Tuesday, March 25, 2014

የህዳሴው ግድብ፡ ሃገራዊ ዘመቻ





Picture taken from: https://www.facebook.com/groups/hdaseethiopia/
እኛ ኢትዮጵያውያን በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም ከምንታወቅባቸው ነገሮች አንዱ ዘመቻ፡፡በተለይም ደር ድንበራችንን ለማስከበር የምናደርገው ዘመቻ በዓይነቱም በመጠኑም ለየት ይላል፡፡ልዩ ህዝቦችም ያሰኘናል፡፡ግብፆች የአባቶቻችንን ሃገረ ሐበሻን ከጫፍ እስከጫፍ ለመቆጣጠርና ህዝቦችዋም ለማስገበር ተንደርደረው ሲመጡ በዘመቻ አይቀጡት ተቀጥተው ያለ ወሬ ነጋሪ በሐበሻ ምድር ቀልጠው ቀርቷል፡፡ፋሽስት ጣልያኖችም እኛን የማስገበር ሃገራዊ ራኢ ነበራቸው፡፡የጠላት አደጋ ባንዣበበባቸው ቁጥር ቆፎው እንደተነካበት ንብ ሆ ብለው የዘመቱት አባቶቻችን ሰላቶዎቹን በመቐለ ውሃ ውሃ አሰኝተውታል፡፡በሰሐጢ፣በደጉዓሊና በዓደዋም አክረካሪያቸውን እየሰበሩ መልሰዋቸዋል፡፡የዚያድባሪ ኢትዮጵያን የመቆጣጠር ህልመም ቀዠት ሆኖ እንዲቀር ያደረገው የአበቶቻችን ዘመቻ መሆኑን አሌ የሚባል አይመስለኝም፡፡

የሱዳኖቹ ማህዲስቶችም ፊት ለፊታቸው የቆመውን ሁሉ እንደ እሳት እየፈጁ እስከ ጥንታዊ ታሪካዊትዋ ጉንደር ድረስ ደርሰው ነበር፡፡በአፄ ዮሃንስ አራተኛ የሚመራው የአባቶቻችን ዘመቻ ቀለበሳቸው እንጂ፡፡መቸስ በትዕቢት ያበጡ የውጭ ወራሪዎች ተኝተው አይተኙልንም፡፡ሌላው ቀረቶ ሻዕብያም እኛን ከመውረር ወደ ኋላ አላለችም፡፡የሻዕብያ ባለቤት የሆኑት ፕረዚደንት ኢሳያስም‹‹እኛ ከባድመ ወጣን ማለት በቃ ፀሐይ ጠልቃ ቀረች ማለት ነው›› በለው ፈክረው ነበር፡፡ዳሩ ኢትዮጵያውያን በካሄዱት ዘመቻ ፀሐይ ግባት አማካኝነት ‹‹በአንድ ራስ ሁለት ምላስ›› እንዲያበቅሉ አደረጋቸው እንጂ፡፡ሻዕብያ ዛሬም ድረስ እኛን ለማድማት መፍጨርጨሯን አላቆመችም፡፡

የኢትዮጵያውያን ዘመቻ በወራሪ ሐይሎች ላይ ብቻ ያነጣጠረ እንዳልነበረ የሚያሳዩን ቋሚ ምስክሮች አሉን፡፡ከአንድ አለት ተፈልፍለው የተሰሩት የአክሱም ሐወልቶች፣የላሊበላና ሌሎች መሰል አብያተ ክርስትያኖች፣የሃረሩ ጀጎል ግንብና የጎንደሩ የፋሲል ቤተ መንግስት ወዘተ በዘመቻ የተገነቡ ስለመሆናቸው የሚያጠራጥረን ነገረ ያለ አይመስለኝም፡፡እነዚህ በዓለም ልዩ የሚያደርጉን ብርቅየና ዘመን ተሻጋሪ ቁሳዊ ቅርሶች ህልቆ መሳፍርት የሌለው ንብረትና የሰው ጉልበት ፈሶባቸዋል፡፡ቢሆንም ግን ዛሬም ደረስ የአንድነታችን ማጠናከርያ፣ የማንነታችን መገለጫ ሆኖው እያገለገሉን ይገኛሉ፡፡ለወደፊትም ቀጣዩ ትውልድ ቀደምቶቹን እያከበረና እያሞካሸ ኮርቶ እንዲኖር የሚያስችሉት ፀፀት አልባ ሃገራዊ ትሩፋቶች ናቸው፡፡

የህዳሴው ግድብም ልክ እንደ አክሱም ሐወልቶችና የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያኖች ሁሉ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተለለፍ አስደናቂ ሃገራዊ ቅርስ ነው፡፡ይህ የሚሊኒየማችን ሃገራዊ ቅርስ እውን እንዲሆን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የቻለውን ያህል እያበረከተ ይገኛል፤ከጥቂት ባንዳዎች በስተቀር፡፡የኢትዮጵያውያን ዘመቻ ግን በጥቂት ባንዳዎች ተኮላሽቶ እንደማያውቅ ታሪክ ምስክር ነው፡፡እናም የህዳሴው ግድብም እንደ ቀደምቶቹ ሃገራዊ ዘመቻዎቻችን ሁሉ እንደምናሳካው ለቅንጣትም አልጠራጠርም፡፡ምክንያቱ ደግሞ ታሪካዊ ቁጭታችንን የምንወጣበት የዘመቻዎች ሁሉ ምሰሶ በመሆኑ ነው፡፡ይህ የዘመቻዎች ምሰሶ ቁጥር አንድ ጠላታቸን የሆነው ድህነትን የምንደመሰስበት የዘመቻዎቻችን ሁሉ እንደ ማሳረግያ የሚያገለግል ነው፡፡እዚጋ ግን የህዳሴው ግድብ እንደተጠናቀቀ ድህነት ሙሉ በሙሉ ይቀረፋል፤ሌሎች ሃገራዊ ዘመቻዎችም አይኖሩም እይልኩኝ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ(እኔ ለፖለቲካ ትርፍ የቆምኩ ኢህአዴግ አይደለሁምና)፡፡


እንደሚታወቀው በአባይ ላይ በቁዘማ ከዘመትን ዘመናት ተቆጥሯል፡፡እንደ አሁኑ ግን በተግባር በተግባር አልነበረም፤ በስነ ቃሎች፣በአባባሎች፣በስነፅሑፎችና በዘፈኖች እንጂ፡፡‹‹የአባይ ልጅ ውሃ ጠማው››፣‹‹አባይ አባይ የሃገር ሲሳይ›› ወዘተ እያለን በቁጭት ከተብሰከሰክን ዘመን የለንም፡፡ከአሁን በኋላ ግን አባይን የምንወቅስበት ጊዜ ታሪክ ሆኖ የምናሞካሸው ዘመን ሩቅ አይደለም፡፡የውሃ ጥምና ርሃብም በመጠኑ እንደሚቀረፉ የሚካድ አይደለም፡፡እንሆ በአባይ ላይ በተግባር ከዘመትን ሶስት ዓመታት ተቆጥሯል፡፡ከአራቱም አቅጣጫዎች ሆ ብለው የዘመቱ ኢትዮጵያውያን ምንም ሳይበግራቸው ቀንና ለሊት እየተረባረቡ ይገኛሉ፤በታሪክ ሰሪው መሃንዲስ ስመኘው በቀለ እየተመሩ፡፡


ለመቃወም ከሚቃወሙት ተቃዋሚዎች ሁሉ ለየት ያለ ሃገራዊ የትግል ስልት በማካሄድ ከሚታወቁት የኢደፓ ግንባር ቀደም መሪዎች አንዱ የሆኑት አቶ ሙሼ ሰሙ የህዳሴው ግድብ እንደሚከተለው በደንብ ገልፀውታል፡፡
የአባይ ውሃ ለኢትዮጵያ ህዝብ አንድ የተፈጥሮ ሀብት ብቻ አይደለም፡፡ የማንነት መገለጫውም ጭምር ነው፡፡ እንደ ሰንደቅ ዓላማው የትም ቦታ ሄዶ የሚያወራበት የሚኮራበት የሚናገርበት ወንዙ ነው፡፡ በሌላ በኩል የአባይ ወንዝ ቀላል የማይባል ድህነትን ለመቅረፍ የሚያግዝ የኢኮኖሚ መሣሪያ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ መጀመሩና ወደ ተግባር መገባቱ በራሱ የሂደቱ መገለጫ ነው፡፡በእያንዳንዱ ሂደት ያለው እድገት በኔ በኩል አመርቂ ነው፡፡ አይቻልም አይሞከርም፣ አይደፈርም የሚባለው ነገር መደፈሩና ወንዙን እስከ መቀልበስ መደረሱ በግብጽ ዘንድ ሁለት ነገርን አስከትሏል፡፡ አንደኛው ሥጋት ሌላኛው ደግሞ የመደፈር ሥሜት፡፡ ይህ ደግሞ በተግባር የእንቅስቃሴው ውጤት መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
የህዳሴው ግድብ በእኔ አቅም ከዚህ በላይ ሊገለፅ አይችልም፡፡ሰውየው እንዳሉት የሃገር አርማ፣የሃገር ኩራት፣ የኢትዮጵያውያን የጋራ ማንነትና መገለጫ ነው፡፡ታድያ ለእናት ሃገር ሰንደቅ ዓላማ የማይዘምት ማን ነው?ኢትዮጵያውያን ‹‹በሃገራቸውና በሚስታቸው ሊሚመጣባቸው አይመለሱም›› የሚባለው ታድያ ለህዳስያችን ካልሆነ ለምን ይፈይዳል?‹‹ጎበዜ ተነስ ጎበዜ በሃገር ጉዳይ የለም ትካዜ›› ማለት ያለብን አሁን ይመስለኛል፡፡

ሃገራዊ ዘመቻ፡ ድሮና ዘንድሮ

ኢትዮጵያውያን ሲዘምቱ ልክ እንደ ደራሽ ጎርፍ ከፊት ለፊታቸው የቆመውን ሁሉ እየበረቃቀሱ፣እያተረማመሱ፣እየገንዳደሱ ጠራርገው ከሰቡበት ያደርሱታል፡፡የኢትዮጵያ ህዝብ የታጋሽነቱን ያህል አንዴ ከተነሳ ማዕበል ነው፤‹‹ሱናሚ›› ነው፡፡ጃፓንን አጥለቅልቆ በመቶ ሽዎችን ጠራርጎ እንደወሰደው ሱናሚ፡፡ክተት ሰራዊት ምታ ነጋሪት የኢትዮጵያውያን ልዩ ማንቅያ ደወል ነው፡፡ሆኖም ግን የድሮና 
የዘንድሮ ዘመቻዎች ለየቅል ናቸው ማለት ይቻላል፡፡

የድሮ ዘመቻዎች (ከቁሳዊዎቹን በስተቀር) አውዳሚ ነበሩ፡፡በዘመቻ ላይ መውደቅና መጣል እኩል ድርሻ አላቸው፤ ጠላት ለመጣል የወገን መውደቅ ግድ ይላል፡፡የሰው ልጅ መተክያ የለሽ ሕይወትና ነብረት ይወድማል፡፡ተራሮች ይራቆታሉ፤ መንደሮች የለወንድ ይቀራሉ፡፡ለም መሬት ተቃጥሎ ወደ አሲድነት ይቀየራል፡፡በአውራው ደግሞ ዓይን ይጠፋል፤ እጅና እግር ይቆረጣል፡፡ወጣቱ አምራች ሃይል አካለ ስንኩል ሆኖ ተመፅዋች ይሆናል፡፡በእንጭጩም ይቀጫል፡፡እንደ አፄ ዮሃንስ አራተኛም አንገት እስከ መቆረጥ ያደርሳል፡፡ውጤቱም በድህነትና ኋላ ቀርነት መደቆስ ነው፡፡የድህነት፣የጦርነትና የኋላ ቀርነት ተምሳሌት ሆኖ መቅረት ነው፤መቀመቅ መውረድ ነው፡፡የድሮዎቹ ዘመቻዎች ድምር ውጤታቸው የኸው ነበር፡፡

ዘንድሮ ግን ጣት፣እግር፣እጅ፣አንገት ወዘተ አይቆረጥም፡፡ቢበዛ የወር ደሞዛችን ብቻ ነው የሚቆረጠው፤ለዛውም ተቆርጦ አይቀርም፡፡የመቆጠብ ያህል ነው፤በብዙ ዕጥፍ ይወልዳል፡፡ይበረክታል፡፡በረከቱም ለትውልድ ይተርፋል፤ልክ እንደ አክሱም ሃውልት፣እንደ ላሊበላዎቹ ውቅር አብያተ ክርስትያናት ሃገር ለሚያስጠራው የህዳስያችን ግድብ መገንብያ ይሆናል፡፡እናም ትርፍ እንጂ ኪሳራ የለውም፡፡አይ ይጎድልብናል እንጂ የምንል ከሆነም ብር እንጂ የሚጎድልብን አካል አይኖርም፡፡የንዋይ(ገንዘብ) እንጂ የህይወት መስዋእትነት አንከፍልም፡፡ውጤቱም እድገት፣ብልፅግና፣ሃገራዊ ክብርና ኩራት፣የአስተሳሰብ ልዕልናና ምጥቀት እንጂ ድህነትና ኋላ ቀርነት አይደለም፡፡

በመሆኑም መሸለል ካለብን፣የህዳሴው ግድብ ቦንድ በመግዛት እንሸልል፡፡የምናቅራራው፣የምንፈክረው የሚሊኒየማችን ታሪካዊ ምሰሶ ለሆኖው ህዳሴ ግድብ የቻልነውን ያህል በማበርከት መሆን አለበት በይ ነኝ፡፡ይገባኛል…አንድ እንድ ራስ ወዳድ ፖለቲከኞች ራሳቸውን ከፍ ከፍ ለማድረግ እንደሚጠቀሙበት፣ ለርካሽ ፕሮፓጋንዳ እንደሚያውሉት ይገባኛል፡፡ቢሆንም ያን ያህል አደጋ የለውም፡፡የአክሱም ሐወልቶችን ያስገነባው መሪ ዘሬ የት አለ?አፄ ፋሲለደስ፣ቅዱስ ላሊበላ፣ጀጎል ወዘተ ዛሬ የት ናቸው? ታድያ በእነዝያ ነገስታት ስም የተገነቡት ሐወልቶችና ድንቃ ድንቅ ግንቦች ዛሬ የምናፍርባቸው ናቸው እንዴ?እንደ እኔ እምነት ከሆነ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት ለፈለገው ዓላማ ቢገነቡም እኮራባቸዋለሁ፡፡የፋሲልና የጀጎል ግምቦችም እንዲሁ ሐሴት ይሰጡኛል፡፡የህዳሴው ግድብ ከእነዚህ በምን መልኩ ይለያል?

እኛ ኢትዮጵያውያን ለተቃውሞ በጋራ መዝመት ያለብን መንግስታት ለክብራቸው አስበውም ይሁን ወይም ሃገር ለማሳደግ የራሳቸው ጉዳይ፣ ሲገነቡ ሳይሆን ሲያፈርሱ ብቻ መሆን አለበት፡፡የባቡር መስመር ሲገነባ ተጠቃሚዎቹ እኛው ነን፡፡አባይ ሲገደብ የሚገደበው ስደትና እንግልት ነው፡፡በአንፃሩ ደግሞ ለመቶ ዓመታት ተከምሮብን የኖረው ድህነትና ኋላ ቀርነት ድርምስምሱን ይወጣል፡፡እናም ማንኛውም መንግስት ሃገር ሲገነባ ከቻልን አብረነው እንገንባ፡፡ካልቻልንም ባናደናቅፈው የሚሻል ይመስለኛል፡፡ሃገር ለማፍረስ ከተነሳ ግን ዋ! ይቀምሳታል፡፡እንደልማዳችን ሆ ብለን በመዝመት ፍርስርሱን ማውጣት ነዋ፡፡

No comments:

Post a Comment