Wednesday, May 8, 2013

የፋሲካ ዋዜማ



ገና በጥዋቱ ሐሳብ ተፈናጠጠብኝና ልክ እንደ ሰጋር ፈረስ ወዳሻው ይነዳኝ ጀመር፡፡ወዴት መሄድ እንደምፈልግ አላውቅምና ታክሲ መያዙ አላስፈገኝም፡፡ተሽከርካሪው እኔ አሽከርካሪው ሐሳብ ... በሕልሜ የምጓዝ ነበር የሚመስለኝ፡፡ የአዲስ አበባ ህዝብ ለበዓለ ፋሲካ የሚያስፈልገው ሁሉ ለመግዛት ላይና ታች ይባዝናል፤ይወጣል፣ ይወርዳል፡፡
እኔም ሀላፊ አግዳሚውን፣መጪና ሄያጁን እያየሁ ከሁሉም አቅጣጫ ወደ ማንኛውም አቅጣጫ ከሚተመው የህዝብ ማዕበል ጋር የሐሳብ ወጀብ ወድያ ወዲህ ያንሳፍፈኛል፡፡አዲስ አበባ እንግዳ ሆነችብኝ፡፡መነሻየ እንጂ መድረሻየን አላውቀውም፤ ምናልባት ጉዞየ በድካም ሊገታ ይችላል፡፡

ከጥዋቱ በአራት ሰዓት ወደ መርካቶ አቀናሁ፡፡ጎጃም በረንዳን አልፌ ይርጋ ሃይለ ህንፃ ስደርስ የመርካቶ ትርምስ ዋጋ ሊያስከፍለኝ እንደሚችል ስለገባኝ በሱማሌ ተራ አድርጌ ወደ ፕያሳ አመራሁ፡፡ የፕያሳ ጎደናዎችም በሰው ተጥለቅልቋል፡፡በየመንገዱ የተለያዩ እቃዎች ዘርግተው የሚሸጡ ወጣቶች በሰው ብዛት የተጣበበው መንገድ የባሰ ዘግተውታል፡፡በተለያየ የድምፅ ‹‹ በምስት ብር ብቻ፣ በአስር ብር በቻ፣ በሃምሳ ብር፣ በመቶ ብር ብቻ እንዳያመልጦ...›› እያሉ ይጮኻሉ፡፡

ከልክ በላይ የተጫኑ መኪኖች ክላክስ እያሰሙ ክንፍ አውጥተው ለመበረር የሚቃጣቸው የሚስላል፡፡በግ፣ደሮ፣ፍሪጅ፣ቴሌቪዥን፣የኤሌትሪክ ምድጃ ወዘተ. በጥድፍያ ያጓጉዛሉ፡፡ የአዲስ አበባ ህዝብ፣‹‹ ከአሁን በኋላ ገበያ ስለማይኖር የሚያስፈልጋቹ ሁሉ ዛሬ ሸምቱ›› የሚል አስገዳጅ አዋጅ የተላለፈበት ይመስላል፡፡የእቃው ዋጋ በእጥፍ ቢጨምርም እንደ ህፃን ልጅ ያየውን ሁሉ ይሰበስባል፡፡

በኢትዮጵያ ስኒማ አድርጌ በመብራት ሐይል ህንፃ በኩል ወደቀኝ ታጥፌ ቁልቁል ወረዱክ በአቋራጭ ወደ አራት ኪሎ ለመሻገር፡፡ ከእሪ በከንቱ ከፍ ብሎ የተሰራው አዲስ ድሊ ከመደረሴ በፊት ከኮንዶምኔም ቤቶቹ ትንሽ ወረድ ብሎ  አንድ ያደፈ ብትቶ ለብሶ በስፓልቱ  ላይ ተኝቶ በብርድ የሚንቀጠቀጥ ጎደና አደር ተመለከትኩ፡፡የብርድና ፀሐይ እየተፈራረቁ ክሰል አስመስለውታል፡፡ ፊቱ በተንዠረገገ ፂም ተወሯል፡፡ያረሱ ፀጉር ከርዳዳና የተንጨፋረረ ነው፡፡ እንደ ሌሎቹ ጎደና አደሮች አልፈው መሄድ አልቻልኩም፡፡ እጄ ወደ ኪሴ በመላክ ዝርዝር ሳንቲም የኖረኝ እንደሆነ ፈለኩኝ፡፡ አልነበረኝም፡፡ አንዲት ብር አውጥቼ ጣልኩለት፡፡

ብሯን አፈፍ አድርጎ ድንገት ተስፈንጥሮ ብድግ ሲል በድንጋጤ ክው አልኩኝ፡፡ነገር ግን የእኔን ድንጋጤ ከመጤፍ አልቆጠረውም፡፡ ምንም ቃል ሳይተነፍስ በአቅራብያ ወደ ሚገኘው ሱቅ እየተንደረደረ ሂዶ ሲጋራ ገዛና በጥድፍያ ያጨስ ጀመር፡፡የሐሳብና የእግር ጉዞየን ለግዜው ገታ የሰውየው አኳሀን በተመስጦ መከታተሉን ቀጠልኩበት፡፡በአፉና በአፍንጫው እየተግተለተለ የሚወጣው የሲጋራ ጭስ የሰውየው በእሳት የተያያዘ ገለባ የሞላ ዋሻ አስመስሎታል፡፡

እውነት ግን ያሁላ ጭስ የሲጋራው ይሆን? ምናልባት ግን በችጋርና በመከራ በዛት ከተቃጠለው ውስጣዊ ማንነቱ የሚወጣ ጭስ ሊሆን ይችላል፡፡ለወጉ የለበሰው ብትቶና ቆዳው ክሰል የመሰለው እንዲሁ ነዶ ተቃጥሎ ስላለቀ ይሆናል፡፡እንዴትስ አይቃጠል!
ይህን እያወጣሁ እያወረድኩ ሳለ የአዲስ አበባ ፎቆች ጫፍ ከደመና ጋር የተገናኘ መሰለ፡፡ቅዝቃዜው በጣም ጨምሯል፡፡ ካፍያ ጀምሯል፡፡ የአራት ኪሎ ጉዞየን ሰርዠ ሽቅብ ወደ ፕያሳ ተመለስኩ፡፡ ጀነቭ ካፌ ፊት ለፊት ስደርስ ዝናቡ ለቀቀው፡፡ የስቅለት ቀን ነበር፡፡ዕለተ ዓርብ፣ሚያዝያ 25 ቀን 2005 ዓ.ም ክርስትያኖች ምንም ሳይቀምሱ በየአብያተ ክርስትያናት እስከ የምሽቱ 12 ሰዓት ድረስ እየሰገዱ የሚውሉበት ቀን፡፡ታድያ ዝናቡ እንዲህ የለቀቀው የእየሱስ ክርስቶስ መሰቀል ትዝ ብሎት እያነባ ነበር ማለት ነው?

ወደ ጀነቭ ካፌም እሱን አልፎ ወዳለው በቅላባ ቤትም አልገባሁም ተሳስቼ ስግደቱን ሳያልቅ እንደልበላ ስለፈራሁ፡፡ ዝናቡግን ፋታ የሚሰጥ አልነበረም፡፡ ስለሆነም፣ ወደ አፍሪካ ኮፊ ገብቼ በአንዱ ከኔ የሚረዝም ጤረጴዛ ቆሜ በቢቢሲ ቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ‹‹hardtalk›› መመልከት ጀመርኩ፡፡ ሰዎች ይበላሉ፣ይጠጣሉ... እንደ ጉድ፡፡ፆም የለም ማለት ነው?
ዝናቡ ለግማሽ ሰዓት ያህል ሲዘንብ ቆይቶ ፀጥ ሲል በጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ድርጌ ወደ ቤቴ አመራሁ፡፡

No comments:

Post a Comment