የጉዞየ አቅጣጫ ከሕዋኔ ወደ ዓዲ ሽሁ የሚያመራ ስለነበር ሕዋኔ ወርጄ የደጃዝማች ወልደኪዳን አሸብር ህንፃን ፎቶ አንስቼ ፣በሕንጻው ላይ የተፃፉ ሁለት መፈክሮችም ዘግቤ ነበር… በክፍል አንድ የጉዞ
ማስታወሻየ፡፡መፈክሮቹን ለማስታወስ ያህል አንደኛው፣‹‹ትግራይን በጥፈራችን እንገነባታለን!!!›› የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደሞ ‹‹ዴሞክራሲያዊ
ሕገ መንግስት የገዢዎች ማነቆ ነው›› ይላል፡፡የባለፈው ጥያቄ እነዚህ መፈክሮች መቼ ተፃፉ፣ማን ፃፋቸው፣ ለምን? በማለት ትንሽ እንሻሽለው እና እንቀጥል፡፡
እነዚህ መፈክሮች የተፃፉት
ነፍሰ በላው የደርግ አገዛዝ ከ17 መራራ የትግል ዓመታት በኋላ ከምድረ ትግራይ ተጠራርጎ እንደተባረረ ነበር… በ1980ዎቹ፡፡የደርግ
አገዛዝ የተገረሰሰበት ማግስት ትግራይ ብሎም መላው ኢትዮጵያ በማሕበራዊ፣ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋበሮች የፈርስራሽ ካቦች
ክምር ሆኖው ነበር፡፡ያች የፈራረሰች ብሔርና ሃገር መልሶ ለመገንባት ነበር ታድያ ‹‹ትግራይን በጥፈራችን እንገነባታለን!!!››፣‹‹ዴሞክራሲያዊ
ሕገ መንግስት የገዢዎች ማነቆ ነው›› እና ሌሎች መፈክሮች በመላው ትግራይ ያስተጋቡ የነበረው፡፡
እነዚያ መፈክሮች ከተፃፉ
ብያንስ 20 ዓመታት ተቆጥሯል፡፡ለዛም ነው ቀለማቸው ደብዝዞ የተፃፉበት ህንፃም ሊፈርስ ተቃርቦ የሚታየው፡፡ግን የትግራይ ችግሮች
ተፈቷል? ህዝቡ ከአሳፋሪው የድህነት ማቅ ተላቋል?ያበሞቶ ሽዎች የሚቆጠሩ የምርጥ ልጆቹን ህይወት ገብሮ በትግሉ ያገኘው ድልስ ዴሞክራስያዊ
መብቶቹን አንዲከበሩለት እስችሎታል?ወይስ በድሉ ማግስት ከአፅናፍ አፅናፍ ያስተጋቡ የነበሩ መፈክሮች ቀለማቸው ደብዝዞ ከነመኖራቸው
እንደተረሳው ሁሉ የህዝቡ ዴሞክራስያዊ፣ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችም ተረስተው ይሆን?የሃገራችን መጣኔሃብታዊ እድገት ታድያ
ማን ይሆን አያጣጣማቸው የሚገኘው?ጉዟች ን ይቀጥላል፤ትእዝብታችንም
እንዲሁ እየቀጠለ ነው እና የጥያቄዎቹ መልስ ወደፊት የምናገኘው ይሆናል፡፡
ከሕዋኔ ወደ ዓድ ሽሁ
የተሳፈርንባት አባዱላ መኪና በተሳፋሪዎች ብዛት ከልክ በላይ ተጨናንቃለች፡፡ሰው በሰው ላይ ተጭኗል፡፡ትርፍ መቀመጫ ቀርቶ ተሳፋሪዎች
ንፁኅ አየር የሚተነፍሱበት ክፍተትም አልነበራትም፡፡ከመጠን በላይ ተጠጋግተው የተቀመጡ ተሳፋሪዎች ሳይወዱ በግድ ትንፋሽ ለትንፋሽ
እየተለዋወጡ ለብዙ ዓመታት በጦርነት ታርሰው ተምሰው ጥርሶቻቸው ገጠው፣ፀጉራቸው ተመላልጦ የተቀረውም ሸብቶ በሚታዩት ተራሮች እየተጠማዘዙ
ይወርዳሉ ይወጣሉ፡፡ከቤትመራ ጀምሮ፣አሁን ፈራርሳ እንዳልነበረች በሆነቸው ዓዲጉራ አልፎ፣እምባ አላጀን ወደ ምዕራብ ትቶ ዓድሽሁ
የሚያደርሰው ጠመዝማዛና ተዳፋት መንገድ መጫን ካለባት በላይ በተጫነች አባዱላ መጓዝ ቀርቶ በእግርም ቢሆን በጣም ያስፈራል፡፡በወረዳ
እምባ አላጀ ከተማ ዓድሽኁ ለስም ብቻ ፖሊሶች አሉ… ተራፊክ ፖሊሶች ጭምር፡፡ነገር ግን መኪኖች ያን ያህል ከልክ በላይ ተሳፋሪዎ
ቢጭኑም ሃይ የሚላቸው አልነበረም፡፡ፖሊሶቹ የተቀጠሩት ደሞዝ ለመቀበል እንጂ ህዝብ ለማገልገል መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች በፍፁም
አይታዩም፡፡ከከተማ ውጭ ያለው አደገኛ የአስፓልትና የጠጠር መንገድ ማንም ተቆጣጣሪ የለውም፡፡አሽከርካሪዎች እንዳሻቸው ይጭናሉ፤
እንዳሻቸው ሒሳብ ያስከፍላሉ፡፡
በስንት ፀሎትና ስለት
ዓድሽሆ ደርሰናል፡፡ህሊና ቢስ፣ጥርስ አልባ ፖሊሶች በከተማዋ ውስጥ ሲርመሰመሱ ነበር፡፡ያሁላ ስራ ፈት፣ያሁላ ከርሳም ሙሰኛ የተከበረውን
የፀጥታ አስከባሪዎች መለዮ ለብሰው፣ ቦርጮቻቸውን ታቅፈው በኩራት ይንጎማለላሉ፡፡ከዓድሽሁ ተወልጄ ወዳደግኩባት ደላ(ስለዋ) ለመጓዝ ሚኒ ባስ ተሳርኩኝ፡፡ሚኒ ባሷ በተሳፋሪዎች ብዛት ተጨናንቀው በአዲስ አበባ ጎዳናዎች እንደሚርመሰመሱ የከተማ አውቶብሶች ጢቅ ብላ ሞልታለች፡፡ህፃናት የዘሉ እናቶች፣አቅመ ደካማ ሽማግሌዎችና በሽተኞች ሳይቀር ለመተንፈስ ሲጣጣሩ ማየት አንጀት የሚበላ ነበር፡፡አንድ ትራፊክ ፖሊስ ሚኒ ባሷን አይቶ እንዳላየ፣ አንዲት ቃል ሳይተነፍስ ተቷት ሄደ… የተሳፋሪዎች ድህንነት ለማረጋገጥ ሳይሆን ሚኒ ባሷ ለባለቤቶቿ ትርፍ ማግበስበስ እንድትችል ለመቆጣጠር የተቀጠረ ይመስላል፡፡
በቲኬታችን የተፃፈው
የገንዘብ መጠን 13 ብር ቢሆንም እንደንከፍል የታዘዝነው ግን 20 ብር ነበር፡፡እኔ ለምን ብዬ በመከራከር መብቴን ለማስከበር ብሞክርም
ከሚኒ ባሷ እንድወርድ ነበር የተነገረኝ፡፡ወደ ወረዳው ፖሊስ ጣብያ ለማመልከት በዝግጅት ላይ እያለሁ አንድ አንድ ወገኖች ‹‹ምንም
ለውጥ ለማታመጣበት ጉዳይ ጊዜህን በከንቱ አታጥፋ፡፡አሁን በፊት ብዙ ጊዜ ሞክረን ሊሳካልን ስላልቻለ ነው ሰንወድ በግዳችን አሜን
ብለን ለመቀበል የተገደድነው፡፡በዚህ ወረዳ ገንዘብ እንጂ ሰው ተናግሮ ማሳመን አይችልም፡፡›› የሚል ምክር ሰጡኝ እኔም 20 ብር
ለመክፈል ተገደድኩኝና ጉዞ ተጀመረ፡፡እማይደረስ ነገር የለምና መኪናዋ ዳገት መውጣት ሲያቅታት በእግራችን እየተጓዝን፣በሜዳዎችና
ቁልቁለቶች ደግሞ በፍርሃት ትንፋሻችን ይዘን ፈጣሪያችንን እየለመንን ደላ ደረስን፡፡
ደላ የድሮ ወረዳ ስለዋ
ፅሕፈት ቤት የነበረች የገጠር ከተማ ነች፡፡አብዛኛው የትግራይ ክፍል በደርግ አገዛዝ ስር በነበረበት ጊዜ ስለዋ ከቀደምት የህወሓቶች
ነፃ ግዛት አንዷ ነበረች፡፡የስለዋ ጋራ ሸንተረሮች እንደ ኮብራ መርዝ በሚረጩና ለነፃነታቸው ለመሰየፍ ወደ ኋላ በማይሉ ማሊሻዎች
ይጠበቁ ነበር፡፡ይህን የሚያውቁ ህወሓቶች በስለዋ ተራሮች የስልክ መገናኛ ምሽጎች ነበሯቸው፡፡ይህን የተገነዘቡ 20 የሚሆኑ የታጠቁ
የድርግ ወታደሮች ህጉጦ በሚባል ተራራ ላይ የነበረው የስልክ መገናኛ ለማውደም አሪ የሚባል አከባቢ ሲደርሱ የአከባቢው ማልሻዎችና
አርሶ አደሮች ተሰባስበው በመክበብ ብረት ያለው በብረት፣ብረት የሌለው ደግሞ በድንጋይ፣በገጀራና በዱላ ተረባርበው ለወሬ ነጋሪ ሳያተርፉ
ሁሉንም ገደሏቸው፡፡በዚህ የተነሳ አንድ ዛሬም የማይረሳ ዘፈን ይዘፈን ነበር በመላው ሰለዋታይ፡-
አታሪእሐኹም ዶ አሪ
ዝተገበረ
ንካላሽን ጎጀሞ ስዓረ
ይባል ነበር፡፡
አያችሁ ወይ አሪ የተደረገው
ለክላሽን ገጀራ ያሸነፈው…
ለማለት ነው፡፡
በዚህ ያቄሙ የደርግ
ወታደሮች ስለዋን ለማንበርከክ ብዙ ዘመቻዎች ቢያደርጉም አንዴም ተሳክቶላቸው አያውቅም፡፡እንደውም የኋላ ኋላ ህወሓቶች የዘመቻ ማእከል
ለመሆን በቅታ ነበር ስለዋ፡፡
ያሁሉ የስለዋ ህዝብ ውለታ ዛሬ የተረሳ ይመስላል፡፡ስለዋ ከነፃነት በኋላ ወረዳነቷ
ተሰርዞ በእምባ አላጀ ጥቀኝነት እንደትተዳደር ተፈረደባት፡፡ማሕበር ልምዓት ትግራይ እና የስለዋ ተወላጆች አለንልሽ ብለው የቅድመ
መሰናዶ(ፕሪፓራቶሪ ስኩል) ባያስገነቡላት ንሮ ልጆቿ 35 ኪሎ ሜትሮችን እያቆራረጡ፣ ስንቅ ቋጥረው፣ቤት ተከራይተው ለመማር ይገደዱ
ነበር…በዓድሽሁ ከተማ፡፡
የውሃ ችግር
ድሮ የስለዋ ከተማዋ
ደላ የውሃ ማማ ነበረች፡፡የስለዋ ሰብሎች በውሃ ብዛት እንጂ በድርቅ ተመትተው አያውቁም ነበር፡፡አሁን ግን በደላ ከተማ” የሚጠጣ
ውሃ ጠፍቶ ኗሪዎች በሰልፍ ለመጠጣት ተገድደዋል፡፡በለፈው ጉዞየ የታዘብኩት በጣም የሚያሳዝን ነበር፡፡በአንዱ በእጅ ፓምፕ የሚሰራ
የውሃ ጉድጓድ 150 ጄሪ ካኖች ተሰልፈው ለመቁጠር ችያለሁ፡፡ማዳበርያ ለማልማት ወይስ ለማውደም?
በየቀበሌዎቹ የተሾሙ
የህወሓት ባለስልጣናት ከልክ በላይ አምባገነኖች ሆኖዋል፡፡የህዝቡ እሮሮ ሰምተው መፍትሔ ለመሻት ሳይሆን ከላይ የሚወርዱ መመርያወችን
ሳያቅማሙ ተቀብለው በህዝቡ ላይ ለመጫን የተቀመጡ ናቸው፡፡በአሁኑ ጊዜ እጅግ አንገብጋቢው ጉዳይ መዳበርያ ነው፡፡ማንኛውም ኗሪ የዩርያና
ዳፕ ማዳበርያዎች ከመንግስት ካልገዛ በስተቀር መኖር አይችልም፡፡
ማዳበርያ ሻጮችና የሽያጩ
ብር ሰብሳቢዎች የሚተዋወቁ አይደሉም፡፡አንድ አርሶ አደር አምና እና ካች አምና ወዶ ለመክፈል ከአቅሙ በላይ የሆነ የማዳበርያ እዳ
እያለው ዘንድሮም የግድ እንዲወስድ ይገደዳል፡፡አልወስድም ካለ ይታሰራል…በቀውጢ ጊዜ…የዓመት ቀለቡን ዘርቶ ለማፍራት ላይታች በሚልበት
ጊዜ፡፡በደለቡ ቁንጫና ቱሐኖች በተሞላችው እስር ቤት ተስሮ አላሳመናችሁኝም፤እዳ እያለኝ ሌላ እዳ መውሰድ አልችልም ብሎ አምቢ ያለው
አርሶ አደር፣ ‹‹አንግድያውስ መንግስት የሰጠህ ማሳ ፈርመህ አስረክበን፡፡ማዳበርያ ወስደው ለሚያለሙ አርሶ አደሮች እንሰጠዋለን
ይባልል፡፡›› ምስኪን አርሶ አደር ሆዬ ምን ምርጫ ይሆረዋል?የልጆቹና የትዳሩ መሰረት የሆነችው የበሬ ግንባር የምታህል መሬት ከተወደችበት
ከሃገር መነቀሉ ነውና ሳይወድ በግድ በእዳ ላይ እዳ እንዲቀበል ይገደዳል፡፡
ያሁሉ ከላይ ከላይ
የተደራረበው የእዳ ክምር እንዴት ሊከፍል ይችላል? የእርሻ ማሳው አፈራች ከተባለ ለዓመት ምግብ ቀርቶ ለማዳበርያው ወጭም አትሸፍንም፡፡ሰለሆነም
ለዓመታት ታግሎ ያረባቸው የቤት እንስሶቹን ሸጦ እንዲከፍል ይደረጋል፡፡ያኔ ‹‹ድሀ››፣‹‹መናጢ››፣‹‹ድንባው››፣‹‹በተኽ›› የሚባሉ
ታርጋዎች ተለጥፎበት ለማያደን እና ለማይገድል እርዳታ ጠባቂ ሆኖ ይቀራል፡፡
እርዳታ እንደ ወጥመድ
አሁን አርሶ አደሩ
የቀበሌ ሹሞኞች መፈኘጫ ከመሆን ውጪ ሌላ አማራጭ አይኖረውም፡፡እርዳታ እንደንሰጥህ ይህን አድርግ፤ ያንን አድርግ እየተባለ የሪፖርት
ሟሟያ ይሆናል፡፡የዚህን ያህል አርሶ አደሮች ህይወት በምግብ ዋስትና ፕሮግራም ራሳቸው እንዲችሉ አድርገናል ወዘተ. የሚሉ ሪፖርቶች
ወደ ከፍተኛ ባለስልጣኖች ይላካሉ፡፡ሪፖርት አድራጊዎች ‹‹ሞዴል›› ባለስልጣን በመባል ይሸለማሉ፤ሌላ ከፍ ያለ ሹመት ይሰጣቸዋል፡፡ያኔ‹‹ትግራይን
በጥፈራችን እንገነባታለን!!!› እና ‹‹ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግስት የገዢዎች ማነቆ ነው›› የመሳሰሉ መፈክሮች ሊፈርስ በተቃረበ
የደጃዝማች ወልደኪዳን ህንፃ እንደተረሱ ሁሉ አርሶ አደሮችም ይረሳሉ፡፡
ሙስና እና ስርዓት አልበኝነት
ድሮ ሂስና ግለ ሂስ
እየተባለ በየጊዜው የእርሰበርስ መገማገም ስለነበረ ስርዓት አልበኝነት ያአሁኑ ያህል ጥርሶቹ ያገጠጠ፣ዓኖቹ ያፈጠጠ አልነበረም፡፡ያ
አሁን ቀርቷል፤ታሪክ ሆኗል፡፡‹‹ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግስት የገዢዎች ማነቆ ነው›› እንደተባለው በስለዋ ዴሞክራስያዊ ሕገ መንግስት
በፅሑፍ ብቻ እንዲታወቅ ተፈርዶበታል፡፡በተግባር ከተሸረፈ የሙሰኞች የሃብት ምንጭ ይደርቃልና፡፡በአሁኑ ጊዜ የአከባቢው ባለሃብቶች
የመንግስት ባለስልጣናትና ነጋዴዎች ብቻ ናቸው፡፡ባለስልጣናት መንግስት በሰጣቸው ስልጣን ተጠቅመው ነጋዴዎችን በማወናበድ ያልተገባ
ሃብት ያገበሰብሳሉ፡፡ጉቦ እና ‹‹ኪራይ መሰብሰብ›› ሁነኛ መሳርያዎቻቸው ሆኗል፡፡ነጋዴዎች ደሞ ባለስልጣናትን በጉርሻዎች በመደለል
የህዝቡ ሃብት በሕገ ወጥ መንገድ ይዘርፋሉ፡፡
ገንዘብ ያለው ሁሉም
ነገር አለው፤ቢናገር ሰሚ አያጣም፡፡ ባለስልጣኖችን መግዛት ይችላልና ስልጣን እና ሃብት በእጁ ናቸው፡፡በፈለገው ጊዜ የፈለገው ማድረግ
ይችላል፡፡አሁን‹‹ትግራይን በጥፈራችን እንገነባታለን!!!›የሚለው መፈክር ማን እንደፃፈው ሊገባን ይችላል፡፡




No comments:
Post a Comment