Saturday, March 1, 2014

የህወሓት የስልጣን ማራዘምያ መንገዶችና ያልተፃፉ አቋራጭ መሰላሎች


በህወሓቶች ዘንድ የተለመዱ ግን ደግሞ ያልተፃፉ አቋራጭ የስልጣን መወጣጫ መሰላሎች አሉ፡፡ብዙዎቹ የሃገራችን ጎምቱ ጎምቱ ባለስልጣናት እነዚህን መሰላሎች ተጠቅመው ከቀበሌ አስተዳዳሪነት ወደ ሚኒስተርነት ተወንጭፈውባቸዋል፡፡ከሌሎች የተለየ የትምህርት ደረጃ፣የማስፈፀም ብቃትና የአመራር ችሎታ ስላላቸው ግን አይደለም፡፡የስርዓቱ ቀዳዳዎችና የመሰላሎቹን አቅጣጫዎች ጠንቅቀው በማወቃቸውና ተግባራዊ በማድረጋቸው ብቻ እንጂ፡፡

መሰላሎቹን የት እንዳሉና እንዴት እንደሚጠቀሙባቸው የማያውቁ ግን ዛሬም ድረስ ‹‹ባለህበት ርገጥ›› እየተባሉ ባዛችው ቀበሌ ይገኛሉ፡፡የስልጠናም የስልጣንም ዕድል ሳያገኙ ሀል ጊዜ የበላይ አለቃ ትእዛዞችን ለማስፈፀም ሲዋትቱ ይኖራሉ፡፡ንሯቸውም ያው ነው፤ ልክ እንደኗሪው ህዝብ አፈር ለብሰው ዳዋ ልሰው ይኖራሉ፡፡ይሁን እንጂ ህዝቡም አይወዳቸውም በመንግስት ደረጃም ብዙ ተቀባይነት የላቸውም፡፡ሰርተው እዳያልፍላቸው ሙሉ ጊዝያቸውን የበላይ አለቃ ትእዛዝ ለማስፈፀም ሲብከነከኑ ያጠፉታል፡፡የአለቃቸው ትእዛዝ ‹‹ከለይ የወረደ መመርያ ነው›› እያሉ በህዝቡ ላይ በግዳጅ ስለሚጭኑበት ደግሞ ህዝቡ አቂሞባቸዋልና ከሁለት ያጣ ሆኖው ይኖራሉ፡፡

የስልጣን ኮርቻ መቆነጣጫ ርካቦቹ ብዙ ናቸው፡፡ለጊዜው ሁለት በጣም የታወቁ መሰላሎችን በናሙናነት አቀርባለሁ፡፡ሃተታየም በእንዚሁ ፍቱን መሰላሎችን የሚያጠነጥን ይሆናል፤ መልካም ንባብ፡፡

የስጋ ዝምድና

የመጀመርያው መሰላል ድሮም የነበረ፣ ዛሬም ህወሓቶች ከድረው በበለጠ አሳምረው የሚጠቀሙበትና በዚሁ የፖለቲካ አካሄዳችን ከቀጠልን ደግሞ ምናልባት ለወደፊቱም የሚኖር ነው፡፡ባለፉት ስርዓቶች፣ ዝምድና ሁነኛው የስልጣን መቆናጠጫ መሰላል ነበር፤ ሰሎሞናዊው ስርወ ንግስነትን ልብ ይሏል፡፡ስልጣን፣ ለተመረጡ ጎሳዎች ከፈጣሪ የተሰጠና ከትውልድ ወደ ትውልድ በዘር የሚተላለፍ እንደነበር በክብረ ነገስት ሰፍሮ ይገኛል፡፡

የህወሓቶች የስልጣን ምንጭም በጥቅም ትስስር ወይም በስጋ ዝምድና ነው የሚገኘው፡፡ማንኛውም ሰው አንድ ትልቅ የህወሓት ባለስልጣን ካለው የስልጣን ኮርቻውን ለመቆናጠጥ ሁለት ዓመታት አይፈጁበትም፡፡በቃ ስራ ከያዘ ከሁለት ዓመታት በኋላ የወረዳ፣የዞን ወይም የአንድ ፌደራል መስርያ ቤት ማናጀር፣ኦፊሰር ወዘተ ሆኖ ታገኙታላችሁ፡፡ለህዝብ የሚጠቅም ስራ ግን ሲሰራ አይታይም፤ ሙሉ ጊዜውን ማለት ይቻላል በስብሰባዎችና ስልጠናዎችን ነው የሚያሳልፈው፡፡

ማንኛውም የውጭ ስልጣናዎች ቁጥር አንድ ተጠቃሚ እሱ ነው፡፡ወደ ቻይናና ሌሎች ሃገሮች የሚያደርገው ጉዞ ከስራ ወደ መኖርያ ቤቱ ከሚያደርገው መመላለስ አያንስም፡፡በየ መስርያ ቤቱ የሚገኙ ህግና ደምቦች ለነዚህ ሰዎች አይመከቱም፤ ተፈፃሚነትም የላቸውም፡፡የአንድ መስርያ ቤት ህግና ደምብ ይቅርና የሃገሪቷ ህግ ደምብም አይገዛቸውም፡፡ የፈለጉትን ያህል ሃብትና ንብረት ማካበት ይችላሉ፡፡ ቀልባቸው የከጀላትን ሴት እሺ ካለች እሰየው፣እምቢ ካለች ግን አስገድደው ይደፍራሉ፡፡ ሌላው ቢቀር ሰው ቢገድሉም የሚጠይቃቸው የለም፡፡በአጠቃላይ ሁሉ በእጃቸው ሁሉ በደጃቸው ነው፤ስልጣኑም፣ ቁንጣኑም፣ሰይጣኑም ለነዚህ ሰዎች ቅርብ ነው፡፡

እዚ ጋ ለምን ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ህወሓቶች አብዮታውያን ስለሆኑ አይደለም እንዴ መስፍናዊው ስርዓት ለመመለስ ይታገል ለነበረው ኢድዩን በምዕራብ ትግራይ በተካሄደው ጦርነት የደመሰሱት? ለህዝብ የቆሙ አብዮታውያን ባይሆኑ ንሮ ነብሰ በላው ደርግን ተፋልመው መገርሰስና ህዝቡ የሚከበርበት ህገ መንግስት ቀርፀው ማጽደቅ ለምን አስፈለጋቸው? ብለው የሚጠይቁ እንደሚኖሩ አልጠራጠርም፡፡አዎ፣ ጥያቄዎቹ ተገቢ ናቸው፡፡

ህወሓቶች ለህዝብ የቆሙ ህዝባዊ ተጋዮች ይመስሉኝ ነበር፡፡አይደሉም፡፡የመስፍናዊው ስርዓት ርዝራዥች ናቸው፡፡ይህን ያረጋገጥኩት የሚከተሉትን ጥያቄዎች ራሴን ከጠየቅኩና በቂ መልስ ለማግኘት ብዙ ከተፍጨረጨርኩ በኋላ ነበር፡፡የህወሓቶች ማንነት ግልፅ የሆነልኝም ከብዙ የሃሳብ ውጣውረድ ግብግብ ነው፡፡ህወሓቶች ህገ መንግስቱን አርቅቀው ያፀደቁት ለምን ነበር? ለምንስ ተግባራዊ እንዲሆን አያደርጉም? ለምንድን ነው ሌሎችን ህገ መንግስቱን ጥሷል ብለው ሲያስሩና ሲያንገላቱ የራሳቸው አባላት ግን ህገ መንግስቱን የማያከብሩት?

ከሃፄ ሃይለስላሴ አከዛዝ ጀምሮ ያለው የሃገራችን ታሪክ ብንመረምር ሃገር የመሳፍንት ብቻ ነበረች፡፡ስልጣን የሚይዘው መስፍንና የመሳፍንት ለጅ ብቻ ነበር፡፡ያሻውን የሚበላውና የሚጠጣው መስፍኑና የመሳፍንት ልጆች ናቸው፡፡የትምህርት ዕድልም ቢሆን ለመስፍናዊው ስርዓት ባለቤቶች ብቻ የተፈቀደ ነበር፡፡የተራው ህዝብ ለጅ መማር ቀርቶ ወታደር የመሆን ዕድልም አልነበረውም፡፡ከአንዱ መስፍን ጋር ተለማምጦ ወታደር(ነጭ ለባሽ) የመሆን ዕድል ካጋጠመውም ሁል ጊዜ ተራ ወታደር ሆኖ ነው የሚኖረው፤ ቀድሞ የጥይት እራት የሚሆነውም እሱ ነው፡፡

የህወሓት የትጥቅ ትግል ጀማሪዎች የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወይም ምሩቆች እንደነበሩ ገድለ ህወሓት በሆኑ መፅሓፎች ሰፍሮ ይገኛል፡፡በተለይ በወቅቱ በእድሜም በስልጣንም ተወዳዳሪ ያለነበረው ገሰሰው አየለ(ስሑል) የአፄ ሃይለስላሴ የምክርቤት(ፓርላማ) አባል ነበር፡፡እነ ስብሃት ነገጋ፣መለስ ዘይናዊ፣ ስየ አብርሃ፣ ስዩም መስፍን ወዘተ እልም ያሉ የመሳፍንት ልጆች ናቸው፡፡

በዛን ጊዜ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ገብተው የመማር ዕድል የሚገጥማቸው የመሳፍንት ልጆች ብቻ በመሆናቸው የህወሓት የትጥቅ ትግል ጀማሪዎችም የመስፍናዊው ስርዓት ትርፍ ራፊዎች ናቸው፡፡የትጥቅ ትግል የጀመሩበት መክንያትም ለትግራይ ህዝብ አስበውና ተቆርቁረው ሳይሆን የስልጣን ጥማቸውን ለማርካት ብቻ ነው፡፡በስልሳዎቹ ተነስቶ እንደ ፊኛ ፈንድቶ የቀረው ህዝባዊ አብዮት የተቀጣጠለውም የከሰመውም በመስፍናዊ ስርዓት ርዝራዣች በመጠለፉ ነው፡፡የስልሳዎቹ ጦርነቶችም ልክ እንደ በዘመነ መሳፍንት እንደ ተካሄዱት ጦርነቶች በመሳፍንት ልጆች መካከል የተካሄደ የስልጣን ሽምያና እሽቅድድም ነበር፡፡


ህወሓቶች በአፄው ስርዓት በትግራይ ክልል ተሹሞው የገዙ የነበሩትን መሳፍንት እንዳለ ለመደምሰስ የተነሱበት ምክንያቱም ይኸው ነው፡፡እነዝያ ሹሞኞች እኮ በህዝብ ተመርጠው ሳይሆን በዘርና በጉቦ ነበር ለሹመትና ለመዓርግ የበቁት፡፡ህወሓቶች እንዛያ ሹሞኞችን ያለ ርህራሄ የፈጇቸው ለህዝቡ አስበው ብቻ ነው ማለት አይቻልም፡፡ምናልባት ትናንሽ ሹሞኞች የነበሩ ወላጆቻቸው በትላልቁ ሹሞኞች የነበራቸው ጥላቻ እየተረኩላቸው ሳያሳድጓቸው አልቀሩም፡፡እንጂማ ተሸንፈው የተማረኩ መሳፍንቶችን መግደል ምን አመጣው?

ህወሓቶች ደርግን ደምስሰው የስልጣን ኮርቻ ከተቆናጠጡ በኋላ ህገ መንግስቱን አርቅቀው ያፀደቁት ሆኖም ግን ከ22 ዓመታት በኋላም ተግባራዊ ያላደረጉት ከላይ በተጠቀሰው መስፍናዊ ርዝራዥነታቸው ምክንያት ነው፡፡ስልጣን ከእነርሱና ከቤተሰቦቻቸው እንዲወጣ አይፈልጉምና የስልጣናቸው መከታ ነው፡፡ቤተሰቦቻቸው በህግ የማይገዙትና ህዝቡን እንደፈለጉ ሲያደርጉት ጀሮ ዳባ ልበስ ብለው ዝም የሚሉትም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡

ዛሬም ልክ እንደ ትናንቱ ‹‹ንጉስ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ›› ነውና፡፡ኢኮነሚውም ስልጣኑም ከእጃቸው እንዲወጣ ስለማይፈልጉም ነው እንዝያ ነፃ አውጪ ነን ባዮች በቶምሰ፣ወንዶ፣ጥረትና ትእምት አማካኝነት የሃገሪቷን ኢኮኖሚ የተቆጣጠሩት፡፡‹‹የተትረፈረፈ ስልጣን የተትረፈረፈ ሃብት ያስገኛል፣ የተትረፈረፈ ሃብትም የተትረፈረፈ ስልጣን ምንጭ ነው›› የሚባለው የፈረንጆች አባባል ተግባራዊ ለማድረግ ነው እየሰሩ ያሉት፡፡የህወሓት በለ ስልጣናት ልጆችም የት እንደሚማሩና ለማስተማርያ ማን እንደሚከፍልላቸውም የታወቀ ነው፡፡ባለ ስልጣኖቻችን በህዝቡ ጫንቃ የሚኖሩ ተገልጋዮች እንጂ አገልጋዮች አለመሆናቸውን የ22 ዓመታት የአገዛዝ ዘመናቸው እማኝ ነው፡፡

የጥቅም ትስስር

ሁለተኛው የስልጣን መቆነጣጫ አቋራጭ መንገድ የጥቅም ትስስር ነው፡፡ከላይ እንደ ተገፀው ህወሓቶች ስልጣን ከእጃቸው እንዳይወጣ ብቻ ሳይሆን ከልጅ ልጆቻቸው እጅ እንዲወጣም አይፈልጉም፡፡እንደ አፄ ሃይለስላሴ በትራስ ተገድለው በወንበራቸው ስር ካልተቀበሩና እንደ ደርግ በጉልበት ካልተባረሩ በስተቀር በእጃቸው ያለው ስልጣን ፈቅደው መስጠት አይፈልጉም፡፡በመሆኑም ከህገ መንግስቱ በተጨማሪ የስልጣናቸው መከታ የሚሆኑ፣ በገንዘብና በስልጣን በቀላሉ የሚታለሉ ሰዎችን ከያሉበት ያሰባስባሉ፡፡

እነዚህ ለግዝያዊ ጥቅም ሟቾች አንዴ በሙስና ከተጨማለቁ መመለሻ የላቸውም፡፡‹‹የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም›› እንደሚባለው ተጨማሪ ሙስናዎችና እጅግ የተወሳሰቡ ዘግናኝ ወንጀሎችን ይፈፅማሉ፡፡ይሁን እንጂ የህወሓቶች ትእዛዝ እስከፈፀሙ ድረስ በሙስናም በሌላ ወንጀለም አይጠየቁም፡፡የሚያስተዳድሩት ህዝብ ጉዳቸው አውቆ ማመፅ ከጀመረም ወደ ሌላ አከባቢ ተዛውረው ከፍተኛ ስልጣን ይሰጣቸዋል እንጂ ማንም አይነካቸውም፡፡በመሆኑም ተጨማሪ ሙስናዎችና ሌሎች ወንጀሎች ከመፈፀም ወደ ኋላ አይሉም፡፡

ሌላው ይቅርና የማያውቃቸው ቢኖር እንኳ ይህን ገመናቸውን እንደ ጀብድ በመናገር ለማስፈራርያነት ይጠቀሙበታል እንጂ አያፍሩበትም፡፡ምክንያቱም የእነርሱ አለቆችም በማንኛውም መልኩ የማይሻሉ ዝንጀሮዎች መሆናቸውን ያውቃሉና ነው፡፡ህወሓቶችም ከምንም በላይ ስልጣናቸው ይበልጥባቸዋልና ወንጀለኞቹን ሃይ አይሉዋቸውም፡፡ይልቁንስ ከቦታ ቦታ እያሽከራከሩ ሲጠቀሙባቸው ነው የሚታው፡፡‹‹ተመሳሳይ ክንፍ ያላቸው ወፎች በጋራ ይበራሉ›› እንደሚባለውም ወንጀለኛ ለወንጀለኛ እየተባበሩ ህዝቡን ቁም ስቅሉን ያሳዩታል፡፡

ከእንዚህ አንዱ ብርሃኑ ሃይለስላሴ ነው፤ያ የማይጨው ኮርማ፡፡የማይጨው ኮርማ የፈፀማቸው ወንጀሎች ህግ ባለበት ሀገር በሞት ፍርድ የሚያስቀጡ ናቸው፡፡በአጠቃላይ ወደ ሃያ የሚጀጠጉ ሴቶችን አስገድዶ መድፈሩን ታውቀዋል፡፡ይህን አስገድዶ የመድፈር አባዜው የተጠናወተው ከአዲስ አበባ ተመርቆ የዓድሽሁ(የወረዳ እምባ አላጅ መቀመጫ) ጤና ጣብያ ሃላፊ ሆኖ እንደተሾመ ነበር፡፡በወረዳው ህዝብ ብዙ ከተወራበትና ብልግናው ሊጋለጥ ከተቃረበ በኋላ ግን ለስልጠና ወደ ጦላይ ተልኳል፡፡

ጦላይ በስልጠናላይ እያለ ከሰልጣኖቹ አንድዋን አስገድዶ ይደፍራል፡፡ነገርየው እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት የሚያስቀጣ ቢሆን ዳሩ በሽምግልና ይሁን በማስፈራራት ውሉ ባልታወቀ ሁኔታ ነፃ ወጣ፡፡ጦላይ ሰልጥኖ(ሰይጥኖ) ከተመለሰ በኋላም የካርል ለምለም ማይጨው ስራ ስኪያጅ ሆኖ ይሾማል፡፡እዛውም እንደለመደው ወደ 15 የሚጠጉ ሴቶችን አስገድዶ ይደፍራል፡፡የህዝቡ ብሶት ከመጠን በላይ ተለጥጦ ሊፈነዳ ሲደርስ ግን ‹‹በሂስና ግለሂስ›› አማካኝነት ነፃ ተብሎ በአሁኑ ሰዓት የክልል ትግራይ የጤና ቢሮ በለሙያ ሆኖ እንደተሾመ ነው አብርሃ ደስታ ቤስቡክ ገፁ ያሰፈረው፡፡

ህሊና ላለው ሰው ይህ ምን ማለት እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ህወሓት ህዝብ ለማገልግል ሳይሆን መስፍናዊ ስርዓቱን ለማስቀጠል የተነሳ ድርጅት መሆኑን ነው፡፡ህወሓት ለስልጣን ያበቃው የትግራይ ህዝብ ደም ነው፡፡የህወሓት በለስልጣናት ዋሻ ውስጥ ሆኖው ህዝቡን እርሰ በርሱ እንዲፋጅ አደረጉ፡፡ደርጎች ከስልጣን ተባረሩ፡፡ህወሓቶች ለህዝብ የቆሙ በመምሰል ህዝቡን አስታጥቀው ደርግን ከደመሰሱ በኋላ ግን ከስልጣንና ሃብት በስተቀር ለህዝብ ግድ የማያሰጣቸው መሆናቸውን አስመሰከሩ፡፡በማንኛውም ስሌት ስልጣን ከእጃቸው እንዲወጣ አይፈልጉም፤ አይፈቅዱምም፡፡


No comments:

Post a Comment