ውድ ጓደኛየ ሰላም ይበልጣል ሆይ እንደምነህልኝ?መላው አብሮ አደጎቻችን፣ቤተሰብና ወገንዘመዳችን አማን
ነው?ደጉና ጀግናው የገጠር ኗሪ ህዝባችንስ እንዴት
ነው?ያጭቃ አብኩተን፣ወሃ ተራጭተን፣ተረት ተረት፣ድብብቆሽ፣እሽቅድድምና
ሌሎች መቸም የማይረሱ እጅግ በሚያዝናኑ ጨዋታዎች እየተደሰትን ያደግንበት ቀያችንስ?ቸሩ እግዚሔር ይመስገን እኔ ደህና ነኝ… ካንተ ናፍቆት በስተቀር፡፡ያአብረን ያደግንበት ጋራ ሸንተረሩ፣ሜዳና
ገደሉ፣ ወንዝና ጫካው እንዴት እንደናፈቀን ልነገርህ አልችልም፡፡ያበሃዘንም ሆነ በደስታ ሃፍትና ደህነት፣ ሰላምና ጦርነት እንዲሁም
የሃይማኖት ልዩነት ሳይለው ያለውን በፍቅር እየተካፋፈለ አብሮ የሚኖረው
የደግነት ተምሳሌት ወገናችንሰ በትል ሰላም?
ውድ ሰላም ሆይ! ፍቅር፣መተሳሰብ፣ መረዳዳትና አብሮ
መኖር እኮ በኛ አከባቢ ቀረ፡፡እንደምታውቀው በኛ አከባቢ ስትለያይ ዳግም በሰላም ለመገናኘት በጎውን ሁሉ በመመኘት፣እንባ በመራጨት
ደናሁን ደናሁኚ እየተባባልክ ነው፡፡ስትገናኝም እንዲሁ ሞቅ ያለ ያአክብሮት ሰላምታ በመለዋወጥ ነው፡፡ በኛ አከባቢ እወቀው አትወቀው
በንገድህ ለሚያጋጥምህ ሰው ሁሉ ‹‹እንደምን ዋሉ፣ እንደምን አደሩ፣እንደምን አመሹ፣አረፈዱ›› ካልተባባልክ ‹‹ምነው እንደ እንስሳ
ዝምብሎ ያልፋልሳ?›› ትባላለህ፡፡የእገዚሔር
ሰላምታ የምታ የምትነፋፈገው በከረረ ጥላቻ ላይ ስትሆን ብቻ ነው፡፡ይህም በሃገር ሽማግሌዎች አማካኝነት በቀላሉ ይፈታል፡፡
እዚሁ አዲስ አባባ ግን ይህ ነገር እንደ ፋራ ያስቆጥርሃል፡፡ባንድ
ህንፃ ውስጥ አብረህ እየኖርክ የእገዚሔር ሰላምታ መለዋወጥ እንደ ነውር ይቆጠራል፡፡የአዲሰ አባባ ሰዎች ሲገናኙና ሲለያዩ እምባ
የሚራጩት ቦሌ የአውሮፕላን ማረፍያ፣ በፊልምና በሙዚቃ ምስሎች ብቻ ነው፡፡እናም ሰዎች እንደሚነፋፈቁ ለማወቅ ከፈልግ አንድም ወደ ቦሌ የአውሮፕላን ማረፍያ ጎራ ማለት አለብህ አልያም ፍቅረኛሞች ሲለያዩና
ሲገናኙ የሚያሳይ ፊልም ወይም በምስል የታጀበ ሙዚቃ ማየት የግድ ይልሃል፡፡
እንደምታስታውሰው የድሮው የኢትዮጵያ ተሌኮምንኬሽን ኮርፖሬሽን(ነብሱን
ይማረውና) አንድ የማይረሳ መፈክር ነበረው፤ ‹‹ኢትዮጵያን ከመጭው ዘመን ጋር መገናኘት›› የሚል፡፡እንኳን ዘመድ ካዝማድና ወገን
ከወገን ዘመን ከዘመንም ለማገናኘት ይፎክር ነበር፡፡ አሁን ግን ያነገር ቀርቷል… በመፈክርም በተግባርም፡፡ኢትዮተሌኮም ‹‹የጋራ
ስኬት(shared success)›› እያለ ይፎክራል፡፡ ስለየትኛው ስኬት እንደሆነ ግን አልገባኝም…ትርፉ ለግሌ ብስጭቱ ግን ለደምበኞቼ
ቢል ያምርበት ነበር፡፡ደብዳቤ መፃፍ እስከዚህም ነኝ፤ ግን ምንታደርጓለህ?ይህ የደምበኞቹን ንጉስ መሆኑን በተግባር የስመሰከረ መስራቤት በስልክና በኢንተርነት እንዳንገናኝ ስለከለከን
ናፍቆቴን ለመግለፅ ይችን ደብዳቤ እየፃፍኩልህ ነው፡፡ተሌ በሞባይላችን ያለው የፅሑፍ መልክት መቀበያ ሳጥን እንደ ማስተወቅያ ሰሌዳ
ብቻ መጠቀሙን ካቆመና እንድንላላክ ከፈቀደልን ግን ‹‹መሰጅ›› አድርግልሃለሁ፡፡
በለፈው ሳምንት ስልክ ቁጥርህን በስንት መከራ አፈላልጌ
እንዳገኘሁ ልደውልልህ ደጋግሜ ብሞክር ያች የተሌ ውሸታም ሰትዮ‹‹ይቅርታ(የስላቅ ምልክት)የደወልላቸው ደምበኛ ከአገልግሎት መስጫ
ክልል ውጪ ናቸው፡፡እባክዎ ትንሽ ቆይተው ይደውሉ›› እያለች ስታስቸግረኝ ጊዜ ተስፋ ቆርጬ ተውኩት፡፡አይገርምህም!ገንዘብህን ከፍለህ
ከናፈቅከው ጓደኛህ ጋር እንዳትገናኝ እየከለከለች ደጋገማ‹‹ይቅርታ›› መለቷ አያናድድም?ይቅርታ ሲባል በፈፀምኩት በደል ተፀፅቼለሁ፣ ተሳስቼ
አስቀይሜሃለሁ፣ ከአሁን በኋላ አይለመደኝም፤ ለአሁን ብቻ ማረኝ ይቅር በለኝ ማለት አያደልም እንዴ?በተደጋጋሚ እየጎዱ ደጋግመው የቅርታ መጠየቅ ምፀት ነው፤…ምንያመጣል
ከሚል አስተሳሰብ የሚመነጭ የንቀት ምልክት፡፡ለዛም ነው ‹‹ትንሽ ቆይተው ይደውሉ›› ትልህና ከአንድ ሰዓት በኋላ ብትሞክርም አይሳካልህም፡፡
የሚገርመው ደግሞ ደውለህ ለማግኘት ስትሞክር ብቻ አይደለም
እንዲህ የምትለው፡፡ ከስንት ጊዜ ምኮራ በኋላ ቀንቶህ የናፈቀከውን ወዳጅና ዘመድ አግኘተህ እጅግ ተመስጠህ እየተነጋገርክ እያለህም
ጣልቃ ትገባና‹‹ መስመሮቹ ሁሉም ለጊዜው ተይዟል፡፡እባክዎ ትንሽ ቆይተው ይደውሉ ›› በማለት መስመሩን ትቆርጧለች…ያች የፍቅር
ምቀኛ!የመገናኘት፣መጠያየቅ፣ሰላምታ ልውውጥ ፀር!በገኛት በጥርሶቼና ጥፍሮቼ ነበር ቦጭቄ ቦጫጭቄ ወፎችን ለማስበርገግ በእንጨት ላይ
የተሰቀል ብትቶ ጨርቅ እማስመስላት፡፡
የምወድህና የማከብርህ ሰላም ይብልጣል ሆይ ባለፈው’ለታ ወደ አዲስ አበባ መጥተህ መኖር እንደምትፈልግ ከነገርከኝ በኋላ ነበር ስልኩ
ድንገት የተቋረጠው፡፡ከመምጣትህ በፊት ግን ስለ አዲስ አበባ አንድ አንድ ነገሮች ልንገርህ፡፡አዲስ በእድገት ግስጋሴ ላይ መሆኗን
የሚያመለክቱ የህንፃ ግንባታዎች እዚህም እዛም ይታያሉ፡፡አሁን ደግሞ የባቡር መስመር ግንባታ
ተጀምሯል…እየተፋጠነ ነው፡፡ሰፋፊ አስፓልቶቸም በመሰራት ላይ ናቸው፡፡
ነግር ግን ኗሪዎቿ በትራንስፖርት እጥረት፣በውሃና መብራት መቆራረጥ፣በቤት
ክራይና በንሮ ውድነት እየማቀቁ ይገኛሉ፡፡በፈልከው ሰዓት የፈለከው ነገር በጊዜው ማከናወን አትችልም፡፡ይቅርና የኢትዮጵያ ትላልቅ
ባለስልጣናት የአፍሪካ ህብረት መሪዎች መቀመጫም እዛው አይደልም እንዴ? ብለህ ልትጠይቅ
ትችላለህ፡፡አልተሳሳትክም! እነዚህ ባለስልጣናት እዚህ የሚኖሩት ለችግሮቻችን መፍትሔ ለማፈላለግ ሳይሆን ምኞታቸውን ለመናገር ነው፡፡ምኞት
ደግሞ ማንም ያመኛል፡፡ምኞት ከቅዠት በምን ይለያል ጃል?
አዲስ አበባ ስትኖር ብዙ
የሚያበሳጩና ግራ የሚያጋቡ ነገሮች ያጋጥሙሃል፡፡ለምሳሌ ያክል የሚከተሉትን ልጥቀስልህና ሐሳቤን በዚሁ ልቋጭ፡፡
1.
እንደኔ ተከራይተህ የምትኖር ከሆነ፣ አምሽተህ
ቤት እንዳትገባ ማጅራት መቺዎች(የከተማ ሽፍቶች)ይገድሉሃል፤ በግዚ ከገባህ ደግሞ አከራዮች ያፈጡብሃል፣ የቤት ከራይ ጨምር ወይም
ቤቱን ለቀህ ውጣ ወዘተ ሊሉህ ይችላሉ፡፡ ግራ ትጋባለህ፣ ተበሳጫለህም፡፡
2.
የስራ ቅጥረኛ ከሆንክ፣ ካረፈድክ የቅርብ
አለቃህ ይቀጣሃል(ከስራ ማባረርም ጭምር)፣ በሰዓቱ ቢሮ እንዳትገኝም ታክሲ አታገኝም፤ ብታገኝም በትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት ቶሎ
አትደርስም፤… ሌላ ብስጭት፣ ሌላ ግራ መጋባት፡፡
3.
በአዲስ አበባ ጎደናዎች በእግርህ ስትጓዝ
በሆነ ግምብ ላይ ‹‹እዚህ አከባቢ መሽናት ክልክል ነው›› የሚል ማስታወቅያ ተለጥፎ ስታይ ብዙ ሰዎች ተሰልፈው ሲሸኑና ሲፀዳዱ
ትመለከታለህ፡፡አፍንጫን የሚቆርጥ ሽታም ያጋጥምሃል፡፡በአዲሳባኛ አባባል ‹‹የተከለከለ ነው›› ማለት ‹‹ የተፈቀደ ነው፣ይቻላል››
የሚል ትርጉም ያለው ይመስላል፡፡
4.
‹‹አከባቢያችንን ፅዱና በአረንጓዴ እትክልቶች
የተሸፈን እናድርግ›› የሚል መፈክር የተፃፈበት ታፔላ ካስተዋልክ፣ ያአከባቢ በቆሻሻ ክምር፣ በሰዎች ተረጋግጠውና ተቆራርጠው በደረቁ
አትክልቶች ወዘተ ምስቅልቅሉን ወጥቶ ነው የምትመለከተው፡፡
5.
በልብስ መሸጫ ስቆች ‹‹በቅናሽ ዋጋ እንሸጣለን››
የሚል በፕላስቲክ የታሸገ የማስታወቅያ ፅሑፍ አንብበህ ወደ ስቁ ጎራ ስትል፣ አንድም ከአስፓልት ዳር ተለቃቅመው የተገዙ ልብሶች(ስልባጆች)
ታያለህ አልያም ወጋቸው በእጥፍ መጨመሩን ትገነዘባለህ፡፡በአዲሳባኛ አባባል ‹‹ማይት ማመን አይደለም››፡፡
6.
ልመናና አለማመን ቦታ፣ፆታ፣ቁመናና ዕድሜ
አይለይም፡፡አንድ ካንተ በሶስት እጥፍ የሚበልጥ ጎረምሳ ‹‹ነብሴ ሳንቲም ሙላልኝ›› ይልሃል፡፡ ከምን ምንያህል እንደጎደለበት ራሱ
ነው የሚያውቀው፡፡ምን የሚያካክሉ ግብዳ ሴቶችም እንዲሁ ይላሉ፡፡ከሁሉም በላይ አንጀት የሚበላው ግን ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ
ህፃናት ‹‹ ጋሼ ለዳቦ መግዥያ ሳንቲም ስጠን›› እያሉ አፈር ለብሰው በሚያሳዝን ድምፅ ሲማፀኑ መመልከት ነው፡፡ አንድ አንድ የውስጥ
አዋቂዎች ግን እነዚህ ህፃናት የሚለምኑት ለራሳቸው አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡‹‹በልጅ አመካኝቶ ይበላል አንግቶ›› ሲባል አልሰማህም?
7.
እጅግ ብዙ ሰዎች የሚበላ አጥተው ከልክ በላይ
የከሱና ሆድና ጀርባቸው ተጣብቆ የተሰፋ የሚመስል ቁመና ያላቸው ወገኖች ስትመለከት ቆይተህ ትንሽ እንደተጓዝክ ደግሞ ክልክ በላይ
ከመብላታቸው የተነሳ ባምቡላ የሚመስሉ መንቀሳቀስ ያቀተቸው ሮቶዎች ተገኛለህ፡፡ሁለቱም ያሳዝናሉ፤ ከልክ በላይ በሆነ ርሃብና ክልክ በላይ በመብላት አካለስንኩል ሁኗል…<<The two
extremes are always vices>> እንዳለው ግሪካዊው ፈላስፋ አሪስጣጥሊስ፡፡
8.
እንዱ ሰማይ ጠቀስ በሆነ ፎቅ ወይም ቤተ
መንግስት በሚመስል ቪላ ሁሉንም ነገር ተማልቶለት ተንደላቆ ሲኖር ሌለው ከፎቁ ስር በሚገኘው አስፓልት ላይ በባዶ ሆዱ እጅና እግር
በሚቆራርጥ ብርድና እንደ ቅቤ በሚያቀልጥ ፀሐይ እየተቃጠለ የኖራል፡፡‹‹ዓለም ደሮ ናት፤ ላንዱ እንቁላል፣ለሌላው ኩስ ተጥላለች››
ይሉሃል ይህ ነው፡፡
ውድ አብሮ
አደጌ ስላም ይበልጣል እንግዲህ ለዛሬው በዚሁ ይብቃን፡፡በሚቀጥለው ጊዜ በስልክ የልብ ልባችንን እንድናወራ ፈጣሪ ለኢትዮተሌኮም
ማስቷሉን የቸረው ዘንድ በትጋት እፀልያለሁ፡፡ ያች በስላቅ‹‹ይቅርታ፣የደወልላቸው
ደምበኛ ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጪ ናቸው፡፡›› እያለች የምታደርቀንና እንዳንገናኝ የምትዋሸው ሰትዮም የበጋ መብረቅ ያድርቃት
ብያለሁ፡፡ ፈጣሪ ፆሎቴን ከሰማ በእርግጠኝነት እደውልልሃለሁ፤ አካል ሆነ ግን በሌላ ደብዳቤ እስክንገናኝ ድረስ ሰላም ሁንልኝ፡፡አሜን!
የምንጊዜም ወዳጅህና አክባሪህ
አስፋው ገዳሙ
አዲስ አበባ፡፡
No comments:
Post a Comment