ትናንት ማታ አምሽቼ ነበር ከስራ የወጣሁት፡፡ከቢሮየ እንደወጣሁ ከለገሃር ወደ ፕያሳ የሚሄደው
ታክስ ወስጥ በሶስተኛ ወንበር ጥግ የዤ ተቀመጥኩ፡፡ታክስው ስላልሞላ ረዳት ሹፌሩ ውጭ ሁኖ እየተጣራ ነው፡፡አንድ ተሳፋሪ መጣና
እኔ ላይ ዘጭ አለብኝ፤ጋን ሙሉ አተላ የተደፋብኝ ነው የመሰለኝ፡፡የሰውየው ድፍረት ስላበገነኝ ‹‹ስሩ እንደተቦረቦረ ግንድ ትገነደስብኛለህ
እንዴ?›› ብየ ቀበቶ ማስታጠቅያው አከባቢ በክርኔ ጎሸምኩት፡፡አፈጠጠብኝ፡፡እኔም ወደ እርሱ ዞሬ አፈጠጥኩበት( ዓይኖቼ በጣም ደቃቃ
ስለሆኑ ስቆጣ የባሰ ወደ ውስጥ ስለሚገቡ አይታዩም፡፡ህፃን እያለሁ አብሮ አደጎቼ በዓይኖቼ ማነስ ይሳለቁብኝ ነበር፤ ባለቤቴም ስትበሽቅ
‹ጠምባር› ብላ ነው የምትሰድበኝ፡፡እንዲህ ስትለኝ ግን አልናደድም፤ አብሮ አደጎቼን ስለምታስታውሰኝ፡፡)
‹‹ይቅርታ›› አለኝ አፍንጫው የተፈነ በሚመስል አነጋገር፡፡ትንፋሹ ተከድኖ የከረመ ጋን ሙሉ
አተላ ያኔው የተከፈተ ይመስላል፡፡
ዝም ኣልኩ፡፡
በድጋሚ ‹‹ይቅርታ›› አለኝ፡፡ንዴቱ አሁንም ስላልበረደልኝ ሃይለ ቃል በተሞላ አነጋገር
‹‹ባክህ ዝምበል! ሰምቸሃለሁ›› አልኩት፡፡ይቅርታ በመጠየቁ ሳይሆን ከአፉ የሚወጣው ትንፋግ ስላስጠላኝ ነው ያልተለሳለስኩት፡፡ዝም
ብሎ አየኝ አየኝና ከአጠገቤ ተነስቶ እየተንደፋደፈ ረዳቱ የሚቀመጥበት ቦታ ላይ ሄዶ ወደቀ፡፡ታክሲው እንደሞላ ረዳቱ ገባና ‹‹ጀለስ
እዛው ዘጭ በይ›› አለው፤በሩ አከባቢ ከጋቢናው ወምበር በስተጀርባ ያለው አብዛኛው ጊዜ ትርፍ የሚጫንባት ቦታ ላይ እየጠቆመ፡፡‹‹እሺ››
ብሎ አየተወላገደ ሄዶ የተባለበት
ቦታ ተቀመጠ፡፡
ሰውየው ባለበት ሁኖ አሁንም አሁንም አንገቱን እያሰገገ ያየኛል፤ የሆነ ነገር ከራሱ ጋር እያልጎመጎመ፡፡ኋላ ላይ‹‹
ብታናግረኝ ደስ ይለኝ ነበር›› አለ፡፡ምንም አላልኩም፡፡‹‹እኔ ግን ብታናግረኝ ደስይለኛል›› አንገቱን አሰግጎ በጥያቄ መልክ ወደ
እኔ እተመለከተ ጠየቀኝ፡፡ ‹‹አሁን በጣም ሞቅ ብሎሃል፤አንተ አይደለህም እኮ›› አልኩት፡፡‹‹ቢሆንም ብንነጋገር ደስ ባለኝ ነበር፤
ሰው አይናቅም፤ ዘራፊ መሰልኩህ እንዴ?›› ጠየቀኝ፡፡እንድያ ሲል አሳዘነኝ፤‹‹ምን ብያጋጥመው ይሆን እስከዚህ ድረስ ጥምብዝ ብሎ
የሰከረው?›› ቅድም ስለ ጎሸምኩት ፀፀተኝ፡፡
‹‹እንካ አስር ብር ነው ያለኝ፤ ደግሞ ማንም እንዲከፍልልኝ አልፈልግም›› ብሎ ለረዳቱ ሒሳብ ሰጠው፡፡‹‹ቅርብ ወራጅ
ነኝ እሺ፤ቅርብ ወራጅ ንኝ›› አለ፡፡‹‹እሺ ጀለሴ›› መለሰ፤ ረዳቱ፡፡ቴድሮስ አደባባይ ስንደርስ ‹‹እዚሁ አውርደኝ፤ወራጅ!››
ብሎ ወረደና ‹‹እናትክን እንትን ትሁን›› ሲል ተሳፋሪው በሙሉ በሳቅ ፈረሰ፡፡እኔም በመጠኑ ሳቅኩ፤አልተቆጣሁም፡፡
No comments:
Post a Comment