Monday, December 16, 2013

ዙረት በአዲስ አበባ




ብዙ ነገሮች ያዞሩኛል፡፡የእንጀራ ነገር ያዞረኛል፤ ተከራይቼ ከምኖርበት ቤት ወደ ስራ፣ ከስራ ወደ ቤት - ከሰኞ እስከ ዓርብ ጧትና ማታ - ሁሌም፡፡ሰው ሁኜ የመፈጠሬን ነገር ያዞረኛል፤ በሐሳብ ማዕበል ስሰምጥ፣ የሆነ ነገር እየከነከነ አላስቀምጥ አላስተኛ ሲለኝ እዞራለሁ፡፡በአጠቃላይ ንሮ እንደ እንዝርት ተሾረኛለች፡፡እንድያ ስታሾረኝ ታድያ ስለ ብዙ ነገሮች እንዳስብና እንድታዘብ ታደርገኛለች፡፡

ያዙረት፣ የሃሳብ ጡዘት፣ በዘመንኛ አነጋገር ዙረት አይባልም፤ የእርድና ስሙ፣ የእግር ጉዞ(walk) ሲሆን በጣም ከሚያዝናኑኝ ነገሮች አንዱ ነው፡፡የእግር ጉዞ በጣም አዝናኝ መሆኑን ያወቅኩት፣ ድሮ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ነበር፡፡ያኔ በጣም አስቸጋሪ ጨጓራ ነበረብኝ፡፡የጨጓራ ነገር የማያውቅ ያለ አይመስለኝም፤ ከመጠን በላይ አናዳጅ ለሆነ ሰው ጨጓራ ብሎ መስደብ የተለመደ ነው፡፡ የጨጓራ በሽተኛ መሆን ግሞ አይጣል ነው፤ ከበላህ ያቃጥልሃል፤ ካልበላህም ይቃጥልሃል፡፡ምን ታደርጋለህ? የት ትሄዳለህ? በቃ! እንደ ሻማ መቃጠል ነው፤ መቅለጥ ነው፡፡ ልዩነቱ ስትቃጠል ብርሃን አትሰጥም፤ እንደውም ፊትህ ይጠቀረሻል፤ለተመልካች ተስጠላለህ፡፡

እናም እማርበት ከነበረው ትምህርት ቤት(ቃላሚኖ) ግቢ ወጥቼ አንዴ ወደ ታች እወርዳለሁ፤ እስከ ሚካኤል ፀላሞ ድረስ፡፡በሌላ ጊዜ ደግሞ እስከ ስላሴ ጨለቆት ድረስ እጓዛለሁ፡፡ወደ አይናለም ህጄም ከቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲምረኝ እለማመጣለሁ፤ በጣም ሲከፋኝም ምሬቴን ሁሉ እዘከዝክለታለሁ፡፡አንዳንዴም እዝትበታለሁ፡፡

እንዲሁ ስዞር የተለያዩ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጦች፣ በአከባቢው የሚኖሩ ሰዎች፣የቤት እንስሳት ወዘተ እያየሁ ሳላስበው ስቃዩ እረሳዋለሁ፡፡ያ ድሮ ያሳለፍኩት የገጠር ንሮየ ያሳታውሰኛል፤ልጅነት፣እረኝነት፣መቆፈር፣ማረስ፣መዝራት፣ ማረም፣ማጨድ፣መሰብሰብ፣መውቃት፣ እህል በአህዮች እየጫኑ ወደ ቤት ማድረስ፣ በሸርፋ ውስጥ መክተት… እንድያ እንድያ እያሉ ማደግ ትምህርት መጀመር…ያኔ የጥላሁን ገሰሰ ‹‹ትዝ አለኝ የጥንቱን›› በእዝነ ልቦናህ ታዳምጣለህ፡፡

ግቢ ስመለስ ደግሞ በድካም ውልቅልቄ ስለሚወጣ አሪፍ እንቅልፍ ይዞኝ እብስ ይላል፡፡ከእንቅልፌ ስነቃ ድካሙ፣ ስቃዩ፣ ሐሳቡ፣ ጭንቀቱ - ሁሉም ነገር ድራሹ የጠፋል፡፡ያች ቅፅበት ምንያህል እንደምታስደስተኝ ልነግርህ አልችልም፤ እፍፍፍይ!!! እላለሁ፡፡ነገር ግን ረሃብ ያጣድፈኛል፤ ምን ልብላ? ሌላ ሃሳብ ነው፤ ሌላ ጭንቀት ነው፡፡ያገኘኸው እንዳትበላ ጨጓራው አለ፣ ያሻህን ለመብላት ደግሞ ብሩ ኬት ይምጣ?መኖር ዕዳ ነው፡፡ስፈራ ስቸር ያገኘሁትን ቀማምሼ የሚመጣውን እጠብቃለሁ፤ለሌላ ጉዞም እዘጋጃለሁ፡፡ወዴት?...

መኪና ቢኖርህም ባይኖርህም የሃሳብ መኪና እያሸከረከሩ በRascal Flat ዘፈን‹‹lifeis a highway››እየተከዙ መመረሽ ነው…
                  Whooo ummmm yeah…
                  Life’s like a road that you travel on
                  When there’s one day here
                                  the next day gone
                     Sometimes you bend,
                     Sometimes you stand
                     Sometimes you turn
                       You are back to the wind
There’s a world outside
Ev’ry darkened door
Where the blues won’t
Haunt you anymore…

በመሆኑም ያኔ የተጠናወተኝ የእግር ጉዞ ዛሬም ድረስ ሱስ ሆኖብኝ እያዞረኝ ይገኛል እልሃለሁ፡፡ስዞር መነሻና መድረሻ አልመርጥም፤ ብቻ ከተነሳሁ እንነሳ እግሬን በመራኝ አቅጣጫ እጓዛለሁ - እስኪደክመኝ ድረስ፡፡በዚህ መሃል ብዙ ነገሮችን እታዘባለሁ፤አንዱን እያነሳሁ ሌላው እየጣልኩ በሃሳብ እነጉዳለሁ፡፡‹‹እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል›› ይባል የለ?ካንዱ ቦታ ወደ ሌላው በዞርኩ ቁጥር ብዙ ነገሮች ያጋጥሙኛል፡፡

አዲስ አበባ ደግሞ የብዙ፣ እጅግ በጣም ብዙ ነገሮች ባለ ፀጋነች(ለጊዜው ፀጋ ልበለው)፡፡እሚበላው፣እሚጠጣው፣እሚለብሰውና እሚኖርበት አጥቶ በየጎዳናው ከሚኖረው በቁሙ የሞተ ምስኪን ወገኔ እስከ ከሚፈልገው በላይ የናጠጠው ቱጃር በመዲናዋ እኩል ይርመሰመሳሉ፡፡አንዱ ከመጠን በላይ ከመብላቱና ከመጠጣቱ የተነሳ ቁመናውና ጤናው ተበላሽቷል፤ ሆድና ጀርባው፣ግራና ቀኙ፣ እጅና እግሩ፣ ሽንጥና ዳሌው የማይታወቅ አሻንጉሊት ሆኗል፡፡ሌላው ለመኖር መሰረታዊ የሆኑ ነገሮች ሊማሉለት ስላልቻሉ ቁመናውና ጤናው ተቃውሷል፤ ከወሎ ረሃብ አምልጦ ብእግሩ እየተጎተተ አዲስ አበባ ከደረሰ በኋላ ጉልቡቱ ከድቶት ዧ ብሎ የወደቀ ይመስላል፡፡ለምን? ትጠይቃለህ፡፡መልስ የለም…

ህፃናት፣ወጣቶች፣ በጣም የሚያማምሩ ሴቶች(የአዲስ አራዶች ችኮች ይሏቸዋል) አያለሁ፡፡እሸትና ፅጌ ረዳ አበባን ያስታውሱኛል፤ እኔም አልፋለሁ እነሱም ያልፋሉ፡፡ይረግፋሉ፣ይገረጣሉ፣ እንረግፋለን፡፡እናም በአበባው፣ በፅጌ ረዳው ጊዜያዊ ገፅታቸው የገረጣው፣የተጨማደደው፣ የተሸበሸበው ፊታቸው፣ የሚንቋቋ፣ አጥንታምና ጎባጣ ቁመናቸው ይታየኛል፡፡እነሱም ይልፋሉ፣ እኔም አልፋለሁ፤ እናልፋለን፣እንተላለፋለን፡፡

ወጣቶቹ እንደ አዳዲሶቹ ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች ቀና፣ዘና፣ኮራ ይላሉ፡፡ረዣዥሞቹ  ህንፃዎች መስታወት በመስታወት ሁነው፣በተለያዩ ህብረ ቀለማት አሸብርቀው ከሩቅ እንደሚያብረቀርቁት ሁሉ እነዚያ ወጣቶችም በተለያዩ ዘመን አመጣሽ ልብሶች፣የከንፈርና የጥፍር ቀለሞች፣የፊት ማሷብያና ማሳመርያ ቅባቶች ወዘተ ያብለጨልጫሉ፡፡ነገር ግን ቀለሙ ይደበዝዛል፤ መስታወቱ ይረግፋል(ጊዜው ሲደርስ ይንኮታኮታል፣ እምሽክሽክ ይላል)፡፡የተፈጥሮ ነገር ይገርማ፣ያሳዝና፣ያስደንቃል…

ይህን ለመታዘብ የትም መሄድ አያስፈልግህም፤ መጓዝ ነው፡፡ያችን የመሰለች ትርንጎ ስታልፍ ትናንት በወጣትነት ያለፉ፣ ወጣትነት… እሸትነት…ፅጌ ረዳነት… መልከ መልካምነት ገንዘባቸው የነበረ የማይመስሉ የገረጡ፣የጎበጡ ሽማግሌዎች ታገኛለህ፡፡ጣርያቸው ላይ ያለው ቆርቆሮ ትናንት እንደ በረዶ ንጭ እንዳልነበረ፣የፀሐይ ጨረር ሲያርፍበት ያብረቀርቅ፣ያንፀባርቅ እንዳልነበር አሁን ከሩቅ ስታየው በእሳት የተቃጠለ ጫካ መስሎልሃል፡፡ቤቶቹን ጠጋ ብለህ ተመልከታቸው ትናንት በተለያዩ ህብረ ቀለማት እንዳላጌጡ ዛሬ ምርጊታቸው ረገፏል፡፡አልፎ አልፎም የግድግዳው እንጨት ይታያል፤አንድ እግሩ ጅብ በልቶት እጥንቱ የሚታይ አህያ ይመስላል፡፡
                

‹‹እናቴ ስትወልደኝ መቼ አማከረችኝ
የፊት ጉዴን ትታ እደግ እማማ አለችኝ
ሳቅኩኝ በልጅነት አለቀስኩ አድጌ
የትላንቱ ወጣት ዛሬ ሽማግሌ…››


በአዲስ አበባ እልፍ ስትል እልፍ ይታያል፡፡አንዳንዶቹ አከባቢዎች ከቆሼ ሰፈር በላይ ይቆሽሻሉ፤በዛው ስታልፍ አፍንጫ የሚቆርጥ ቅርናት ያውድሃል፡፡ቆሻሻ ፈሳሽ የሚደፋበት ትቦ አፉን ከፍቶ ይጠብቅሃል፡፡ እናም እንደ ሰካራም፣አጫሽና ቃሚ የግማቶች ዓይነት ሁሉ ግማት ያገሳብሃል፡፡ሰገራ፣ሽንት፣የአትክልትና የሌሎች ምግቦች ተረፍ መረፍ እዚህም እዝያም ተዝረክርኮ ያጋጥምሃል፡፡ያ አከባቢ ስታልፍ ጊዜው የዓመት ያህል ይረዝምብሃል፤መንገዱም ይርቅብሃል፡፡

ይሁን እንጂ ተስፋ ልትቆርጥ አይገባም፤ አሁንም መጓዝ ይሻልሃል፡፡ምኑን አየህ እና? ያ ለአይን የሚቀፍ፣የሆድ እቃህን እየናጠ የሚያቅለሸልሽ ጥምባት ስትመለከት ቆይተህ በአትክልት ወደ አሸበረቀው ንፁህ ስፍራ መደረስህ አይቀርም፡፡ያኔ ከሲኦል ወደ ገነት እንደ መዘዋወር ያህል መንፈስህ ይታደሳል፤መላው የስሜት ህዋሳትህን ያነቃቃል፡፡በመጨረሻም ለካስ ይህም ንሯል? ትላለህ፡፡ ብዙ ነገሮች ትረሳና ሌላ ድሮ የረሳኸውን ታስታውሳለህ፤ የማታውቀውን ታውቃለህ… አንተ ልትቀጥልም ላትቀጥልም ትችላለህ፤ህወይት ግን በዚህ መልኩ ትቀጥላለች፤ላትቀጥልም ይሆናል፡፡


በሃሳብም በእውንም ለሚጓዝ ሰው ሙዚቃ ማሽ ማስቀየርያ
መሳርያ ነው፡፡ሙዚቃው ከፍና ዝቅ፣ሄድና መለስ፣ፈጠና ቀስ ሲል የሃሳብ መጎዱም እንዲሁ ይቀያየራል፡፡ እንግዲህ የዙረት ሱስ እግሮቼም ናላየም ያዞረብኝ መንገደኛ ንኝና ሃመልማል አባተ‹‹የማይከተሉኝ የሃሰብ ተጓዥ  የሩቅ መንገደኛ 
ተው ሲሉኝ የማልተው የሃሳብ መጎደኛ…››እያለች የምትዘፍነውን ዘፈን
ምንያህል ዙረታም መሆኔን ያስረዳልኝ ዘንድ ጋብዤሃለሁ፡፡
 

No comments:

Post a Comment