ዓለም ቁጥር ስፍር በሌላቸው ተከታታይ ፈተናዎች የተሞላች ነች፡፡በዚች ዓለም የማይፈተኑ ምናልባት ህይወት የሌላቸው ነገራት
ብቻ ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡በተረፈ ግን ህይወት ያለው ሁሉ በተለያዩ ዓይነት ፈተናዎች ይፈተናል፡፡የቻለ ህይወት ያዘጋጀችለት ፈተናዎችን
በማለፍ የተለያዩ ቁሳዊና መንፈሳዊ የህይወት ስጦታዎችን ተሸላሚ ይኖናል፡፡እንድ አንዶቹ የሁለቱም ፀጋዎች(ቁሳዊና መንፈሳዊ) አሸናፊ
ሲሆኑ ሌሎቹ ደሞ እንዱን ስጦታ ብቻ ሊያሸንፉ ይችላሉ፡፡ሁሉቱም ፀጋዎችን የማየት፣የመስማትና የማሽተት ዕድል ያላገኙ ደሞ አሉ፡፡እነዚህ
ምስኪኖች ህይወት ካቀረበችላቸው ፈተናዎች ለማንኛውም የለሽልማት ዓይነት የሚያበቃቸው ውጤት ያላገኙ ናቸው፤ በሌላ አባባል ወድቋል
ማለት ነው፡፡
አሁን ስለፈተና ለመፃፍ የተነሳሁበት ምክንያት በሃገራችን በመማር ላይ ያሉ ተማሪዎች ሁሉ የዓመቱ ወይም የተወሰኑ ዓመታት
የመጠቃለያ ፈተና በመውሰድ ላይ ስለሆኑ ነው፡፡የ10ኛና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ሃገራዊ ፈተናዎች እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡ የከፍተኛ
ተቋማት(የዩኒቨርሲቲ ) ተማሪዎችም የዓመቱ የመጠቃለያ ፈተና እየተፈተኑ ነው፡፡የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችም እንዲሁ አንድም
በዝግጅት ላይናቸው አልያም ተፈትነው ጨርሰው ሊሆን ይችላል፡፡እነዚህ ከአንደኛ ክፍል እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ የምንፈተንባቸው ፈተናዎች
ህይወት በሰው ልጅ አማካኝነት የምትፈትነን ዓይነት ፈተናዎች ሲሆኑ ማንም በትምህርት ዓለም ያለፈ ሁሉ ጠንቅቆ ያውቃቿል፡፡
እነዚህ ፈተናዎች በአግባቡ ያለፈ ከአንዱ ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ወደ ሚቀጥለው ደረጃ ይሸጋገራል፡፡ብሎም አስተማሪ፣ሃኪም፣ተማራማሪ፣አውሮፕላን
አብራሪ፣የሃገር መሪ ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ማለፍ ያልቻለውም በሌሎች የሙያ ዘርፎች ሊሳካለት ይችላል፡፡ዝሮ ዝሮ ግን በትምህርት
ዓለም የምንፈተናቸው ፈተናዎች በጣም ቀላልና ጥቂቶቹ የህይወት ፈተናዎች ናቸው፡፡ምክንያቱም በጋራ ተምረን በጋራ
የምንፈተንባቸው ዓይነት ፈተናዎች ስለሆኑ ጥያቄዎቹ ሲዘጋጁ የአብዛኛው ተማሪ ችሎታ ወይም ብቃ ከግምት ውስጥ ያስገቡ ስለሆኑ ነው፡፡በድጋሚ ተፈትኖ ማለፍም ይቻላል፡፡በተጨማሪም የማለፈያ ውጤቱ ሃገሪቷ በምታስቀምጠው ኮታ ከፍና ዝቅ ሊል ስለሚችል ያን ያህል አስቸጋሪ ላይሆን ይችላል፡፡እነዚህ ካልተሳኩም በንግድና በእርሻው ዘርፍ ሊሳካልን ይችላልና አሁንም ተስፋችን አይጨልምም፡፡
የምንፈተንባቸው ዓይነት ፈተናዎች ስለሆኑ ጥያቄዎቹ ሲዘጋጁ የአብዛኛው ተማሪ ችሎታ ወይም ብቃ ከግምት ውስጥ ያስገቡ ስለሆኑ ነው፡፡በድጋሚ ተፈትኖ ማለፍም ይቻላል፡፡በተጨማሪም የማለፈያ ውጤቱ ሃገሪቷ በምታስቀምጠው ኮታ ከፍና ዝቅ ሊል ስለሚችል ያን ያህል አስቸጋሪ ላይሆን ይችላል፡፡እነዚህ ካልተሳኩም በንግድና በእርሻው ዘርፍ ሊሳካልን ይችላልና አሁንም ተስፋችን አይጨልምም፡፡
በጣም አስቸጋሪው ፈተና
ግን ህይወት በምትባል ትምህርት ቤት የምንፈተንባቸው ፈተናዎች ናቸው፡፡ከእርግዝና እንጀምር ብለን ብንነሳ ራሱ አንድ ህፃን ለአቅመ
እርግዝና የሚደርሰው አንድ ወንድ በፆታዊ ግንኙነት ወቅት ከሚለቃቸው በቢልዮን የሚቆጠሩ የዘር ፈሳሾችን ቀድሞ በሴትየዋ ማህፀን
የነበረቸውን እንቁላል በመስበሩ ነው፡፡ሌሎቹ ግን ለሃጭ ብቻ ሆኖው ቀርቷል፤ የመጀመርያው የህይወት ፈተና ማለፍ አልቻሉምና፡፡ፈተናው
ግን በዛው አያቋርጥም፤ በእርግዝና ወቅትም ይቀጥላል፡፡የቻለ ጤነኛ ሆኖ ይወለዳል፤ ያልቻለ ግን ይጨነገፋል፡፡ፈተናው አሁንም እየቀጠለ
ነው፤ የቻለ ያድጋል… ለአቅመ ስም፣ለአቅመ አዳምና ሄዋን፣ ለወግ ለማዓርግ፣ለአቅመ ስልጣን ወዘተ ይደርሳል፡፡ያልቻለ ደሞ ገና በጧቱ
የሰናበታል … ታሪክ ሳይማርና ሳይሰራ!፡፡ታላቁ የውድቀቶች ውድቀት ታሪክ ሳይሰሩና ሳይማሩ በአጭሩ መቅረት ነው፡፡አንድ ሰው በጣም
ከባዱ ፈተና አልፏል ማለት የሚቻለው ደሞ መኖር ሲችል ብቻ ነው፡፡መኖር መቻል በራሱ እጅግ በጣም ብዙ ውጣ ውረዶችን ማለፍ የግድ
ይላል፡፡
በእርግጥ ህይወት የምታቀርብብን
የፈተና ዓይነቶች የተለያዩ ናቸው፡፡ለአንዱ በጣም ቀላል፣ለሌላው ደሞ በተቃራኒው በጣም ከባድ ሊሆን ይችላል፡፡አብዛኛው ሰው የሚመርጠው
ቀላሉን ፈተና ተፈትኖ በቀላሉ ለማለፍ ነው፡፡ለዛም ነው ብዙ ሰዎች ኩረጃ፣ሙስና፣ስርቆት፣ ማጭበርበር፣ ማታለል፣ የሌሎች ንብረት
በሃይል መዝረፍ፣ሌሎችን መጨቆን እስከ መግደል በሚደርሱ ወንጀሎች የሚዘፈቁት፡፡ውጤቱም እስረኛ መሆንን ያስከትላል… የህግ ወይም
የህሊና እስረኛ!፡፡በአንዱ ወይም በሁሉቱም መታሰር ደስታን ያሳጣል፡፡ድስታን ማጣት ጤናን ያሳጣል፡፡ጤና ማጣትም ሞትን ያስከትላል…
የሰው ልጅ ታላቁና የመጨረሻው ውድቀት፡፡
ጥቂቶች ግን በጣም ከባዱን ፈተና ወደውም ሆነ ተገደው ይፈተናሉ፡፡ከባዱን ፈተና
ያለፉ ህይወት ከሁሉም የላቀውን ሽልማት ትሸልማቿለች፡፡አዎ! የፈተናው መቅለልና መክበድ የሽልማቱን ዓይነትና መጠኑን ይወስኗል፡፡ከባድ
ፈተና ያለፈ ከባድ ሽልማት ይሸለማል፤ ቀላል ፈተና ያለፈ ደሞ ቀላሉን ሽልማት ይሸለማል፡፡ትንሹ ሽልማት በቁሳዊ ነገሮች ራስን መደልል
ሲሆን ታላቁ ሽልማት ደሞ ደስታን መቀዳጀት ነው፡፡ደስተኛ የሆነ ንሮ መምራት ነው፡፡ደስታን ለማግኘትና አግኝቶም ለመረዳት የሚቻለው
ደሞ ደስታን በሚያሳጡ ከባድ ፈተናዎችን እንደ ብረት ቀልጦ እንደ ዱቄት ተፈጭቶ ማለፍን የግድ ይላል፡፡ይህ ማለት በእሳት ሲቃጠሉ
አመድ ሳይሆን ብረትን መቁረጥ የሚችል ጠንካራ ብረት መሆን ማለት ነው፡፡እንደ በረዶ በሚያቀዘቅዝ ፈተና ሲፈተኑም በብርዱ ተቆራፍዶ
ቁጭ ማለት ሳይሆን በረዶውን አቅልጦ ወደ ውሃ መቀየርና በውሃው ላይ ዋኝቶ ዓሳ ይዞ መውጣት ማለት ነው፡፡
በዓለማችን ይህን ዓይነት
ፈተና ማለፍ የቻሉ ሰዎች በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ እነሱ ተፈትነው ያለፉት ዓይነት ፈተና ተፈትነን ማለፍ ሳይሆን ከፈተናው በኋላ
የተሸለሙት ገፀበረከት የኛ እንዲሆን የምንመኝ ግን ብዙ ነን፡፡ለምሳሌ ከ2500 ዓመታት በፊት በግሪክ የኖር የነበረው ሰቁራጠስን
እንውሰድ፡፡የተማረ ሁሉ የሰቁራጠስ ጀብድ የማያውቅና ልክ እንደሱ የተለየ ስብእና እንዲኖረው የማይመኝ የለም ማለት ይቻላል … አስተምህሮው
ከገባው ማለት ነው፡፡ እሱ ተፈትኖ ያለፋቸው ፈተናዎች ግን መፈተን የሚፈልግ የለም፡፡ ማን ነው ለህግና ለእውነት ራሱን አሳልፎ
መስጠት የሚደፍረው! ማን ነው ለእውነት ብሎ ሄምሎክ እንደ ቡና ተጎንጭቶ የሚወዳት ህይወቱን አሳልፎ የሚሰጠው! ማንም አላየንም፤
አልሰማንም፡፡
አገሩን በሃይል ወረው፣
ወገኖቹን ለባርነት የዳረጉበት ጭራቆችን በፍቅር አሸንፎ ከሃገሩ በማባረር ወገኖቹን ነፃ ያውጣው ማህተመ ጋንዲን የሚወዳደር ጀግና
አለ ማለት ያስቸግራል፡፡የሱ ትእግስት ግን ማንም ሊታገሰው አይችልም፡፡ሲያስሩት ሲያንገላቱት፣ሲገርፉት ሲያሰቃዩት እስራቱን በማሰር፣
ስቃዩን በማሰቃየት አልተበቀለም፡፡የባሰውን ራሱን በማሰቃየት ነበር ጠላቶቹን ታግሎ ማሸነፍ የቻለው፡፡የሱ እስራት፣ግርፋት፣ራብና
ስቅያት እንዲደርስበት የሚፈልግ ባይኖርም የሱ ስምና ዝና የሚመኘው ግን በጣም ብዙ ነው፡፡
የማርቲን ሉተር ኪንግ
ፈተናዎችን ተፈትኖ ለማለፍ ዝግጁ የሆነውስ ማን ይሆን!በእርግጥ ማርቲን ሉተር የፈተናው ውጤት ለማየት የታደለ አይመስለኝም፡፡ ነገር
ግን ስቃዩን ሳይሰቃይ፤ ሞቱን ሳይሞት አሁንም የሱ ስምና ዝና የማይመኝ አለ ለማለት ይከብዳል፡፡ከመቃብር በላይ የተወው ስምና ዝና
በህይወት ያሉ ሊደርሱበት አልቻሉም፡፡ህልማቸውን እውን ለማድረግ ውድ ህይወታቸው ለመክፈል የተዘጋጁ ጥቂቶች ብቻ ናቸውና፡፡
ኔልሰን ማንዴላ ለ27
ዓመታት በአፓርታይድ አምባገነኖች ታስሮ አብዛኛው የወጣትነት ዕድሜውን በሮቢን ደሴት በሚገኘው እስር ቤት አሳልፏል፡፡ከእስር ቤት
ከተፈታ በኋላ ግን የደቡብ አፍሪካ የመጀመርያው ጥቁር ፕረዚደንት ለመሆን በቅቷል፡፡በዓለም አቀፍ ደረጃም የጀግንነት ተመሳሌት ሆኗል፡፡በሰላም
ታግሎ ጠላቶቹን ማሸነፉ ብቻ አይደም ማንዴላን ልዩ ሰው የሚያደርግው፡፡ ከሌሎች አፍሪካውያን መሪዎች በላይ የሚያደርገው ያን ያህል
ዓመታት ታግሎ ያገኘው ስልጣን ለሌሎች አሳለፎ መስጠት መቻሉን ነው፡፡ተዓምር እኮ ነው! ሌሎች መሪዎች ወንደሞቻቸውና ጓደኞቻቸውን
ገድለው ስልጣን ይቀማሉ፤ ህዝባቸውን ይጨቁናሉ… ይጨፍጭፋሉ፤ ለአሰቃቂና አሰፋሪ ድህነትና ኋላ ቀርነት ይዳርጋሉ፡፡ ማንዴላ ግን
ለ27 ዓመታት ታግሎ ያገኘው ስልጣን ለሚወደው ህዝቡ በደስታ አስረከቧል፡፡ያን ያደረገው እንደሌሎቹ የአፍሪካ መሪዎች በአቋራጭ የስልጣን
ርካብ ባለመጨበጡ ነው፡፡በብዙ ፈተናዎች ተፈትኖ በደረሰበት ደረሰ፤ሌላ ብዙ ተጉዞ መውጣት የሚገባው ተራራ መኖሩን በማወቁ በእጁ
የያዘውን ለሌሎች አስረክቦ ወደፊት ገሰገሰ፡፡አዎ! ለዛም ነበር ‹‹በህይወት ዘመኔ ብዙ ተጉዤለሁ፤ ብዙ ተራራዎችም ወጥቻለሁ፤ ብዙ
ተራሮችን በወጣሁ ቁጥር ግን ሌሎች ብዙ ተራሮች መኖራቸውን ነው የተማርኩት›› ያለው፡፡ለዛም ሳይሆን አይቀርም ከአፍሪካውያን ሁሉ
በተለየ ለ94 ዓመታት በላይ ለመኖር የታደለው፡፡ግን ማናችን ነን ለ27 ዓመታት በአሰቃቂ ሁኔታ ታስረን ለነፃነት የምንታገለው!?
ታላቁ መፅሐፍ ቁዱስ
‹‹በፈተና ያለፈች ህይወት ጣፋጭ ነች›› ይላል፡፡በእውነት ከጣፋጭም ጣፋጭ ነች፡፡የህይወት ተከታታይ ፈተናዎች ማለፍ ትእግስተኛ
ያደርጋል፡፡ የለመዱት ወገን ዘመድና፣ ያደጉበት ቀዬ ለቆ ወደ ሩቅ ለመሰደድ የሚያስገድድ ሁኔታ ቢያጋጥምም ችግሩን ለመቆጣጠር እንድንችል
ይረዳናል፡፡በበሽታ፣በራብ፣በባርነት፣በእስራት፣በጭቆና… ማለፍ ግድ የሚልበት ጊዜ ሊኖር ይችላል፡፡እነዚህ ዳገት ቁልቁለቶች አልፎ
ግን ሰጥ ያለ ለምለም መስክ ይገኛል፡፡ ችግሩ እዛው ለመደረስ የሚያስችል ትእግስት አለን ወይ ነው፡፡ያላቸው ደርሰውበታል፤ለመድረስ
የተቃረቡም ይኖራሉ፡፡ያልቻልን ግን የሽልማቱ ተቋዳሽ መሆን አንችልም ማለት ነው፡፡በሌላ አገላለፅ ከሁሉም በላይ የሆነውን የህይወት
የምስክር ወረቀት(ISO certificate) ማግኘት አልቻልንም ማለት ነው፡፡ታላቁ የንሮ ሰርቲፊኬት የምናገኘው በህይወት ዘመናችን
መቋቋም በቻልናቸው ይንሮ ቁስሎች መጠን ነው፡፡ብዙ ቆስለን፤ መላ አካላችንና አእምሯችን ተላልጦና ተጋግተጦ ከዳነ በኋ በሚኖረን
የበሰላ መጠን ነው የኛ የህይወታችን የምስክር ወረቀት ውድነት የሚመዘነው፡፡ማንነቱን በብዙ የህይወት በሰላዎች ዥንጉርጉር የሆነው
የብዙ የምስክር ወረቀቶች ተሸላሚ ይሆናል፡፡ይህ ማለት ለመኖር ብቁ መሆኑን ያስመሰክራል ማለት ነው፡፡
ይህ የህይወት የምስክር
ወረቀት እንደ ሌሎቹ ሰው ሰራሽ ሰርትፊኬቶች ተኮርጆ ሊሰራ አይችልም፡፡ማንም ሰው አስመስሎ ሊሰራው ቢሞክርም አሳካለትም፡፡የህይወት የምስክር ወረቀት የተሸላሚው ብቻ
ነው፡፡
የስነ ህይወት ሊቁ
ቻርለስ ዳርዊን የመኖር ብቃት(survival of the fittest) ብሎ የሰየመው ይህንኑ የህይወት ታላቁ የምስክር ወረቀት ይመስለኛል፡፡ለመኖር
ብቁ የሆኑ ሰዎች ሳይበርያም ይህዱ ዳሉል መኖር አያቅታቸውም፡፡ለመኖር ብቁ ስለሆኑ ወደበረዶነት የሚቀይር ብርድም ሆነ እንደ ቅቤ
የሚያቀልጥ ሙቀት አይበግራቸውም፡፡የህይወት ጠባሳዎችን ተቋቋሞው ለማሸነፍ ይኖራሉ፤ለመኖርም ያሸንፋሉ፡፡የአሸናፊዎች ብቃት የሚለካው
በጊዜያዊ ቲፎዞዎች ብዛት ሳይሆን ህይወት ራሷ በምትሰጣቸው በዓለም አቻ ይማገኝለት ልዩ ሽልማት ብቻ ነው፡፡ያኔ ደሮ ይጠሏቸው የነበሩ
ሰዎችም እንደ ጣኦት ያከበሯቸዋል፤ለመስገድም ይቃጣቸዋል፡፡በሌሎች ተገድደው ወይም በጥቅም ተደልለው ሳይሆን በገዛ ስሜታቸው ሰለሚያስገድዳቸው ብቻ ነው፡፡
ስለሆነም ነው ማንኛውም
ዓይነት የህይወት ፈተና በትዕግስት፣ በጥንካሬ፣ በብረታትና ለሌሎች ተምሳሌት መሆን በምንችልበት መልኩ ጥርሳችን ነክሰን ማለፍ ያለብን፡፡የራሳችን
ፈተና በራሳችን መስራት ስንችል ብቻ ነው የተረጋጋ፣ጤነኛና ደስተኛ ንሮ መምራት የምንችለው፡፡ካልሆነ ግን ከሌሎች በመኮረጅ የኩረጃ
ንሮ ለመምራት እንገደዳለን፡፡ዓረቦችን ስናይ ዓረብ፣የሩቅ ምስራቅ ሰዎችን ስናይ የሩቅ ምሰራቆቹን፣ምዕራባውያን ስናይ ደሞ ምዕራባውያንን
ለመምሰል የምንፍጨረጨረው በራሳችን ልዩ ማንነት መተማመን ስለማንችል ነው፡፡አንዴ ወደ ምዕራብ ሌላ ጊዜ ደሞ ወደ ምስራቅ እጃችን
ለእርዳታ የምንዘረጋው የራሳችን እምቅ ሃብት በራሳችን ጉልበትና ጥበብ ተጠቅመን ራሳችን ማሳደግ ስላቃተን ነው፡፡በራሳችን ሰለማንተማመን
ነው የውጭ ኢምባሲዎች ከትብያ አንስተው በስልጣን ርካብ ላይ እዲያቆናጥጡን የምንማልደው፡፡በራሳችን ልዩ ማንነት ተማምነን እኛ በመረጥነው
መኖር የምንችለው ግን በራሳችን አኗኗር መኖር እንደምንችል ስናውቅ ብቻ ነው፡፡ይህን የሚያረጋግጥልን ደሞ የራሳችን ፈተና ራሳችን
ሰርተን ብቃታችን ስናረጋግጥ ብቻ ነው፡፡
በህፃንነታችን መንከባለሉን
ትተን መንፋቀቅ፣ መንፋቀቁን ትተን፣ ተንከርከር ማለቱን… መውደቅ መነሳቱን፣ ይህንንም አልፈን መሮጥ ባንጀምር ንሮ እንደ እባብ
በሆዳችን እየተሳብን በኖርን ነበር፡፡ለመናገር ባንኮላተፍና አንዱን እየጣልን ሌላውን እያነሳን ክፉና ደጉን ለማወቅ በተግባር ተፈትነን
ባናልፍ ንሮ እንደ እንስሳት ሳርቅጠሉን እየበላንና በቁማችን እየተፅዳዳን በኖርን ነበር፡፡የሰው ልጅ ፈተና ፈርቶ እጁና እግሮቹን
አጣጥፎ ቁጭ ቢል ንሮ ዛሬ ከዋሻ ወጥቶ ተአምረኛ የሆኑ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ወጤቶችን ባለቤት መሆን አይችልም ነበር፡፡ ‹‹ሰውን
ሰው ያደረገው ስራ ነው፡፡›› የስራው ትክክለኛነት የሚታወቀው ደሞ በፈተና ብቻ ነው፡፡
እናም ለትክክለኛ ስራ፣ለእውነተኛ
ማንነት፣ ደስተኛና ጤነኛ ህይወት ለመምራት ፈተናን እንውደድ፤ኩረጃን እናስወግድ፡፡ሙስናን እናጥፋ!! ሰርተን፣ ጥረነ ግረን በህይወት
ተፈትነን ማንነታችንን እናስመስክር ፡፡ተንኮል፣ምቀኝነት፣ጭፍን ጥላቻና ዘረኝነትን እንፀየፍ፡፡ከሁሉም በላይ ደሞ ጥገኛ አስተሳሰብን
መጥላት ይጠበቅበናል፡፡እነዚህ ሁሉ ፈተናን በማይወዱ ግለሰቦች የሚዘወተሩ የደካሞች መለያ ናቸውና፡፡‹‹ወደ ፈተና አታግባኝ›› ብለን
መፀለዩን ትተን፣‹‹ሸክላ የሚጠነክረው በእሳት ተጠብሶ ነው፤ ወርቅም ወርቅ የሆነው በእሳት ተፈትኖ ነው›› በማለት በህይወት እሳት
ተፈትነን ህይወት ያዘጋጀችልን ሽልማት ለመውሰድ እንሸቀዳደም፡፡
No comments:
Post a Comment