የማንኛውም ነጋዴ ዋና ግብ ትርፍ ነው፡፡ትርፍ ለማግበስበስ ደሞ ሌሎች ነጋዴዎችን በልጦ መገኘት አለበት፤ ከተቻለም ከገበያ
ውጪ ማድረግ አለበት... በተለይ በካፒታሊዝም ስርዓት፡፡ካፒታለዝም በነፃ ገበያ ስም በማንኛውም መንገድ ተወዳድሮ ማሸነፍና ትርፍ
ማግበስበስ ይጠይቃል፡፡በሚያገኘው የትርፍ መጠን የንግዱ አድማስ እየሰፋ ሲሄድ ለደምበኞቹ ያለው ተደራሽነት ምንያህል ሰፊ መሆኑን
ማስታወቅያ በማስነገር ገበያው እንዲሰፋለት ይጥራል፡፡ በማስታወቂያ የሚነገረው ከልክ በላይ ግነት የተሞላበት የጥራትና የአገልግሎት
መግለጫ ግን በመሬት ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን ይታወቃል፡፡
በጣም የሚገርመውና በማስታወቂያ የሚደረገው ማጭበርበር
የሚፀመው ግን የነጋዴው ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ሲሄድ ነው፡፡ በተለይም በተለያዩ የንግድ ዘርፎች የተሰማሩ የአዲስ አበባ
ነጋዴዎች በገበያ ድርቅ ሲመቱ የሚያደርጉት ማስታወቂያ ዘመቻ በጣም ያስገርመኝ ነበር፡፡የልብስ ነጋዴዎች(በለቡቲኮች) ገበያ ሲያጡ
‹‹ታላቅ ቅናሽ!›› የሚል ማስታወቂያ ይለጥፋሉ፡፡በቅናሹ ለመጠቀም
ወደ የገበያው መዕከል ጎራ ብትል ግን አንድ በእጥፍ ጨምሮ ይተብቅሃል አልያም የሚሸጠው ልብስ ሰልባጅ ሆኖ ታገኘዋለህ፡፡
ምግብ ቤቶች፣ካፌና ሬስትሯነቶችም እንዲሁ ‹‹...በዓዲስ መልክ ማቅረብ ጀምረናል!›› የሚል ማስታወቂያ ይለጥፉና ስትጎበኛቸው
ከዋጋጭማሪ በስተቀር ምንም ለውጥ እንዳለመጡ ትገነዘባለህ፡፡ተጠቃሚው እንዲህ እንዲህ ያሉ ነገሮች ሲደጋገሙበት ከተወሰነ ጊዜ በኋላ
በውስጡ ‹‹ነቅተንባችኋል!›› በማለት በድጋሚ በአጠገባቸው አያልፍምና ይከስራሉ፡፡በዚህ ጊዜ የሚኖራቸው አማራጭ አንድም የንግዱ
ዓይነት መቀየር ነው አልያም በማይታወቁበት አከባቢ ሄደው መነገድ ነው፡፡ አብዛኞቹ ገበያውን በማጥናት ምንይዘው ቢቀርቡ ገበያተኛው
ሊሸምታቸው እንደሚችል አያውቁም(አይፈልጉም)፡፡
እንድ አንዶቹ ነጋዴዎች ደሞ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ አቋራጭ ለመበልፀግ ይሯሯጣሉ(በሙስናና በኮንትሮ ባንድ)፡፡በሚያቀርቡት አገልግሎት ወይም በሚሸጡት እቃ ገበያተኛው
ይጠቀም ይጎዳ አያገባቸውም ... ዋና ዓላማቸው ትርፍ ማግኘት ነውና፡፡እነዚህ ነጋዴዎች ትርፍ ካገኙ የግላቸው የልፋትና የብልጠት
ውጤት ነው፡፡ ከከሰሩ ግን መንግስትን ይወቅሳሉ፤ ሃገርና ህዝቡንም ይራገማሉ፡፡
ይህ ተስፋ የመቁረጥና
‹‹የከሰረ ዓረብ›› የመምሰል አባዜ በነጋዴዎች ብቻ የሚታይ ሳይሆን በፖለቲከኞችም እየተለመደ መጥቷል፡፡አብዛኞቹ ፖለቲከኞች የደገፋቸውን
እንደ ፃድቅ፣ሃገር ወዳድ፣ሊቅ ወዘተ ሲቆጥሩት የሚቃወማቸውን ደሞ ባንዳ፣አላዋቂ፣ዘረኛ ወዘተ የሚሉ ታፔላዎች ይለጥፉባቿል፡፡
የመንግስት ደጋፊ ወይም
አባል ለሆነው፣ መንግስት የሚያስፈፅማቸው ሃገራዊ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን የሚደግፍ ካደሬ ነው፤ ወያኔ ነው፤ አላዋቂ ነው፤የአምባገነኖች
ተባባሪ ነው፡፡ ምንም እውቀት የሌለውና ነገሮችን መገንዘብ የተሳነው ተብሎ ይፈረጃል፡፡በተቃዋሚዎች እይታ አባይን ገደብ ማለት ገዢውን
ፓሪቲ እንደመገደብ ይቆጠራል፡፡ ለአባይ ግደብ ቦንድ መግዛትም ለሙሰኛው መንግስት ስጦታ እንደ ማበርከት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡የነአቡነ
ጴጥሮስ ሀወልት በባቡር መስመር ግንባታ ምክንያት ለጊዜው መነሳት የሃገር ሰማእታትና አርበኞችን እንደመዳፈር ይቆጠራል፡፡በአጠቃላይ
ከሃገር ውጭም ሆነ በሃገር ውስጥ የሚገኙ ተቃዋሚዎች ስልጣን እስካልያዙ ድረሰ ሙሰኞችንና ሌሎች ውንጀለኞችን ማስር፣ትላልቅ ፕሮጀክቶችን
ነድፎ ለተግባራዊነታቸውን መንቀሳቀስ፣ ሃገርን ማሳደግ፣ልማታዊ ባለሃብቶችና ገበሬዎችን ማበራታታት አንድም ቅጥፈት ነው አልያም ወንጀል
ነው፡፡ ለተቃዋሚዎች ‹‹ወደ አፍ›› ከሚገባው ‹‹ከአፍ የሚወጣው›› መቅደም አለበት፡፡ነገር ግን ካልገባ ከየት ሊወጣ እንደሚችል
አይታወቅም፡፡
በተለይ ግን ‹‹ካድሬ››
የምትሏን ቃል ከከሰሩ ፖለቲከኞች የምትሰነዘር ነች፡፡የማሳመን ብቃት ካላቸው የዛሬው ካድሬ የነገው አባላቸው ሊሆን እንደሚችል አያውቁም፡፡‹‹ካድሬ፣
ካድሬ›› ሲሉትም እነሱን ባለመደገፍ ሊይጠፋቸው እንደሚችል አይገባቸውም፡፡ በራሳቸው ድክመት ደጋፊ ሲያጡና ሳይመረጡ ሲቀሩ ተወዳዳሪያቸው
የሆነውን ገዢው ፓርቲን መክሰስ ይቀናቸዋል፤ ይራሳቸው ስንፍና ግን አይታያቸውም፡፡አብዛኞቹ የሃገራችን ተቃዋሚዎች አንድም ገንዘብ
ለማግኘት ከተሳካ ደሞ ገንዘብም ስልጣንም ለመጨበት አቅጣጫ ሳይጠይቁ እንደ ጅብ የሚሮጡ የራኢ ድሆች ናቸው፡፡ጅብ የቀበሮ አጎት
ነው ይባላል፡፡ እናም አንድ ቀን አያጅቦ እሚበላው ሲያጣ ለወራት ረስቶት ከከረመው አጥንት ጋር እየታገለ ቀበሮ አገኘችውና ‹‹አጎቴ
አንተ ከተጣለ አጥንት ጋር ትታገላለህ እዛ እኮ ስጋ አለልህ፡፡›› ስትለው የት መሆኑን ሳይጠይቃት በሩጫ እግሩ ወደ መራው ሮጠ
ይባላል፡፡የሃገራችን ተቃዋሚዎችም ስልጣንና ገንዘብ አለ ስለተባሉ ብቻ ‹‹እንዴት ይገኛል?››፣‹‹የት ይገኛል?››ና ሌሎች ጥያቄዎችን
ሳያጣሩና ሳይመልሱ ዝም ብለው በደመነፍስ ይሮጣሉ፡፡
ድሮ ገዢው ፓርቲ በእንትን
ፕርሰንት ሃገር እያሳደግን ነው ሲል፡፡ ውሸት ነው! እድገቱ የት አለ ይሉ ነበር፡፡ አሁን ደሞ ክህደቱ እንደማያዋጣቸው ሲያውቁ
ጊዜ ‹‹ከእድገት በፊት ነፃነት ይቅደም›› በማለት መጮኽ ጀምሯል፡፡ድሮ ምንግስት ሙሰኛ ስለሆነ ሙሰኞችን በህግ ፊት ማቅረብና ብሎም
መቅጣት አይችልም ሲሉ ነበር፡፡ሰሙኑን በታሰሩ ከ50 በላይ ተጠርጣሪዎች እየተሰጠ ያለው አስተያየት አስቂኝ ነው፡፡ አሁን ደሞ አንድ
አንዶቹ ‹‹ቲያትር ነው፣መጠላለፍ ነው›› ወዘተ በማለት እያጣጣሉት ይገኛሉ፡፡አብዛኛው ህዝብ ግን መንግስ ይህ ተግባሩን እንዲገፋበት
የሚፈልግ ይመስለኛል፡፡
እስኪ የሃገራችን ትላልቅ
ተቃዋሚ የፖለቲካ መሪዎች ምን እንዳሉ እንመልከት፡፡
“ኢህአዴግም እንደ
ድርጅት ሙሠኛ ነው” ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ -የመድረክ አመራሮች አባል
“ይሄ የዶሮ ትራፊ
ነው፤ ትልቁ ገንዘብ የት ነው ያለው?” ኢ/ር ሃይሉ ሻውል
“አሣ ማጥመጃው ትልልቅ
አሣዎችን የሚያጠምድ ከሆነ እንተባበራለን” ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማሪያም
“ገቢዎች ከመንግስትም
በላይ ስልጣን የተሰጠው አካል ነው” አቶ ሙሼ ሠሙ - የኢዴፓ ሊቀመንበር
ምንጭ: አዲስ አድማስ
እነዚህ ፖለቲከኞች
ሙሰና የባህላችን ምንጭ መሆኑን ያውቃሉ ነገር ግን እውነትን ለመቅበርና በገዢው ፓርቲ ለማላከክ ሲሉ ብቻ ህሊናቸው የማይፈቅደው
ነገር ይናገራሉ፡፡ሙስና በሃገራችን የተንሰራፋው በርስተ ጉልታዊው ስርዓት ነው፡፡ ያኔ ‹‹የእጅ መንሻ››፣‹‹ጉቦ›› ወዘተ መስጠት
እንደ ግዴታ ይቆጠር ነበር፡፡‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› የሚባለው አባባለም ከድሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣብን መሆኑን ይታወቃል፡፡ቆይ
ዛሬስ ቢሆን እንዚህ ተቃዋሚዎች በስራ ዓለም የሉበትም ማለት ነው? ታድያ ሁሉንም ደምበኞች በእኩልነት ነው የሚያስተናግዱት?
መንግስት ይህን እያወቀ
በሙስና ላይ መካሄድ የነበረበት ውግያ አላከናወነም ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ጀምሮታልና እንዲቀጥልበት ድጋፍ መስጠት ግን አስተዋይነት
ይመስለኛል፡፡ሙስና የመልካም አስተዳደር እጦት ቢሆንም ስር የሰደደ ሃገራዊ ችግር ስለሆነ ተቃዋሚ ደጋፊ ሳንል ልንዋጋው ይገባል፡፡

No comments:
Post a Comment