ከፈረንጆች ጋር ቢኖር:-
ነገሩን አቅልሎ
ቆዳቸው ቢነጣም ሰዎች ናቸው ብሎ
ጥቁረቱን አይተው ጥቀርሻ ነህ አሉት
ከሰው አሳንሰው ከዝንጀሮ መደቡት፡፡
ከዓረቦች ጋር ቢኖር:-
በባህል በታሪክ ተሳስረናል
በሃብት በእምነት ማን ይለያየናል
የሚል ግምት ይዞ
ሰርቶ እንዲያልፍለት ህይወቱን አስይዞ
ጥፋልን ሐበሻ
የድህነት ማጣቀሻ
ብለው ሲጮኹበት
አስረው አስቃይተው
የልፋበትን ቀምተው
በአሸዋው ላይ ጥለው
ልሃጭ ሲተፉበት
ቆሽቱ ተቃጠለ የሚለው ጠፋበት፡፡
ከኢትዮጵያውያን ጋር ቢኖር:-
በዘር በሃይማኖት፣ በባህል በእምነት
በስጋ ዝምድና፣በመልክ በቁመና
በናት ሃገር ታሪክ አንድ ናቸውና
ያላቸው አንድነት ውስጡን አሳምኖት
ዘራቸው ቢመዘዝ ከትግራይ ቢሆንም
‹‹ትግሬ›› ነህ ብለው ከዱት ወንድሞቹም፡፡
ከተጋሩ ጋር ቢኖር:-
በአንዲት የናት ጓዳ
በሰፈር፣በቀበሌ፣ በዞን በወረዳ
ከፍለው ከፋፍለው አደረጉት ባዳ፡፡
በሄደበት ሁሉ ባእድ ሲያደርጉት
እንግዳ ሆነበት የራሱ ማንነት፡፡
ግን ከሁሉም በላይ በጣም ያስመረረው
የሐበሻ ጠላት ሐበሽ መሆኑን ነው፡፡
No comments:
Post a Comment