ትናንት ህፃን ልጅ ነበርኩ፤የቤተሰብ ሙሉ ድጋፍ የሚስፈልገኝ እምበቆቅላ፡፡የምስቀውም የማለቅሰውም፣የማዝነውም
የምደሰተውም በቀላሉ ነበር፡፡ብቸኛው መሳርያዬ እምባ ነበር፡፡ከፋኝ ደላኝ ተጠያቄዎቹ በከፊል ያደኩበት ማሕበረሰብ በአውራው ደግሞ
ወላጆቼ ነበሩ፡፡ምንም የማላውቅ ግን የማወቅ ጉጉት የሚያንገበግበኝ፣ምንም ነገር የማያሳስበኝ፣ራሴን ችዬ መቆም የማልችል ቀምበጥ
ነበርኩ፡፡የመጠየቅ እንጂ የመመለስ፣የመቀበል እንጂ የመስጠት ግዴታ እንዳለብኝ አላውቅም ነበር፡፡ባጭሩ ዓለም ማለት እኔ ስተኛ የምትተኛ፣
ስነቃም የምትነቃ፣ ወርድና ቁመቷ፣ስፋትና ጥልቀቷ በእኔ ልክ የተሰራች ይመስለኝ ነበር፡፡
ልጅ እያለሁ ብዙ ነገሮችን አይቻለሁ፡፡እረኛ ሁኜ ፍየል፣በግ፣ከብትና አህያ አግጃለሁ፤ ከእሮኞች
ጋር ጣፋጭና መራራ የእረኝነት ህይወት አሳልፌያለሁ፡፡ከአርሶ አደሮች ጋር አርሻለሁ፣ማሳዎቼን በሰብል ሸፍኛለሁ፣ አርሜያለሁ፣በአጨዳው
ላይ ቀንና ሌሊት ተሰማርቻለሁ፡፡በአጠቃላይ የገጠር ንሮ ኑሬበታለሁ፡፡የኸው እስከ ዛሬም በሐሳብ የኋሊት እነጉዳለሁ፡፡
ብዙ ወንዞችን ተሻግሬ ሌሎች ብዙ ወንዞችን ተሻግሬያለሁ፡፡ብዙ ሰዎች ጎርፍ ጠራርጎ ሲወስዳቸው
አስተውያለሁ፤ከጎርፍ አደጋ ለጥቂት ካመለጡ ሰዎችም አንዱ ነኝ፡፡ ብዙ ተራሮችን አልፌ ሌሎች ብዙ ተራሮችን አዳርሻለሁ፡፡እንደ ዝንጀሮ
ከቋጥኝ ወርጄ ወደ ቋጥኝ ወጥቻለሁ፡፡ገደላገደሎችን በእጆቼ ቧጥጬ ወጥቻለሁ ወርጃለሁ፤ በእነዝያ ገደሎች ብዙ ሰዎች መሞታቸውም አውቃለሁ፡፡ዳገቱም
ቁልቁለቱም ወርጄ ወጥቸበታለሁ፡፡ሜዳውም ሩጬበታለሁ፣ ተራራውም ሌሎች ተራራዎችን አይቸበታለሁ፡፡ብዙ ጫካዎችን አቋርጫለሁ፡፡እንደ
ጦጣና ጉሬዛም ከአንዱ ዛፍ ወደ ሌላኛው ዘልያለሁ፡፡
ለአቅመ አባትነት የደረሰው ልጅ በውሃ ቀጠነ ምክንያት ወላጅ እናቱን ገድሎ እሪ በከንቱ በሚባል
ጉድጓድ ውስጥ መክተቱን ሰምቻለሁ፡፡መጀመርያ እንጂ መጨረሻው የማይታወቀው ጉድጓድም በአይኖቼ አይቸዋለሁ፡፡ጉድጓዱ ማን ቆፈረው፣መቼ፣ለምን?
አላውቅም፡፡
አባት ያለ በቂ ምክንያት ምስኪን ልጁን ደብድቦ መግደሉን አውቃለሁ፡፡ልጁ ልጅነቱን እንኳን
ሳይጣጥም በለጋ ዕድሜው ተቀጨ፡፡አባት ግን አልገደልኩም ብሎ በመካዱ አምስት ዓመታት ብቻ ታስሮ ተፈታና ብዙ ሴት ልጆችን ወልዶ
ከብዶ ዛሬም ድረስ በሰላም ይኖራል፡፡
ህንደያ ከትዳር ውጪ የተወለደ ነበር፡፡ምስኪን ልጅ! እናቱ ልጅ ማሳደግ ቀርቶ ለራሷም የሚላስ
የሚቀመስ አልነበራትም፡፡አባቱም ከቁመናው በስተቀር ክፉና ደጉን በወጉ ያልለየ ትልቅ ህፃን ነበር፡፡ከሌላ ሴት ጋር በተከበረው ትዳር
ተጣምሯል፡፡ይሁን እንጂ ከመናገር መጮህ ያስቀድም ነበር፡፡ከመጮህም መደባደብ ቀዳሚው ምርጫው ነበር፡፡
ህንደያን ጥዋት ማታ ይጮህበታል፡፡ባገኘው ቁጥር እጁ ላይ በገባው ማንኛውም ነገር ይደበድበዋል፡፡የሚደበድበውን
ያህል የሚበላም የሚጠጣም አይሰጠውም ነበር፡፡ህንደያ ከቀን ወደ ቀን እየከሳ፣እየመነመነ፣ እየተዳከመ ሄደ፡፡በጣሙን የከሳውና የተዳከመው
አካሉ ብቻ አልነበረም፡፡ቅስሙም ተሰብሯል፤ተስፋውም ጨልሟል፡፡ዕድሜው ከአስር ዓመት የማይበልጥ ቢሆንም ፊቱ ግን የሰማያንያ ዓመት
አዛውንት ይመስል ነበር፡፡
ሁል ጊዜ የደረቁ የእምባ ዘለላዎች በሁለቱም ጉንጮቹን አቋርጠው አጥንት ብቻ ወደ ቀረው ደረቱ የሚወርዱባቸው ቦዮች
ይታያሉ፡፡እንደ ህፃን አይጫወትም፡፡አይስቅም፡፡ሁል ጊዜ ፍዝዝ፣ትክዝ እንዳለ ነበር፡፡ከመጠን በላይ ከመደብደቡና፣ በውሃ ጥምና በረሃብ
ከመቀጣቱ የተነሳ ፍርሃቱም ጭንቀቱም የረሳው ይመስላል፡፡ትንሽ ራመድ ብሎ ድንገት ይቆምና አሻግሮ እየተመለከተ እዛው ደርቆ ይቀራል፡፡ያኔ
አባቱ መጥቶ ባለው በሌለው ሃይሉ ተጠቅሞ ነብሱን እስኪስት ይደበድበዋል፡፡‹‹ሰውየው›› ልጁን ደብድቦ ሲደክመው እዛው ትቶት ይሄዳል፡፡
አህህህ! ህንደያ ግን ለምን ነው የማልረሳው? ብዙ ነገሮችን ረስቻለሁ፤ቅስምን የሚሰብር ሐዘን፣እንደ ግልገል የሚያዘልል
ደስታ፣ ብዙ ክፉና ደግ ሰዎችን ረስቻለሁ፡፡ህንደያን ግን ልረሳው አልቻልኩም፡፡ያ ከመጠን በላይ የተጎሳቆለው አካሉ፣ያ በእንባ የራሰው
ፊቱ፣ያ የህፃንነት ቀንና ተስፋ የሌለው አመለካከቱ ዛሬም ድረስ ከፊት ለፊቴ ቆሞ ይታየኛል፡፡ከዕለታት ባንዱ ቀን ህንደያ ቤት መድረስ
አቅቶት በረሃ አደረ፡፡በገባው በወጣው የሚቀጠቀጠው ልጅ ብቸኛው መሸሻው በዋለበት በረሃ ማደር ነው፡፡ህንደያ ግን ይሞታል እንጂ
ዱላ የአባቱን ዱላ ፈርቶ በረሃ አድሮ አያውቅም ነበር፡፡ያኔ ግን እግሮቹ ቀጤማ ሆነው አላላውስ አላንቀሳቅስ አሉት፡፡ከአንድ የሸበት
ትልቅ ቋጥኝ ስር አረፍ እንዳለ እንቅልና ረሃብ ተባብረው ደቆሱት፡፡እዛው ወድቆ አደረ፡፡
በነጋታው ያ ጭራቅ አባቱ እወደቀበት ቋጥኝ ስር አገኘው፡፡እሳት ጎርሶ እሳት እየተፋ በያዘው ሽመል ይከተክተው ገባ፡፡‹‹ተነስ
አንተ አህያ!›› እያለ እንደልማዱ ጉልበቱ እስኪዝል ድረስ ደጋግሞ ነረተው፡፡ባለ በሌለ ሐይሉ ቀጠቀጠው፤ ደበደበው፡፡ህንደያ ግን
እንባው ያንቆረቁራል እንጂ መጮህ አልቻለም፡፡በወደቀበት ሆኖ ይንፈረፈራል፡፡ያጣጥራል፡፡በመጨረሻም አይኖቹን ገልብጦ እስከወድያኛው
አሻለበ፡፡ዓለም እንደ ብረት ግላ፣ እንደ እሾህ ሹላ አላስቆም አስቀምጥ አለችውና የህይወት ሩጫውን በጅምር ቋጨው፡፡
እኔም የህንደያን ያህል ተደብድቤያለሁ፡፡ተርቤያለሁ፤ ምላሴ እስኪደርቅ ድረስ በውሃ ጥም ተሰቃይቻለሁ፡፡ብዙ ጊዜም
በረሃ አድሬያለሁ፡፡ሆኖም ግን ጅብም አልበላኝም፣ ሞትም አልወሰደኝም፡፡እንሆ ያ ሁሉ ውጣ ውረድ አልፎ ለዛሬ ደረሻለሁ፡፡ውድ አንባቢ
ግን ‹‹እና ምን ይጠበስ?›› ይሉኝ ይሆናል፡፡መልሴ ምን ነው፡፡ምንም ባይጠበሰ፣ምንም ባይቆረስ፣ምንም ባይጎረስ፣ ምንም ባይደቆስም
ዛሬ ለእኔ ልዩ ቀን ነች፡፡መራራውን ልጅነት ሸኝቼ የአባትነት ህይወት አንድ ብየ የጀመርኩባት፡፡
ዛሬ አባት ሁኛለሁ፤የአባትነት ሃላፊነቶችና ግዴታዎች መወጣት ያለበኝ የአንድ ቤተሰብ ሃላፊ
ነኝ፡፡ቢቻልም ባይቻልም ራሴን ችዬ ሌሎችን የመቻልና የማስቻል ግዴታ ተሸክሜያለሁ፡፡ብዙ ነገሮች ያሳስቡኝ ነበር፡፡የውድ ባለ ቤትየ
መውለጃ እየተቃረበ ሲመጣ የወንድ ምጥ ማማጤን አልቀረም፡፡የእርሷ ምጥ የእኔም ምጥ ነበር፡፡በሰላም ተገላግላ እፎይይይ!ስትል ደግሞ
እኔም እፎይይይ! አልኩ፡፡አሁን ብዙ ነገሮች ያሳሰቡኝ ያህል ያስደስቱኛል፡፡ዓለም ጣፋጭና መራራውን የምታስጎነጭ የሃሳብ ማዕበል
ነች፤ ሕይወትን ለማስቀጠል ማዕበሉን ተቋቁሞ መዋኘት የግድ ትላለች፡፡
ሕይወት በትናንት፣ ዛሬና ነገ ምዕራፎች የተከፋፈለች መሰላል ነች፡፡እናም ስትወጣም ሆነ ስትወርድ
ከፍተኛ ጥንቃቄና ትዕግስት ትጠይቃለች፡፡ትናንት የትምህርት ክፍል ጊዜ ነበር፤ብዙ ነገሮችን የቀሰምኩበት፡፡ዛሬ የትናንቱ ክልሰ ሐሳብ
ለመተግበር ላይ ታች የምልበት ነው፤ እያስተማርኩ የምማርበት፡፡ነገ የዛሬው ልፋቴ ውጤት የማይበት ይሆናል፤የዘራሁትን ይጎመራል፣ያፈራል፡፡
አሁን የልጅነት ምዕራፍ አጠናቅቄ በአባትነት የመጀመርያው ገፅ ላይ እገኛለሁ፡፡በመሆኑም በጣም ተደስቻለሁ፡፡ለካ
ከልጅነት ወደ አባትነት የሚደረገው ሽግግር ይህን ያህል አስደሳች ንሯል?ለካ ሙሉ ሰው ማለት ሐላፊነት የሚሰማው አባትነት ንሯል?
No comments:
Post a Comment