Friday, June 28, 2013

ደደቢት





የካቲት 1966 ዓ.ም የአፄ ሃይለስላሴ ዘውዳዊው ስርዓት ከስሩ ምሶ የሚያፈራርስ የህዝብ ተቃውሞ አጋጥሞታል፡፡ሊወልቅ እንደ ተቃረበ ጥርስ መነቃነቅ ጀሯል፡፡የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች 

‹‹መሬት ላራሹ አትሽሹ››፣


‹‹ ወዝ አደር ወዝ አደር

ወዝ አደር ገበሬ

በርታ ለአነት ሆኗል


ጥገትና በሬ፡፡››  



የሚሉና ሌሎች የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄዎች የሚያስተጋቡ መፈክሮችን አንግበው የአዲስ አበባ ጎደናዎችን እያጨናነቁ ነው፡፡የታክሲ ሹፌሮች፣አስተማሪዎችና የመንግስት ሰራተኞችም ስራ የማቆም አድማ በማድረግ የአፄው ንጉሳዊ አገዛዝ ከስረ መሰረቱ ለማናጋት ቆርጠው ተነስቷል፡፡የአፄው አገዛዝ ግን ቀጥተኛ መልስ ከመስጠት ይልቅ ‹‹የእንዳልካቸው ካቢኔ›› ምናምን እያለ የስልጣን እድሜውን ለማራዘም ‹‹መሟዘዙን›› የሙጢኝ አለው፡፡

የዝያኔው ሞላጫ ወታደሮች ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የደሞዝ ጭማሪ ይደረግልን በሚል ሰበብ ተጋግሎ በመቀጣጠል የነበረው ህዝባዊ አመፅ የስልጣን ጥማቸውን ማርክያ አደረጉት፡፡ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም የወታደራዊው አምባገነን ደርግ ምስረታ እውን ሆነ፡፡ቀጥሎም የአምባገነንነቱን አመላካች የሆኑ አዋጆችን ማወጅ ጀመረ፡፡
ደርግ ‹‹ዴሞክራሲያዊ አስተደደር ለጭቁኖች አሁን››፣‹‹ኢትዮጵያ ወይም ሞት››፣‹‹ከምንም በላይ አብዮቱ››፣‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም›› ወዘተ የመሳሰሉ የውሸት መፈክሮች አንግቦ ማስተጋባት ሲጀምር እነኢህአፓ ደግሞ ‹‹ገዜያዊ ህዝባዊ አስተደደር አሁን››፣‹‹እናቸንፋልን››ወዘተ በማለት የመልስ ምት ማስተጋባቱን ተያያዙት፡፡

የደርግ አዋጆች በቢሮከራሲዎች፣በአህአፓና በሜኢሶን ተቃውሞ ገጠመው፡፡የዘውዳዊው ስርዓት ርዝራዦችም ቢሆን ሙሉ በሙሉ አልከሰሙም ነበር፡፡መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ዘውዳዊው ስርዓት ተገርስሶ በወታደራዊው አምባገነን መተካቱን የኢትዮጵያ ህዝብ መርዶ ሰማ፡፡ከዛም የደርግ አዋጆች መጉረፍ ቀጠሉ፡፡
ደርግ ሕዳር 12፣ 1967 ዓ.ም ‹‹ማንኛውም ሰው ኢትዮጵያ ትቅደም የሚለውን ዓላማ ለመፈፀም በመንግስት ወይም በመንግስት በለስልጣን የሚወጡ አዋጆች፣ድንጋጌዎች፣ትእዛዞች እና ደሞቦች እንደይከበሩ፣በንግግር፣በፅሑፍ ወይም በማንኛውም መንገድ በግልፅ ሲያነሳሳና ሲያደፋፈር ከተገኘ ከአንድ እስከ 10 ዓመት በሚደርስ ከባድ የእስር ቅጣት ይቀጣል›› የሚል አዋጅ አውጥቶ ማንኛውም ሰላማዊ ተቃውሞ ተቀባይነት እንደሌለው አሳወቀ፡፡ወደዳችሁም ጠላችሁም የኢትዮጵያ ፈላጭ ቆራጭ እኔ ነኝ አለ፤በድፍረት፡፡

ሰላማዊው የህዝብ ተቃውሞ ወደ ለየለት የእርሰ በርስ ደም መፋሰስ ተሸጋገረ፡፡ኢህአፓዎች ማንኛውም የነሱ ዓላማ ተቃዋሚ መስሎ የታያቸውን ሁሉ ጭጭ ለማድረግ የከተማው ነጭ ሽብር አቀጣጠሉት፡፡ ደርግ ነጭ ሽብሩን በቀይ ሽብር መታው፡፡ኢትዮጵያ ደም አነባች፤በልጆቿ ደም ታጠበች፡፡ሃገር የደም ሃይቅ ሆነች፤የደርግ ጀሌዎች የወንደሞቻቸው ደም በአንድ ትንፋሽ ጭልጥ አድርገው ከልክ በላይ ሰከሩ፤ ሰክረውም የዲያብሎስ ጭሆት ጨሁ… ኢትዮጵያ ትቅደም! እያሉ እማማ ኢትዮጵያን ለሞት አሳልፈው ሰጧት፡፡

ከ1960 ዓ.ም ጀምሮ በጋራ ይንቀሳቀሱ የነበሩ የብሄረ ትግራይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማሕበር ወደ ማገብት ተቀየረ፡፡ማገብት(ማሕበር ገስገስቲ ብሄረ ትግራይ…የብሄረ ትግራይ ተራማጆች ማሕበር) የከተማው ሰላማዊ ትግል እንደማያዋጣ ስለተገነዘበች ሌላ መንገድ መፈላለግ ጀመረች፡፡ስብሰባዎች በድብቅ መካሄዳቸው ቀጠለ፤‹‹የከተማው ትግል አያዋጣም፤ረዥምና መራራ የትጥቅ ትግል›› ለማካሄድ ተስማሙ፡፡በዚህም መሰረት ማገብት በሶስት ብዱኖች ተከፋፈለች፡፡
አንደኛው ብዱን የከተማው ስምሪት ለማጠናከር በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ተሰማራ፡፡ሁለተኛው ወደ አስመራ በማቅናት እዛው የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች በትጥቅ ትግሉ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማግባባትና ከሻዕብያ ጋር ግንኙነት በመፍጠር ወታደራዊ ስልጠና ለመውሰድ ያለመ የቤት ስራ ተስጥቶታል፡፡ሶስተኛው ግን ወደ ደደቢት አመራ፤በምድረ ትግራይ የነፃነት ትግል በይፋ መጀመሩን ለማብሰር፤የነፃነት ጅቦ ለማቀጣጠል፡፡

በአፄው ጊዜ የፓርላማ አባል የነበረው አየለ ገሰሰ(ስሑል) ለትጥ ትግል አመቺ የሆነ ቦታ  እንዲያጠና በተሰጠው የስራ ድርሻ መሰረት በሰሜን ኢትዮጵያ፣ በምዕራብ ትግራይ በአድያቦና አስገደ ፅምብላ አከባቢ የምትገኘው ደደቢት ተመራጭ መሆኗን ለትግል ጓዶቹን አበሰረ፡፡ደደቢት በሱዳን ደምበር ትገኛለች፤ ጠላት ገፍቶ ቢመጣ ወደ ሱዳን ለማፈግፈግ፣ከነፍሰ በሎቹ የደርግ ሚጎች ለመሸሸግ፣ውሃና ምግብ በቀላሉ ለማግኘትና ህዝቡን ለማስታጠቅ አቻ የማይገኝላት ስፍራ በመሆን ተመረጠች… ደደቢት፡፡

በጥናቱ መሰረት 11 የማገበት አባላት በየካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም አንድ ጓንዴ፣አንድ ካርባይን፣ አንድ ቶምሶን፣አንድ ሳንጃ አልቢን እና አንድ ሽጉጥ(በአጠቃላይ አምስት ኋላ ቀር መሳርያዎች) ይዘው ደደቢት ደረሱ፡፡የትግል ችቦው ለኮሱ፤የነፃነት ትግሉ በይፋ ተበሰረ፡፡ዳግባይ ወያነ ትግራይ እውን ሆነ፡፡የትግራይ ህዝብ እና መሬት እንደልማዳቸው ‹‹ለፋሽስቶች አልገዛም! በጭራሽ!›› ብለው ለነፃነታቸው ለመፋለም ተነሱ፡፡ትግራይ ዳግም አነባች… በሃዘን፣በችግር፣በግፍ ጭቆና፣በድርቅ፣በጦርነት እንደገና… እንደገና የገሃንም ደጆች ተከፍተው በማይጠፋ እሳት ነደደች፣እንደበረዶ ድንገይ የበሚያደርግ ቅዝቃዜ ተቃጠለች፣በማያንቀላፋ… በቃኝ በማያውቅ ዲያብሎስ ልጆቿን አጣች፡፡የትግራይ ሰማይ ይህን አይቶ ደነገጠ፤ክው አለ፡፡ ወደ ሰባተኛው ሰማይ ሸሸ…ቢጠብቁት ቢጠብቁት…ሳይመለስ ለዘመናት እዛው ደርቆ፣ተንጠልጥሎ ቀረ፡፡ትግራይ በርሃብ ተመታች! ይህን አልበቃ ብሏት በምድር እሳት…በሰማይ እሳት … እንደ ቡርክታ በእሳት ባህር ተጠበሰች፡፡

‹‹እንዳያሉፍት የለምያሁሉ ታለፈ



ታጋይ ህዝብ ልጅበደሙ በላቡ ደማቅ ታሪክ ፃፈ…››



ታሪክ ለታሪክ ሰሪው እንጂ ለፃሐፊውና ለአንባቢው ምንግዜም ቢሆን እስከዚህም ነው፡፡እነ ጀብሃ፣አህአፓ፣ግንባር ግድሊ ትግራይ፣እድዩ፣ጠርናፊት በትግሉ ከስመው ቀሩ፡፡የደደቢት ልጆች የሻምፔንነነት ፉክክሩን ተቆናጠጡት፡፡የደርግ ዘመቻዎች ፍሬ ማፍራት ተሳናቸው…የደደቢት ልጆች በሜዳቸውና በደጋፊያቸው ፊት ነበርና የሚጫወቱት፡፡የቀይ ከከው ዘመቻ፣የሽራሮ ዘመቻ፣የዓድዋ ዘመቻ፣(የልምጭ?) ዘመቻ… ዘመቻ… ዘመቻ… ዘመቻ…ሁሉንም ዘመቻዎች በደደቢቶች አሸናፊነት ተጠናቀቁ፡፡የደደቢት ልጆች ትግል ከተጀመረ በ15 ዓመታቸው(1981 ዓ.ም) መጀመርያ የተነሱበትን ዓላማ አሳኩ፤የትግራይ ህዝብ የነፃነት ሻምፔን ሆነ፡፡ዋንጫውን ከፍ አድርገው የነፃነት ድምፅ አሰሙ፤የኢትዮጵያ ተራሮች ደምፁን በመቀባበል አስተጋቡት፡፡
የትግራይ ህዝብ የነፃነት ሻምፔን መሆን ብቻ ግን ለደደቢቶች በቂ አልነበረም፡፡እናም ትግሉን ገፉበት ለኢትዮጵያ ነፃነት ከሚታገሉ ሌሎች ኢትዮጵያውያኖች ጋር፤ በተላይም ኢህደን!፡፡በ1983 ዓ.ም(ከ17 ረዥምና እልህ አስጨራሽ መራራ ትግል በኋላ) የደደቢት ልጆች ከሌሎች ጓዶቻቸው ጋር የኢትዮጵያ ህዝብ የነፃነት ሻምፔን ሆኑ፡፡የደርግ መሪዎች ለኢትዮጵያ ህዝብ የገቡለት ቃል አንድም ሳያሳኩ አገርጥለው ፈረጠጡ፡፡ኢህአዴግ አዲስ አበባን ተቆጣጠረ፡፡
ሲናገሩ እንጂ ቁምነገር ሲሰሩ የሚይታወቁ አንድ አንድ የሽዋ ምሁራን ተብየዎች በደደቢት ታጋዮች ማሽሟጠጥ ጀመሩ፡፡
የኢህአዴግ ሰራዊት መጠጡ ለስላሳ
የበረሃ አንበሳ የከተማ ኮሳሳ
በማለት ተሳለቁ፡፡እየተሳለቁም ነበር እንገባበት የዝንጀሮ መንጋ አለቁ፡፡

የትግራይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማሕበር ማገብትን ወለደች፣ማገብት አዲስ አበባ ተወልዳ ደደቢት አደገችና ተሀህትን ወለደች፤ ተሀህት ደሞ የትግራይ ብሎም የኢትዮጵያ ነፃነት ፋናወጊዋን ህወሓትን ወለደች፤ህወሓት ደሞ አደገችና፣ጠላቶቿን ሁሉ አምበረከከችና፣ ወዳጆቿን በማሰባሰብ ኢህአዴግን ወልዳ አሳደገች፡፡የእርሰበርስ የደም መፋሰስ ትግሉ አበቃና በሰላማዊ ትግል ተተካ!፡፡እማማ ኢትዮጵያ(ከትግሉ በኋላ አንድ ዓይኗን አጥታም ቢሆን) የደም እምባ ማንባቱን ትታ በመጠኑ ፈገግ በማለት የወላለቁ፣የተሰባበሩ፣የበለዙና ወጣገባ ጥርሶቿን ማሳየት ጀመረች፡፡
እዚህም እዝያም የተሞነጫጨረ፣ከመድርና ከሰማይ በዘነበባት እሳት የታረሰ፣የተማሰ፣የተቦዳደሰ፣የተቆፋፈረ፣እንደ ጥጥ የተበዛዘተ፣እንደ አሮጌ ልብስ የተቀዳደደ፣ የዝንጀሮ መንጋ እንደገባበት ክምር የፈራረሰ …ገ…ላ…ዋ!!!፣ወፍ በልታ ባዶ እንዳስቀረችው ምሸላ ባዶ የቀረው ራስ ቅሏ!፣ምስጥ እንደበላው ዛፍ የሚልፈሰፈሱት እግሮቿ!፣እሳት የለበለባቸው እጆቿን ዓለም እንዳያይባት በሃፍረት መሸማቀቁን እርግፍ አድርጋ በመተው እንደእኩዮቿን ቀና፣ዘና፣ኮራ ብላ ለመራመድ እየተጣጣረች ትገኛለች፡፡

የዛሬ አውራ ጥላቶችዋ አንደኛ ድህነት፣ ሁለተኛ ድህነት፣ሶስተኛ ድህነት ናቸው፡፡ይህ መናጢ ጠላቷን ለማንበርከክ እንዳትችል እንደጋሬጣ ተተክለው አላላውስ፣ አላንቀሳቅስ ያልዋት ደግሞ እነ ሙስና፣የመልካም አስተዳደር እጦት፣ኋላ ቀርነት፣የበሽታዎች ብዛትና የመፍትሔዎቻቸው እጥረት(እጦት)፣የትምህርት ጥራት መጓደል፣የአመራሮች የብቃት መነስና ቸልተኝነት፣የተቃዋሚዎች እና የገዢው ጤነኛ ያልሆኑ ፉክክሮች፣ የፅንፈኛ ደጋፊዎችና የፅንፈኛ ተቃዋሚዎች የዜሮ ድምር ፖለቲካ…እፍፍፍፍፍ!!!እንደው መኖር ከተባለ፣እማማ ኢትዮጵያ ስንቱን ችለሽ ነው የምትኖሪው?
የደደቢት ልጆች ከሌሎች የኢትዮጵያ የትግል አጋሮቻቸው እጅ ለእጅ በመያያዝ በእነዚህ የእማማ ኢትዮጵያ ችግሮች ላይ መዝመት አለባቸው፡፡ድህነት ለማጥፋት የሚደረገው ትግል የማይደግፉ ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል›› ባዮች አስተሳሰባቸውን ለማስተካከል ይሞክሩ፤ካልቻሉ ከእማማ ኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በማበር ትግሉን ከማደናቀፍ ይታቀቡ፤አልታቀብም ካሉ ግን እጆቻቸው ይቀረጠፋሉ፣እግሮቻቸው ይሰበራሉ!!! በእማማ ኢትዮጵያ መቀለዱን ያቁሙ፡፡‹‹እሾህን በእሾህ›› በሃገር ጉዳይ አይሰራም፡፡የደደቢት ልጆች የደርግ አገዛዝን ድባቅ ለመምታት ከሻዕብያ ጋር ተባብረው ነበር፤ኋላም ለኤርትራ ነፃነት ፈቅዷልና እኛም እድሉን የመጠቀም መብት አለን የሚል ከሌሎች ድንቁርና የሚይማር የደንቆሮዎች ደንቆሮ ካለ…እማማ ኢትዮጵያ ይቅርታ አይኖራትም፤በግልፅ መታወቅ አለበት፡፡

ደደቢት እግርኳስ ክለብ ተመሰረተ

በ1990 ዓ.ም ከደደቢት ፍሬዎች ጋር ታግሎ የትግራይ ብሎም የኢትዮጵያ ነፃነት ለመመለስ የተታገለው ኮለኔል አወል ደደቢት የተባለ የእግርኳስ ክለብ መመስረቱን ተሰማ፡፡የሜዳው ትግል በ11 ታጋዮች ተጀመረ…በ 11 ተጫዋቾችም ደደቢት የእግርኳስ ክለብ ተመሰረተች፡፡ተአምረኛ ቁጥር 11፡፡በ2002/03 ዓ.ም የኢትዮጵያ የሁለተኛ ደረጃ ክለቦች ሻምፔን በመሆን የኢትዮጵያ ፕሪሜር ሊግ መቀላቀሉን እውን ሆነ፡፡ከዛም በየዓመቱ ከፍተኛ ደረጃ እያስመዘገበ መጥቶ ከደደቢት ቦክር ልጆች ግንባር ቀደም እንደሆነ ዓለም የመሰከረለትና የኢትዮጵያ ህዳሴን በመቀየስ በሚታወቀው የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዘይናዊ የተሰየመው … የመለስ ማንጫ በዘንድረው ዓመት አሸነፍ…የ2005 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሜር ሊግ ሻምፔን ሆነ፡፡ህወሓት(ደደቢት ልጅ) በ15 ዓመቷ ትግራይን ከደርግ አገዛዝ ነፃ እንዳወጣቻት ሁሉ ደደቢቶችም በ15 ዓመታቸው የኢትዮጵያ ፕሪሜር ሊግ ሻምፔን ሆኑ!!! ትራንስ ኢትዮጵያና ጉና የእግርኳስ ክለቦች እንደነ ኢህአፓ፣ኢድዩ፣ግንባር ገድሊ ትግራይ ወዘተ ተሸንፋ ከጫወታ ውጪ ሲሆኑ የደደቢት ፍሬዎች ግን ፍፁም ሰላማዊ፣አዝናኝና ዓለም አቀፋዊ በሆነው የእግርኳስ ጨዋታም አሸናፊ መሆናቸውን በድጋሚ አስመሰከሩ፡፡ደደቢት በድጋሚ ታሪክ ሰራች…ሻምፔን ሆነች!!!

በ1992 ዓ.ም የደደቢቶች ድህነትና ኋላ ቀርነት ለማጥፋት የሚደረገው ትግል ሊያኮላሽ የሚችል አደገኛ ክፍፍል ተፈጥሮ ነበር፡፡ነገር ግን ‹‹ወያነና ነዊሕን መሪርን እዩ፤ዓወትና ናይ ግድን እዩ!… አብዮታችን ረዥምና መራራ ነው፤ድላችን ግን የግድ(አይቀርም) ነው›› ብለው የተነሱ የደደቢት ልጆች እንቅፋቱን እንደፍጥነት መጨመርያ ተጠቅመውበታል፡፡በኤሊ እርምጃ ይንቀራፈፍ የነበረው የፈራረሰች ኢትዮጵያን መልሶ የመገንባት ሩጫን እንደማርሽ ማስቀየርያ ነበር የቆጠሩት፡፡ትግሉን ጥለው ለወጡት የድሮ ጓዶቻቸውም ‹‹ዝኻኣለ ይሳለ፤ዘይኻኣለ ድማ ይታአለ…የቻለ ያዝግም ያልቻለ ግን ይወገድ›› የሚል መፈክር እንዲያስታውሱ ነግረዋቿል፡፡
አሁን ደሞ የደደቢት ልጆች ከሌሎች የኢትዮጵያ ፕሪሜርሊግ ክለብ አቻዎቻቸውን ጋር በመሆን ከ31 ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የአፍሪካ ሃገሮች የእግርኳስ ጨዋታ ተሳታፊ እንደትሆን በማስቻል የሃገራችን ባንዴራ በደቡብ አፍሪካ ስታዴሞች እንዲውለበለብ አድርጓል፡፡ዓለም በዋልያዎቹ የእግርኳስ ጥበብና በህብረቀለማት ባሸበረቁ ደጋፊዎቻቸው ስሜት ስሜቱን ተነክቷል፡፡መቼም የማይረሳ አሻራ ትቷል፡፡
ህይ የደደቢት ልጆች ብቃት በአፍሪካ ሃገሮች የሚደረገው የዋንጫ ፉክክር ለማለፍ ብቻ የተገደበ አለመሆኑን ለማስመስከር በበራዚል ለሚዘጋጀው የዓለም የእግርኳስ ውድድር ለማለፍ የሚደረገው ፉክክር በማሸነፍ የአንደኝነት ደረጃው ቢቆናጠጡም ከመናገር ውጭ ምንም የማይችሉ፣ማየት፣መስማትና ስራቸውን መስራት በተሳናቸው የእግርኳስ ፈደሬሽን ሃላፊዎች እንዝህላልነት ምክንያት ሶስት ነጥብ ተቀንሶባቸዋል፡፡ይሁን እንጂ፣ የደደቢት ልጆች የ1992ን መከፋፈል እንደማርሽ ማስቀየሻ እንደተጠቀሙበት ሁሉ አሁንም የማሸነፍ ብቃታቸውን እንደማጎልመሻ ይጠቀሙበታል፡፡ለደደቢት ልጆች የሚሳናቸው ነገር የለምና የማእከላዊ አፍሪካው ክለብ በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ውድድር ያልፋሉ፡፡
ያኔ በደደቢቶች የ17ኛው የምስረታ በዓል ምን እንደሚሰሩ እናያለን…ለአፍሪካሻምፔና ቀንደኛ ተወዳዳሪ ይሆናሉ፡፡በ39ኛው የምስረታ በዓላቸውስ?ምናልባት ያኔ የኢትዮጵያ እግርኳስ ክለብ የአፍሪካ ዋንጫን አሸንፎ…ዓለም ወንጫም ለማሸነፍ ከሚፎካከሩ የዓለም ክለቦች አንደኛው የሆናል፡፡

ትግሉ ይቀጥላል፡፡ደደቢት የኢትዮጵያ ነፃነት፣አንድነት፣እንዲሁም ህዳሴ ፋናወጊ መሆኗንም ይቀጥላል… ገና ብዙ ታረክ ይሰራል፡፡ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች ግንባር ቀደም ትሆናለች…የድሮ ገናና ስሟ በድጋሚ በመላው ዓለም ያስተጋባል፡፡ድህነትና ኋላ ቀርነት ኋላቀር ታሪኮች ይሆናሉ፡፡ያኔ እማማ ኢትዮጵያ የደስታ እምባ ታነባለች…በደስታ ብዛት ስቅስቅ ብላ ታለቅሳለች…ደሞ ልቧ እስኪፈነዳ ድረስ ትስቃለች ‹‹አሀሀሀሀሀሀሀሀ…ሀሀሀሀሀሀሀ…አልልልልል….ሀሀሀሀሀሀ….ሀሀሀሀሀ…ሀሀሀሀ…ሀሀሀ…ሀሀ…ሀ…እልልልል…ልልልል…ልልል…ልል…ል››



                                                   


No comments:

Post a Comment