Saturday, March 15, 2014

‹‹ቴሌፎን ተቋረጠ ተብሎ ኢንዱስትሪዎች አይቋረጡም፤›› ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል



በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ እና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ያደረጉት ቃለ መጠይቅ በሆርን አፌርስ ድረ ገፅ አነበብኩ፡፡ ሚኒስትሩን በጥያቄዎች ያፋጠጣቸው ጋዜጠኛ አሸናፊ ቱፋ በመንግስታዊ ድርጅት ተቀጥሮ የሚሰራ ‹‹ልማታዊ ጋዜጠኛ›› አይመስልም፡፡

ምናልባትም ሚኒስትርን የሚክል ከፍተኛ ባለስልጣን ጠጠር ባሉ ጥያቄዎች ያጣደፈ የሚጀመርያው ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ሳይሆን አይቀርም፡፡ሚኒስትሩ ‹‹ሁሉም ነገር አማን ነው›› ባይ ሲሆኑ ጋዜጠኛው ግን ሃገር ያወቃቸው ፀሐይ ያሞቃቸው አንገብጋቢ የህዝብ ሮሮዎችን እንደ ወረደ ቁጭ ሲያደርግላቸው ቆጣ ቆጣ(ሃይለ ቃል የተላበሱ መልሶችን ሰጥቷል) ማለታቸው አልቀረም፡፡ለምሳሌ የሚከተሉት ጥያቄና መልስ እንይ፡፡

አሸናፊ ቱፋ፡- በመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ የሚሳተፉ ኮንትራክተሮች ምርጫ ግልጽነት ይጎድለዋል። 
ዶክተር ደብረጽዮን፡- በየመንገዱ የሚወራውን ከመያዝ የመንግሥት አሠራር ምን ዓይነት ነው? ማለት ያስፈልጋል።

አሸናፊ እየጠየቀ ያለው የመንግስት ባለስልጣንን ነው፤ ራሳቸው ሚኒስትሩን፡፡የጠየቀውም የምንግስት አሰራር ግልፅ አለመሆኑን ነው፡፡ሚኒስትሩ ግን ‹‹በየመንገዱ የሚወራውን ከመያዝ›› ብለውት እርፍ፡፡አማርኛ አይገባቸውም ልበል?ጋዜጠኛው እኮ ሰዎች በምግስት ግልፅነት የጎደለው አሰራር ምንክንያት በየመንገዱ ሲማረሩ ታዝቦ ነው የጠየቃቸው፡፡

መቼ ይሆን የሃገራችን መሪዎች ከመናገር ይልቅ ማዳመጥ የሚያስቀድሙት?መቼ ይሆን ሃይለ ቃል በተለበሰ አነጋገር ዝም ጭጭ ለማሰኘት ሳይሆን የህዝብ ችግር ለመፍታት በማሰብ በጥሞና አዳምጠው ነገርችን ለመረዳት የሚሞክሩት?እውነቱን መናገር ማንን ገደለ?የመንግስት ባለስልጣናት ለምን ይሆን እውነትን እንደ ጦር የሚፈሯት?

እስኪ በሞቴ በሃገራችን ህዝብ የማይማረርባቸው የመንግስት አገልግሎቶች ካሉ ጥቀሱልኝ፡፡ቴሌ ነው? መብራት ሃይል ነው? የተጓዥ ህዝብና የመጓጓዣ አለመመጣጠን ነው? የንሮ ውደነት ነው? የህዝቡ የመኖርያ እጦት ነው? ለአስርት ዓመታት የዘለው የውሃ ችግር ነው?

መንግስት አፉን መልቶ በሃገራችን እጥረት የለም ማለት የሚችለው የፀሓይ፣ የንፋስ፣የብርድ፣ የሙቀት፣የውርጭ፣ የህዝብ፣ የፍትሕ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የሙስና፣ የውጭ ምንዛሪ፣ የትምህርትና የህክምና  ወዘተ ብቻ ነው፡፡በስተቀረ ግን በየትኛውም የምንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋሞች ችግር አለ፡፡እጥረት አለ፡፡የህዝብ ዋይታና ሮሮ አለ…በየትኛውም ዘርፍ፡፡

ሚኒስትሮቻችን ግን አንዱን ክደው ሌላኛውን መኖሩን ለማሳመን ይሞክራሉ፡፡ችግር አለበት ብለው የሚያምኑበትም እንዳሻቸው እንዲለማመዱበት እንጂ ችግሩን ለመቅረፍ የሚወጣው ወጪ ያህል ውጤት ለማምጣት አይደለም፡፡ለምሳሌ ቴሌን መውሰድ ይቻላል፡፡

ከስድስት ዓመታት በፊት የቴሌ መሰረታዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ታስቦ ስር ነቀል ለውጥ የተባለለት አሰራር ይሳካ ዘንድ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ወጣበት… TPO (Transformation program office) ከሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት ከፍ ብሎ የሚገኘው የቴሌ ቢሮ የህኛው ለውጥ ለማሳካት የተመረጡ ሰራተኞች ከአሜሪካውያን ልዩ ምክር እየተሰጣቸው የሚሰሩበት ቢሮ ነበር፡፡ሌላው የቴሌ ሰራተኛ ወደዛው ብቅ እንዲል አይፈቀድለትም ነበር፡፡ነገር ግን ከትርፉ ኪሳራው ከመጠን በላይ በመሆኑ ፕሮግራሙ የታሰበው ውጤት ሳያመጣ ተቋረጠ፡፡ወይም ምን እንደበላው አልታወቀም፡፡

ሌላው ቴሌን ሙሉ ለሙሉ ለመቀየር ታልሞ የተቀረፀው አስራር ነበር፡፡ወደ አምስት ሺህ የሚጠጉ አንጋፋ ሰራተኞች ተባረሩ፡፡ቴሌ በፈረንሳዮች የዕድሜ ባለፀጎች(ጥሮተኞች) እንዲተዳደር ተደረገ፡፡ ከወርሃዊ ደሞዛቸው በተጨማሪም 30 ሚሊዮን ዩሮ ተከፈላቸው፡፡ለውጡ ግን የቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን በኢትዮ ቴሌኮም የመቀየር ሆኖ እርፍ፡፡
ምክንያቱም የፈረንሳዮቹ ጥናት ያረጋገጠው የኢትዮጵያ ህዝብ ‹‹የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን›› ብሎ ለመጥራት መቸገሩን ነበር፡፡ በተለይም በእንግሊዘኛው ሲፃፍ የፈረንሳዮቹ ጥናት መሰረታዊ ለውጥ አምጥቷል፡፡ኋላ ቀሩ መስርያ ቤት Ethiopian Telecommunications Corporation (ETC) ነበር፡፡ አዲሱ የፈረንሳዮች ግኝትና ከ30 ሚልዮን ዩሮ በላይ የወጣበት ግን Ethio Telecom(ET) ሆኗል፡፡ከዚህ የዘለለ ለውጥ አለ የሚል ካለ ለመስማት ዝግጁ ነኝ፡፡


አሁን ደግሞ በሶስተኛው የቴሌ ስር ነቀል ለውጥ ላይ ነን፤ TEP( Telecom Expansion Project) ይሉታል፡፡የዚሁ ፕሮጀክት ዓላማና ግብ በወረንጦ ተለቅመው ከተሰበሰቡ ‹‹ታማኞች›› በስተቀር ለሌላው ሰራተኛ እንቆቁል   ሽ ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡ያው ወሬው ግን ውሎ አድሮ ‹‹ከታማኞቹ›› መስማታችን አልቀረም፡፡የቀረብን ነገር ቢኖር ‹‹ታማኝ›› የሚሉት ታፔላ ያልተለጠፈብን መሆኑን ብቻ ነው፡፡

አሁን ክቡር ሚኒስትሩ ስለቴሌ በአዲስ ዘመን ጋዜጠኛው ተጠይቀው የሰጧቸው መልሶችን እንመልከት፡፡
አሸናፊ ቱፋ፡- ኢትዮ ቴሌኮም አሁን ካለው የአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ተቋሙ ባለመሸጡ ከምታገኘው ጥቅም ይልቅ ያጣችው በጣም ይበልጣል ይባላል፤ እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ዶክተር ደብረጽዮን፡- በቴሌ ላይ ያለው የመንግሥት አቋም የሚታወቅ ነው። አገልግሎት አሰጣጡ ካለመሸጡ ጋር አይያያዝም። ለግሉ ዘርፍ ስላልተሸጠ «አገልግሎቱ እንደዚህ ሆኗል» የሚለው አይሠራም። ይሄ እንደዚህ የሆነው መሠረተ ልማቱ በዕድገት ላይ ያለ ኩባንያ በመሆኑ ነው …

የቴሌ ችግር በጣም አስከፊና ረዥም ነው አይደል?የሚኒስትሩ መልስም ረዥም ነው፡፡ቀሪዉን ለማንበብ ድረ ገጹን ይጎብኙት፡፡እሺ ቴሌስ አይሸጥ… የህዝቡ ስቃይ መጨረሻው መቼ ነው? ህዝቡ እየተሰቃየ ያለው እኮ በቴሌ መሸጥና አለመሸጥ አይደለም… ቴሌ ከሚያደርስበት ስቃይ ነፃ የሚወጣበት አማራጭ ማጣቱን ነው፡፡

የባንኪው እንዳስትሪም ልክ እንደ ቴሌ በንግድ ባንክ ፈላጭ ቆራጭነት ስር እያለ ህዝቡ አቋራጭ በሌለው ስቃይና መከራ ውስጥ ነበር፡፡አማራጭ የግል ባንኮች ተከፈቱ፡፡ህዝቡ እፎይ! ብሎ ንግድ ባንክን ደና ሁን ብሎ ፊቱን ሲያዞር ንግድባንክ ወደ ልመና ነበር የዞረው፤ በሽልማት መልክ በሰፊው በማስተዋወቅ፡፡ለዛም የሚሰጠው አገልግሎት ከግል ባንኮች በላይ ደንበኞችን የሚያረካ በማድረግ፡፡

ተሌም እንደ ንግድ ባንክ ለግል ባለሃብቶች ሊፈቀድ ይገባል፡፡ህዝቡ የአማራጭ ንፋስ ለመተንፈስ ይፈቀድለት፡፡ኢህአዴግ እስከ መቼ ነው 99.6 ከመቶ ለመረጠው ህዝብ የአማራጭ ንፋስ በመንፈግ የሚያፍነው? ይህ መንግስት እስከ መቼ ነው ‹‹በእኔ አውቅልሃለሁ›› ይትብሃሉ የህዝብን ትንፋሽ የሚያፍነው?
ሚኒስትሩ ምን ይላሉ መሰላችሁ ‹‹ዘመኑ ረቅቋል፤ ብዙኃኑ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ነው። ቴሌፎን ተቋረጠ ተብሎ ኢንዱስትሪዎች አይቋረጡም፤ መብራት ሲጠፋ ግን ኢንዱስትሪዎች ይቆማሉ። ኤሌክትሪክ ሲቋረጥ ‹እንጀራ አልጋገርንም፣ ምግብም አላበሰልንም› የሚሉ ቅሬታዎች ናቸው የሚመጡት።›› ለፅሑፌ እንደ ርእስ የተጠቀምኩባት አርፍተ ነገር ከዚሁ አንቀፅ ነበር የወሰደኳት፡፡

የእኛ ነገር እዩልኝ እንግዲህ፡፡በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ እና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር(የሚኒስትሩ መዓርግ የአፄ ሃይለስላሴ ሙሉ መጠርያን የሚበልጥ መዓርግ በ21ኛው ክፈለ ዘመን… ሞ አንበሳ ዘእም ነገደ ይሁዳ፣ቀደማዊ ሃይለስላሴ፣ ንጉሰ ንገስት ዘ ኢትዮጵያ)፡፡ ይህን ያህል መዓርግ ተሸክሞ የቴሌፎን መቋረጥ የኢንዱስትሪዎችን መቋረጥ እንደሚያስከትል አለማወቅ ያሳፍራል፡፡

ሚኒስትሩ እኮ ቃል በቃል ‹‹ቴሌፎን ተቋረጠ ተብሎ ኢንዱስትሪዎች አይቋረጡም፤ መብራት ሲጠፋ ግን ኢንዱስትሪዎች ይቆማሉ።›› ነው ያሉት፡፡ቴሌፎን ተቋረጠ ማለት ምን ማለት ነው? ኔትወርክ የለም ማለት ነው፡፡ኔትወርክ የለም ማለት ደግሞ የባንክ አገልግሎት ተቋረጠ ማለት ነው፡፡‹‹ሲስተም የለም›› የሚሉት አባዜን ልብ በሉልኝ፡፡ለሚኒስትሮችችን ግን (ለዛም መዓርጋቸው በጣም ከመርዘሙ የተነሳ ያለማስታወሻ ለመጥራት የሚያስቸግር) የባንኪው እንዳስትሪ ሲቋረጥ የኢንዳስትሪ መቋረጥ አይደለም፡፡

ኢንዳስትሪዎች በትክክል እንዲሰሩ የማይቆራረጥ የመብራት አገልግሎት የሚያስፈልጋቸው ያህል የቴሌ መስመርም የግድ ያስፈልጋቸዋል፡፡ከጥቂቶች በስተቀር፡፡የቴሌ ኔትወርክ መቆራረጥ ለውጥ የማያመጣው ምናልባት በወፍጬ ቤቶችና መሰል ኢንዳስትሪዎች ሊሆን ይችላል፡፡አስተማማኝና ፈጣን የሆነ የገንዘብና የመረጃ ለውውጥ እንዲኖር ግን የኔትወርክ መኖር የግድ መሆኑን ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ነው፡፡ታድያ የፋይናንስ እንዳስትሪው በመምራት ላይ ያሉት ዶክተር ምን እያሉን ነው?

ይህ አባባል በህዝቡ ቁስል ላይ ስንጥር መጨመር እንጂ ሌላ ሊባል የሚችል አይመስለኝም፡፡




No comments:

Post a Comment