የከተማ ልጅ በእቅድ ይወለዳል በእቅድ ያድጋል፤ሆስፒታል ውስጥ ተወልዶ፣ልዩ የህፃናት መኝታ ተብጅቶለት፣የእናት ጡት ካነሰበት
ጥጦ ተገዝቶለት እየጠባ፣ተንከርከር እያለ በእግሩ መራመድ ሲጀምርም በአፀደ ሕፃናት እንክብካቤ እየተደረገለት ገና ጨቅላ እያለ የፊደሎችና
የቁጥሮች ስያሜና ቅርፅ በቴሌቪዥን በሚቀርቡ ፊልሞች ጭምር እየተማረ…የእውቀትና የጥበብ ማንነትና መርሖችን እየቀሰመ፣ በየዓመቱ
የልደት ቀኑን እየተከበረለት፣ እደግ ተመንደግ እየተባለ ያድጋል፡፡ከተማ ተወልዶ፣እዛው እየተማረ አድጎ፣እዛው ስራ ይዞ ንሮውን ይመራል፡፡ተወልዶ
ያደገበት ቀየ ለቆ የሚሰደድ ቢኖርም ወደ ገጠር የሚሄድ ግን ያለ አይመስለኝም… ወደ አውሮፓና አሜሪካ ካልተሳካለትም ወደ ዓረቦችና
ሌሎች የአፍሪካ ሃገሮች ቢሄድ ነው፡፡ወደ ገጠር የሚጓዘው ምናልባትም ለጉብኝት ይሆናል፡፡
ውልደቴም እድገቴም በገጠራማው ሰሜን ኢትዮጵያ ነው፡፡እንደ ማንኛውም የገጠር ልጅ በገጠርኛ አስተዳደግ ነበር ያደኩት…
በጋጣሚ ተወለድኩ፤ በጋጣሚም አደኩ፡፡አጋጣሚው ቀጠለና በድግሪ ተመርቄ በስራ ምክንያት ንሮየ አዲስ አበባ እንዲሆን ሆነ፡፡ይሁን
እንጂ፣ ሰው የሚኖረው የድሮውን በትዝታ እያንጉራጎረ የወደፊቱን ደሞ መልካሙን ሁሉ እየተመኘ በተስፋ ነውና እኔም ያደኩበት ቀየና
ማህበረሰብ ትዝ ሲለኝ ጊዜ ናፍቆት ብጤ መላ አካላቴን ይንጠው ጀመር፡፡የኋሊት ብዙ ባሰብኩና በሰላሰልኩ ቁጥር ተወልጄ ወደደኩበት
ሰሜን ኢትዮጵያ በረር በረር ይለኝ ገባ፡፡ወደ ቤተሰብ ስልክ ደወልኩ፡፡ የሰማሁት ድምፅ ግን የናፈቅኩት የቤተሰብ ሰላምታ ሳይሆን
…‹‹ይቅርታ፣መስመሮቹ ሁሉ ለጊዜው ተይዘዋል፤ እባክዎ ትንሽ ቆይተው ይደውሉ፡፡›› የሚል በኮምፒተር የተቀዳ የቴሌ ድምፅ ነበር ፡፡እንደገና ደውልኩ፡፡ አሁንም የቴሌዋ መንቻካ ሴትዮ ጣልቃ ገባችና‹‹ይቅርታ፣መስመሮቹ
ሁሉ ለጊዜው ተይዘዋል፤ እባክዎ ትንሽ ቆይተው
ይደውሉ፡፡››በማለት ተስፋ ልታስቆርጠኝ ሞከረች፡፡ነገርየው ለምጄዋለሁና ተስፋ አልቆረጥኩም፡፡ከብዙ ድግግሞሽ በኋላ ተሳካልኝ፤ ‹‹ጭርር… ጭርር…ጭርር…›› ስልኩ
ተነሳ፡፡ድህንነቴና ድህንነታቸው ተጠያየቅን፤ሞቅ ደመቅ ያለ ሰላምታ ተለዋወጥን፡፡በስልክ የተጀመረው የመረጃ ልውውጥ ወደ ትውልድ
ቀየዬ ይበልጥ ሳበኝና ለመሄድ ቆረጥኩ፡፡ስሆነም ወደ ሰላም ባሶች ስልክ ደውዬ ሳምንት ወደ መቐለ ከሚጓዙ ባሶች ቦታ ይገኝ እንደሆነ
ጠየቁኝ፡፡መልሱ ለማንም ደምበኛ የማይመጥን፣ ልቅነትና ትዕቢት የተላበሰ ነበር…ስልኩን ያነሳው ሰውዬ ‹‹የለም!›› ብሎ ስልኩን
በጆሮየ ድርግም አደረገው፡፡
በሳምንቱ አውቶብስ ተራ ህጄ ትኬት ቆርጬ ተመለስኩ፡፡በነጋታው ሁሉም ተጓዦች ቦታ ቦታቸውን እንደያዙ ጉዞ ተጀመረ… ወደ
ሰሜን ኢትዮጵያ፡፡አዲስ አበባን በጥዋቱ ወደኋላ ትተናት ነጎድን፡፡ከጥዋቱ ሁለት ሰዓት ሲሆን ደበረ ብርሃን አከባቢ ስንደርስ ሹፌሩ
ለአስር ደቂቃ ተናፍሰን እንድንመለስ
ፈቅዶልን ወደ በህርዛፎቹ ውስጥ ገብተን ፊኛዎቻችንን ነፃ አደረግን፡፡ከየጥጋጥጉ እንደተመለስን ሹፌሩ ከአንድ ሁሉም ነገር በጉልበትና
በፍጥነት ለመፍታት የሚፈልግ ተሳፋሪ ጋር በቡጢ ሊቧቆሱ ለገልጋይ ሲያስቸግሩ ደረስን፡፡ተሳፋሪው ከአውቶብስ ተራ ጀምሮ ነበር ከሽፌሩ
ጋር ንትርኩን የተያየዘው፡፡ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ‹‹ንዳው እንጂ!ለማጅ ነህ እንዴ?››ይለዋል፡፡‹‹ሃላፊነት አለብኝ ወንድም! ለተሳፋሪዎች፣ለራሴና
ለአውቶብሱ ድህንነት!›› ይመልሳል ትዕግስተኛው ሹፌር… በትህትና፡፡በመጨረሻ ላይ ያግብዝ ተሳፋሪ ለድብድብ ሲጋበዝ ግን ተሳፋሪው
ሁሉ ቆፎው እንደ ተነካ ንብ ሊወረው ዝግጁ መሆኑን ሲያውቅ ቤተ መቅደስ ውስጥ የገባች ውሻ መሰለ… የሚለው ጠፋበት፤ የሚገባበት
አጣ፡፡ሹፌሩ ትዕግስትና ጥበብ የተሞላበት አነዳድ የአብዛኛው ተሳፋሪ ደጋፍ አገኘ፡፡አውቶብሱን ሜዳ ላይ አንደሚፈስ ጅረት ያንፈላስሰዋል
ሹፌሩ፡፡የሚያስታውከው፣የሚያጥወለውለው ተሳፋሪ አልነበረም፡፡ሰላማዊው ጉዞ ቀጥሏል…
ልክ በአራት ሰዓት
ላይ ደብረሲና ደረስንና በ20 ደቂቃ ውስጥ ቁርሳችን በልተን አንድንመለስ ተስማማን፡፡በየሆቴሎችና ቡናቤቶች መግብያ የቆሙ ሰራተኞች
ተሳፋሪዎችን ያሻማሉ… ‹‹ወደህ ኑ! ምርጥ ቁርስ አለ›› እያሉ፡፡ወደ አንዱ ቁርስ ቤት ገብተን ጥብስ አዝዘን መጠባበቅ ጀመርን፡፡ያዘዙትን
ቁርስ የዘገየባቸው ተስተናጋጆች አኩርፈው ቁርስ ቤቱን ጥለው መውጣት ጅሯል፡፡ትንሽ የታገስን የመጣልን ጥብስ ‹‹ጥብስ›› አልነበረም…
በዩኒቨርሲቲ ከፌዎች የምናውቀው ‹ዜርፎር›› ነበር፡፡በመጠኑ ቀማምሰን ለአንድ ‹‹ዜርፎር›› 35 ብር ተዘርፈን ወጣን፡፡ሰላማዊው
ጉዞ ቀጥሏል…
አውቶብሱና ሹፌሩ ተወራራሽ
የሆኑ ባህሪዎች የተላበሱ ይመስላሉ፡፡ሁለቱም በየጊዜው ቤንዚን ይወስዳሉ… ሹፌሩ ያለጫት የሚሆንለት አይመስለም፤ ረዳቱ ከሹፌሩ አጠገብ
ቁጭ ብሎ ቀንበጥ ቀንበጡን እየመረጠ በመዳፉ ላይ አያሰባሰበ የጎርሷል፡፡ሹፌር እንደፍየል ቅጠል ይበላል፤ያላምጣል፤የመነዥካል፤ያሞሰኳል፡፡እየነዳ
ጫት ያኝካል፤ሆቴል ውስጥም ፈርሾ ጫቱን ይሰለቅጣል…ያለምንም ፋታ፡፡አውቶብሱ በተገኘው ማዳያ ሁሉ ነዳጅ የሞላል፡፡ጋራ ሸንተረሩ፣ዳገት
ቁልቁለቱ፣ቆላና ደጋው፣ሜዳና ተራራው እያቆራረጠ፤እየወጣ እየወረደ ይበራል… አስፓልቱን የሚነካ አይመስልም… ድምፅ ሳያሰማ፤ሳይንገራገጭ
ወደፊት ይነጉዳል፡፡
ስድስት ሰዓት ተኩል
ሽዋ ሮቢት አሪፍ ምሳበልተን፣ ኮምቦልቻና ደሴን አልፈን ለአስራ ሁለት ሩብ ጉዳይ ሃይቅ ደረስን፡፡አንድ አንድ ተሳፋሪዎች ጉዟችን
አንድንቀጥል ተማጠኑ፡፡ሹፌሩና ረዳቱ ግን ፍቃደኞች አልሆኑምና ሃይቅ አደርን፡፡ሃይቅ ወበቃማ ነች፡፡እዛው ሳድር የመጀመርያየ ባይሆሆንም
አየሯን ልለምደው አልቻልኩምና ለሊቱን ሙሉ እንቅልፍ ብሎ ነገር በዓይኔ አልዞረም… ከቢምቢዎችና ከሙቀቱ ጋር ስታገል፡፡ከለሊቱ በአስርሰዓት
ጉዞ ተጀመረ፡፡ወለዬዎችን በሚያሞካሹ ታዋቂ ዘፈኖችና የወፎች ዝማሬዎች ታጅበን በሃይቅ፣ወልድያና ቆቦ መካከል የሚገኙ በከፊል ራቆታቸውን
የተገተሩ ተራሮች አልፈን ሶስት ሰዓት ተኩል አላማጣ ደረስን፡፡እዛው ቁርስ በልተን ከሞኾኒ ወደ ሕዋኔ በሚወስደው አድስ የአስፓልት
መንገድ እየትንፈላሰስን ወደፊት መረሽን...ወደ ሰሜናዊቷ ከኮብ…‹‹ዓይኒ ትግራይ››… መቐለ፡፡
እኔ ሕዋኔ ስደርስ
ወራጅ አልኩኝ፡፡የጉዜ አቅጣጫ በእምባ አላጀና በፅበት ተራሮች መሃከል ወደምትገኘው ዓድ ሽሁ የሚያመራ ስለነበር፡፡እዛው ሕዋኔ ሻንጣየን
በጀርባይን አዝዬ በእግሬ ስዘዋወር የሚከተለው አሮጌ ህንፃ ዓይኔን ሳበውና በሞባይሌ ፎቱ አሳሁት፡፡
ይህ ከላይ የምትመለከቱት
ህንፃ ደርግና ኢህአዴግ የስልጣን ርካብ ከመቆናጠጣቸው በፊት የተሰራ ነው፡፡የህንፃው ባለቤት ደጃዝማች ወልደኪዳን አሸብር ይባላሉ፡፡ከአርባ
ዓመታት በፊት የተገነባ ቢሆንም እስካሁን ደረስ ለእርጅና እጁን አልሰጠም፡፡አሁን ግን በህንፃው ውስጥ ማንም አይኖርም፡፡በየአቅጣጫው
ተተርትሯል፣ምርጊቱ ረግፏል፡፡ዓይኔን የሳበው ግን የህንፃው እርጅና ወይም በደጃዝማች እንቶኔ ስም ስለሚጠራ አይደለም፡፡ከህንፃው ፊት
ለፊት ከጊዜ ብዛት በደበዘዘ ቀይ ቀለም የተፃፉ ሁለት መፈክሮች ይታያሉ፡፡አንደኛው ‹‹ትግራይ ብፅፍርና ክንሃንፃ ኢና!!!›› ይላል…‹‹ትግራይን
በጥፈራችን እንገነባታለን!!!›› ማለት ነው
፡፡ሁለተኛው ደሞ ‹‹ዲሞክራሲያዊ ሕገ መንግስቲ ማሕንቖ ገዛእቲ እዩ!!!›› የሚል ሲሆን
ትርጉሙም ‹‹ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግስት የገዢዎች ማነቆ ነው›› ማለት ነው፡፡
እነዚህ መፈክሮች ማን ፃፋቸው? ለምን?በሚቀጥለው ክፍል
እናየዋለን… እስከዛው ቸር አንሰንበት፡፡



No comments:
Post a Comment