Wednesday, May 1, 2013

ድንቅ ነሽ



ሉሲ በዓለም የምትታወቅበት ስሟ ነው።የሃገርዋ ልጆች ደሞ ድንቅ ነሽ ይሏታል።ከ3.2 ሚልዬን ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ተወለደች።አደገችና ለአቅመ ሄዋን ደረሰች፤ወለደች ከበደች፤ኖረች።በመጨረሻም በዓፋር ክልል ልዩ ስሙ ሃዳር በመባል የሚተወቀው አከባቢ ዓረፈች። ሃዳር ለ3.2 ሚልዬን ዓመታት የድንቅ ነሽ መካነ መቃብር ተሸክማ ኖረች።

ከ3.2 ዓመታት በኋላ የመጡ የቅሪት አካል አነፍናፊዎች ብዙ ጥናትና ምርምር በማካሄድ በ1966 ዓ.ም አጥንቷን ከተቀበረበት ቦታ ቆፍረው ሲያወጡት ዓይናቸው ማመን አቃታቸው። ተገርመው ዓለምን አስገረሙ። የዓመታት ልፋታቸው ውጤት የሆነውና ባልተለመደ መልኩ ሙሉ በሙሉ ሳይበላሽ የተገኘው አጥንትም የሴት መሆኑን ሲያውቁ ሉሲ ብለው ሰየሙት።ኢትዮጵያውያንም ቀበል አድረገው ድንቅ ነሽ አሏት።

የድንቅ ነሽ ሌላው አስደናቂ ነገር የተከሰተው ከአምስት ዓመታት በፊት ለጉብኝት ወደ ሃገረ አመሪካ ስታመራ ነበር።ብዙ ኢትዮጵያውያን «ከሞትና ከአመሪካ የሚቀር የለም» ይላሉ ይባላል። ይኸው ድንቅ ነሽም እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ምኞቷን እውን ለማድረግ ከብዙ ሚልዬን ዓመታት በኋላ ወደ አመሪካ አቀናች።የአመሪካ ግዛቶችን አካለለች፣ በ350 ሺ ሰዎች ተገበኘች። የጉዞዋ ዓላማ ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ የተለየ አልነበረም… ብር ሰብስቦ ወደ ሃገር ቤት መመለስ።

እማማ ድንቅ ነሽ ግን አንደ ሌሎች ኢትዮጵያውያን «ድያስፖራ» ሆና አልቀረችም።የነበራት የአምስት ዓመታት ቆይታ አጠናቅቃ ወደ ሃገሯ በሰላም ተመልሳለች። ታድያ እቺ 3.2 ሚልዬን የዕድሜ ባለፀጋ ከህይወት ተሞክሮዋና ከአመሪካው ጉብኝቷ ምን ተምራ፣ በምን ተማርራ፣ በምን ተደንቃ በምንስ ተጨንቃ ይሆን? በሚልዬን ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ አመሪካን ስትጎበኝ ኢትዮጵያውያን በየግዛቱ ፈሰው ስታያቸው ምን ተሰምቷት ይሆን? ሃዘን ወይስ ደስታ? ኩራት ወይስ ሕፍረት?

ኢትዮጵያውያን «ድያስፖራዎችስ» ምን ተሰምቷቸው ይሆን? የፖለቲካ ጥገኝነት በመጠየቅ እንደወጣች በለመቅረቷ ምን ያህል ተገርመው ይሆን? ከድንቅ ነሽ ልምድ በመቅሰም የሷን እግር ተከትለው የያዙት እውቀትና ገንዘብ ይዘው ወደ ሃገራቸው ይመለሱ ይሆን ወይስ እነሱም ከ3.2 ሚልዬን ዓመታት በኋላ አጥንታቸው ወደ በለፀገች ኢትዮጵያና ብሎም አፍሪካ ለጉበኝት እስኪላክ ይጠብቁ ይሆን? ከተንቀሳቃሽ አጥንት የሚሻሉበት መንገድ ለማሳየት ቁጠኝነቱን ይስጣቸው።

No comments:

Post a Comment