻ አልነበረም ራሱን የሚያስበው የአህጉረ አፍሪካ መሪ ጭምር እንደሆነም እንጂ፡፡ከነዳጅ ሽያጭ በሚያገኘው ገቢ ኪሱ ስለደለበ አስተሳሰቡም እንዲሁ እንደ ኪሱ በትዕቢት ተወጥሮ ያስቸግረው ነበር፡፡ የአሜሪካና አጋሮቿ ምት ግን መቋቋ አልቻለም፡፡እንደ የአዲስ አበባ ሌባ ቱቦ ውስጥ ተደብቆ ተገኘና ያለፍርድ በጥይት ተደብድቦ ከዚች ዓለም ተሰናበተ፡፡

በኒቶ ሙሶሎኒም እንዲሁ እንደ ሌሎቹ አምባገነኖች ሲሸሽ ተገኝቶ ከውሽማው ጋር በጥይት ተጨፍጭፎ ነበር የተገደለው፡፡

ወደሃገራችን ስንመለስም የአፄ ቴድሮስና የመንግስቱ ሃይለማርያም ጭካኔና ትዕቢት ከመጠን በላይ ጎልቶ ይታያል፡፡አፄ ቴድሮስ ቆራጥና ሃገራቸውን የዘመናዊ መሳርያ ባለቤት ለማድረግ ቁርጠኛ አቋም እንደነበራቸው ይተረካል፡፡ነገር ግን ከመጠን በላይ ጨካኝና ትዕቢተኛ(እንደውም ወደ ዕብደት የሚያደላ ራስን የመቆለል አባዜ) ጭምር ነበሩ፡፡ያ ባህሪያቸው ነበር ድያ ራሳቸውን ለማጥፋት ያደረሳቸው፡፡ግዛተቸውን ከቱርኮችና ሱዳኖች ለመታደግ ያስችላቸው ዘንደ የእንግሊዝ ንግስትን የጦር መሳርያ ሚሰሩላቸው በለሞያዎች እንዲልኩላቸው በደብዳቤ ተማፅነው መልስ ሊሰጧቸው ስላልቻሉ ተናደው በእጃቸው የነበሩ ሚሴናውያንን በማሰር አስገድደው መድፍ አሰሯቸው፡፡
ይህን የሰሙ እንግሊዞች የአፄ ቴወድሮስን የእትዕቢት እባጭ ለማስፈንዳት ታጥቀው ወደ መቅደላ ገሰገሱ፡፡አፄ ቴወድሮስ የርሳቸው እጅ በቀላሉ ሊጠመዝዝ የሚችል ሃይል ያለ አይመስላቸውም ነበርና መድፋቸውን ወድረው ጠበቋቸው፡፡ ከዛም መድፉ አንዴ ፈንድቶ አቆመ፤ ወታደሮቻቸው(አጃቢዎቻቸውም ጭምር) በእንግሊዝ ወታደሮች ተገድለው አለቁ፡፡በስተመጨረሻም እርሳቸውም በሽጉጣቸው አናታቸውን አስፈነዱትና የትያትር ቤት ተዋናዮችን ቀልብ በእጅጉ መሳብ ቻሉ፡፡


የመንግስቱ ሃይለማርያም ጭካኔና ትዕቢትም እንዲሁ መላው ዓለም የሚመሰክረውና ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ነው፡፡መንጌ የስልጣን ጥሙን እስኪያረካ ደርስ ‹‹ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም›› በሚል መፈክር ህዝቡን ሲያጃጅል ከርሞ ሃገራችን ደምበደም አደረጋት፡፡ ከዛም በአፍሪካ አንደኛ እንደ ነበረ የሚነገርለት የመከላከያ ሰራዊት አቋቆመና ማን እንደኔ በሚል ትዕቢት ተወጥሮ ጠላቶቹን ‹‹ትሐህት፣ቅማላም፣ምንትስ›› እያለ ማጣጣሉን ገፋበት፡፡እንዚያ ትሐህት እያለ በወሬ ብቻ ሲያንቋሽሻቸው የነበሩት ታጋዮች ግን ያ አንጀቴ የተባለለት ሰራዊቱን ማባረር ጀመሩ፡፡መንጌም በየቴለቪዥን ጣብያው ያለ የሌለውን መቀባጠር ጀመረ፡፡በመጨረሻም ‹‹አንድ ጥይትና አንድ ሰው አሲኪቀር ድረስ›› እንደሚዋጋ ቃል ገብቶ ሲያበቃ የተኩስ ድምፅ ሳይሰማ መንበረ ስልጣኑን ትቶ ፈረጠጠ፡፡ይህ ነው የሁሉም ፈሪዎችና ትዕቢተኞች መጨረሻ‹‹በለፈለፉት አፍ ይጠፉ›› እንዲሉ፡፡


አሁንም የፈለገው ያህል በቴክኖሎጂ የታገዘ የጦር መሳርያ ባለቤት እንሁን ጉራና ትዕቢቱ የቆይልን ነው እምለው፡፡ትዕቢተኛ ሰው ወይም ሃገረ ገዢ በጣም የተነፋ ፊኛ ምስሎ ይሰማኛል፡፡ ፊኛ ሲነፋ ጠንካራና ሙሉ መስሎ ይታያል… እንዲሁ ሲመለከቱት በቀላሉ እጅ የሚሰጥ አይመስልም፡፡በስለታም ነገር ትንሽ ቢነካ፣ቢረገጥ ወይም በቡጢ ቢመታ ግን ወድያው ይፈነዳል፤ ይተነፍሳል፡፡አንዴ ከፈነዳ ደግሞ የነበረም አይመስልም፡፡እናም የፊኛ እጣ እንዳይ ደርስብን ከመጠን በላይ የተወጥረን መስለን መታየት የለብንም የሚል አቋም አለኝ፡፡


No comments:

Post a Comment