Tuesday, February 5, 2013

ዝርፍያ፡ ድሮና ዘንድሮ




በዚህ ዘመን የማይዘረፍ ነገር የለም፡፡ምሁራን ይህ ያለንበት ክፍለ ዘመን የመረጃ ዘመን የሉታል፡፡ጊዜና መረጃ እኩል የሚሮጡበት ዘመን ነው፡፡ለሰው ልጅ ሂይወት ወሳኝ የሆነ መረጃ እንደተገኘ በጊዜው ጥቅም ላይ ካልዋለ ከትንሽ ጊዜ በኃላ ከትዝታነት የሚያልፍ ፋይዳ አይነረውም፡፡እናም በአሁኑ ዘመን ዓለም እንደ ሸረሪት የተሳሰረች ስለሆነች የንብረት ብቻ ሳይሆን የጊዜ ቀማኞችም እንደ አሸን ፈልቷል፡፡

ልክ ነው አጭበርባሪዎች፣ዘራፊዎችና ኪስ አውላቂዎች የሰው ንብረት ለመዘረፍ ማዘናጋትን እንደ ቀዳሚ ምርጫቸው አድርገው ይጠቀሙበታል… በተለይ የአዲስ አበባ ሌቦች፡፡ ሌብነት በሃይማኖት ሃጥያት፣ በባህላችን ነውር በሕግ ደግሞ ወንጀል ነው ቢባልም አሁንም ከማሕበራዊ ንሯችን ልናስወግደው አልቻልንም፡፡እንደውም ከጊዜ ወደ ጊዜ ድግግሞሹ እየበዛና አፈፃፀሙም እየከፋ ይገኛል፡፡በተለይ ትላልቅ ከተሞች የሽፍቶች መሸሸግያና መናሃርያ ጫካዎች እየሁኑ ነው፡፡ኪስ አውላቂዎችም ከኪስ አውላቂነት ወደ እስትንፋስ አውላቂነት በመሸጋገር ‹‹ማጅራት መቺ›› የሚል መዓርግ ተቀዳጅቷል፡፡  

ነገር ግን ለገንዘብ ሲባል መተክያ የሌለውን የሰው ሂይወት ከሚያጠፉ ማጅራት መቺዎች የኪስ አውላቂዎች አዘራረፍ ይሻል ነበር፡፡እንደውም አንዳነዴ አሰራረቃቸው በመጠኑ ፈገግ ያሰኛል…የጦጣና ቀበሮ ባህሪ ነው ያላቸው፡፡የማጅራት መቺዎች መሳርያ ክንድ ብቻ ሲሆን ኪስ አውላቂዎች ግን እጅግ ውስብስብ የሆኑ የስነ ጥበብ አስተሳሰቦችን በመጠቀም ነው ዓላማቸውን የሚፈፅሙት፡፡ኪስ አውላቂዎች የኪስ መጠን ጠንቅቀው ያውቃሉ፤ወደ ባዶ ኪስ ዝው ብለው አይገቡም፡፡ ከዝርፍያው ክብደትና ቅለት ተመጣጣኝ የሆነ ጥናት ያካሂዳሉ፤ትርፍና ኪሳራቸውን ይቀምራሉ፡፡እናም ትልቁ መሳርያቸው አእምሮ ነው፡፡አእምሮን ተጠቅሞ የሚከናወን ስራ ደግሞ እንደ ፈረጠመ ክንድ መሰንዘር ቀላል አይደለም፡፡

የማጅራት መቺዎች አሰራር ግን ከአሸባሪነት የማይተናነስ እንስሳዊ ተግባር ነው፡፡መጀመርያ ይገድላሉ ከዛም ኪስ ይፈትሻሉ፤ካገኙ እስየው ካላገኙም ምራቃቸውን እሬሳው ላይ በመትፋት እየተራገሙ ወደ ሌላ ግድያ ያመራሉ፡፡እንዚህ ሰዎች ከጅብ የሚለዩት ቤት ውስጥ ሰለሚኖሩ ብቻ ነው፡፡ልክ እንደ ጅብ ዝርፍያውም ግድያውም የሚያከናውኑት ጨለማን ተግን አድርገው ነው፡፡ህሊናና አእምሯቸው በተለያዩ ስሶች ታውረዋል፡፡የቀቢፀ ተስፋ አኗኗር ነው ሚመሩት፡፡‹‹የሰው ልጅ ሰው የሆነው ሰውን ገድሎ ነው››በሚል የጫካ ሕግ ይመራሉ፡፡ማጅራት መቺዎች በአብዛኛው ጊዜ ግለሰቦች ሳይሆኑ ብዱኖችና ደርጅቶች ናቸው… ‹‹ተደራጅተው ይገድላሉ፣ከዛም ይዘርፋሉ››… በደመ ነፍስ፡፡ይህ ዓይነት የመንግስት መዋቅሮችም ይጨምራል…ሙስናና ኩረጃ!!!

በአንድ ስሙን በውል የማላስታውሰው መፂሔት ያነበብኩት ገጠመኝ እንደ ምሳሌ ላቅርብ፡፡ልጁ ወጠምሻ ነገር ነው አሉ፡፡እናም የሰፈሩ ልጆች አደራጅቶ ማጅራት እየመታና የግዳዮቹን ኪስ እየበረበረ በሚያገኘው ገንዘብ ይጠጣል፣ያጨሳል፣ይጨብሳል ሌላም ሌላም ያደርጋል፡፡አንድ ምሽት ታድያ  እንደልማዱ ለማድረግ ከግብረ አበሮቹ ጋር  ሁኖ በሆነ አሳቻ ቦታ አሽምቆ ይጠብቃል፡፡ከዛም አንድ ሽማግሌ ከዘበኝነት ስራቸው ወደ ቤታቸው ሲያዘግሙ ይመለከታሉ፡፡ያወጠምሻ ጥግ ይዞ ጓደኞቹን በሉት አላቸው…በምልክት፡፡እንዚያ ወመኔዎች ተንደርድረው ሂደው ያሚስኪኑን ሽማግሌ አንገት ቆልምመው ግደሏቸውና ኪሳቸውን በርብረው ያገኟት ሐምሳ ብር ይዘው ሊሄዱ ሲሉ አንዱ ፊታቸውን ትኩር ብሎ ሲመለከት የወጠምሻው አባት መሆናቸው አወቀና ድንገት ራሱን ይዞ‹‹ጋሼ እንትና! ጋሼ! ጋሼ!›› እያለ እየየውን አቀለጠው፡፡ወሮበላው ማጅራት መቺ በፀፀት አንጀቱ አረረ፤ተቃጠለ፣ጨሆ አባቴ አባቴ እያለ አለቀሰ፡፡ነገር ግን በመፀፀትና በማልቀስ ሊመልሳቸው አልቻለም፡፡የእጁን በእጁ አገኛት!!!

ዘራፊዎች ድሮም ነበሩ፤አሉ ለወደፊትም ይኖራሉ፡፡በዕዳዊ አገዛዝ፣ ሽፍትነትና የባርያ ገባያ ድሮ የነበሩ አሁንም ያሉ ሰይጣናዊ የዝርፍያ ዓይነቶች ናቸው፡፡የድሮው ዝርፍያ የግለሰቦች፣ድርጅቶችና የላዓለዊ ሃገሮች ድምበር በመሻገር በጉልበት የሚፈፀም ነበር፡፡አሁን ግን የትም ሳይንቀሳቀሱ ባንኮች፣የግለሰብና የድርጅት ምስጢሮች፣ የሃገር ድሕንነት ወዘተ አደጋ ላይ የሚጥሉ ምስጢራዊ ሰነዶች በርቀት እየተመነተፉ ይገኛሉ፡፡

የሚዘረፍ ምስጢር ካልተገኘም አግልግሎት ማሳጣት(Denial of service)የሚባል የጊዜ ስርቆት አለ፡፡ኮምፒተሮች በተጠቃሚያቸው የታዘዙት ስራ እንዳይ ሰሩ የሚያስተጓጉል መጥፎ ተግባር ነው፡፡
ኢራን እስራኤልን ስትወነጅል እንደነበር በቅርቡ የምናስታውሰው ጉዳይ ነው፡፡የኒኩለር ማበልፀጊያ ቴክኖለጂዋ በቫይረስ ስለተጠቃባት፡፡ጁልያን አሳንጅም አምባገነኗን አሜሪካን ሳይቅር ጉድ አስኝቷት ነበር፡፡ዊኪ ሊክስ ብሎ በሰየመው ድረገፁ ላይ ያጋልጣቸው በነበሩ የአፍጋኒስታንና የኢራቅ ዘግናኝ ግፎች፡፡ አሜሪካ አሁንም ቻይናን ጥብቅ ምስጢሮቼን እየዘረፈችብኝ ነው ስትል እየወቀሰች ነው፡፡ሌባን ሌባ ቢዘርፈው ምኑን ይደንቃል?

እናም ዝርፍያ ከጊዜው ጋር እየዘመነ፣ የአዳዲስ ፈጠራዎች ባለ ቤት በመሆን የዘራፊዎችን ንሮ እያበለፀገ ይገኛል፡፡ዘራፊዎች ሁሌም ዓይናቸውን በሌሎች ንብረትና ምንነት እዳንከራተቱ የኖራሉ፡፡የናጠጠ ቱጃር ሁነውም የሚስኪኑ ወገናቸው ንብረት፣ጉልበትና ጊዜ ከመመንተፍ ዓይናቸውን አያሹም፡፡

No comments:

Post a Comment