ሰብሳቢው ማን ነው?ክራይ ሰብሳቢ አይደለም፡፡ሊሆን የሚችልበት ዕድል ቢኖርም ገና በሕግ አስከባሪዎች
አልተጠየቀም፤ አልተፈረደበትም፡፡ገስጥ አስታጥቄ ይባላል፤ በአንዱ የፌደራል መስራቤት ማናጀር ሆኖ እየሰራ ይገኛል ፡፡ቆሞ ሲመለከቱት
በጣም ቀጭንና ረዥም ነው... ቀውላላ የሚሉት ዓይነት፡፡የፈለገው ዓይነት ልብስ ይልበስ በፍፁም አያምርበትም፤ ወፎችን ለማስበርገግ
በማሽላ መሀል የተሰቀለ አሮጌ ልብስ ይመስላል፡፡ሲንቀሳቀስም ንፋስ የሚያወዛውዘው እንጂ በራሱ የሚራመድ አይመስልም፡፡
የተመጣጠነ
የሰውነት ቅርፅ የለውም፤ እጅና እግሮቹ ከሌላው አካሉ በእጅጉ ይራዝማሉ፡፡ስለሆነም ቁጭ ሲል የተቀመጠበት ወንበር በቁሙ የዋጠው
ይመስል ድንክ ሆኖ ይታያል፡፡አንገቱ በጣም አጭር ስለሆነች ትንሽየ ራስ ቅሉ በትክሻው ላይ የተቀመጠች ጨርቅ ኳስ ነው የምትመስለው፡፡አጥንታም
ፊቱ ተረጋግጦ የተጣለ ባዶ የውሃ ፕላስቲክ(ሃይላንድ) ትመስላለች...
ጉንጩ ቢስሙት እንደ ቀጋ ይዋጋል፤ እንደ ሰማ ይለበልባል፡፡አፉን የሚከድንበት ከንፈር ያለው አይመስልም፤ ሁሌም አፉን እንደከፈተ
ነው፡፡ቀይ ድዱ ሙሉ በሙሉ ይታያል፤የዝንጀሮ ቂጥ ይመስላል፡፡ጥርሱ ፈንጭት ይበዛበታል፤ተበታትነው የሚታዩ የምድረ በዳ ቆጥቋጦዎች
ይመስለሉ፡፡ቀያይ ዓይኖቹ ምንጊዜም እንዳፈጠጡና ወደ ወጭ እንደተጎለጎሉ ናቸው፤በድንጋጤ እንዳፈጠጠ የቀረ ሬሳ ይመስላል፡፡
ገስጥ
ሲናገር በጣም ይፈጥናል፤ሁሌም ይንተባተባል፤ እንትን፣ምናምን የመሳሰሉ
ቃላት የንግግሩ 50 በመቶ ይሸፍናሉ፡፡መናገር እንጂ ማዳመጥ አያውቅም፤ ችሎታ ባይነረውም የመናገር ሱስ ስላለበት ሁሌም እንደቀባዠረ
ነው፡፡አንድ አዝብጤ የሚባል በጣም አጭር ጓደኛ አለው፤ ድቡልቡል ነገር ነው ... ልክ እንደኳስ፡፡ስለሆነም ሲራመድ የሚንከባለል
ነው የሚመስለው፡፡ገስጥና አዝብጤ አብረው የእግር ጉዞ ሲያደርጉ አንድ አባትና የሰባት ዓመት ልጁ ይመስላሉ፡፡ገስጥ አዝብጤን ይወደዋል፡፡ምክንያቱም
አውርቶ እስኪደክመው ድረስ በጥሞና ስለየሚያዳምጠው ነው፡፡አዝብጤ ገሌለ ማንም ከቁብ ቆጥሮት ጀሮ አይሰጠውም፡፡
ገስጥ
በስሩ ያሉ ሰራተኞች ሰብስቦ የበጥ የቆጡን ሲዘበርቅባቸው ነው የዋለው፡፡ምንም ትንፋሽ ሳይወስድና ያለማቋረጥ ለሁለት ሰዓታት ተናገሯል፡፡በተሰብሳቢዎቹ
ፊት ድብርት ይነበባል፡፡ የእንጀራ ነገር ሆኖባቸው ታገሱት እንጂ የርሱ ትርጉም የለሽ ዲስኩር ከመስማት ይልቅ በሁለቱም ጀሮ ግንዳቸው
በጥፊ ቢመቱ ይመርጣሉ፡፡ስለሚያወራው ነገር ማንም አያውቅም፤ እራሱም ጭምር የገባው አይመስልም፡፡ቢሆንም ግን ዝም ብሎ ይለፍፋል፤
የመናገር ድኳኩን ለማባረርና የመሰብሰብ ግዴታውን ለመወጣት፡፡ከዚሁ ስብሰባ እንደወጣ ከየበላይ አለቃው ሌላ ስብሰባ ይጠብቀዋል፡፡
የስብሰባው ውጤት በስብሰባው ላይ ሪፖርት መደረግ አለበት፡፡
‹‹እ...››
በማለት ነበር ስብሰባውን የጀመረው፤‹‹እ... እየሰራችሁ ያለችሁት ስራ የመደነቅ ነው፡፡ ‹ቲም ስፕሪታችሁ› ምናምን ነገር፣ከጊዜ
ወደ ጊዜ ምናምን ነገር፣ እየተሻሻለ ነው ምናምን ነገር፡፡ስለሆነም ቢዚሁ ብትቀጥሉበት ምናምን ነገር፣ለወደፊት እንትን ማድረግ ትችላላችሁ
ምናምን ነገር፡፡ነገር ግን አንድ እንትን አለ፡፡ ሁላችሁም ማለት ይቻላል ሰዓት አታከብሩም ምናምን ነገር፡፡ጥዋት በሰዓቱ ቢሮ አትገኙም፤
ማታ ደሞ የስራ ሰዓት ሳያልቅ ትወጣላችሁ ምናምን ነገር፡፡በዚህ ምክንያት አለቃየ እንትን እያለኝ ነው፡፡እንትና የት ሄደ? አትቆጣጠራቸውም
ወይ? ምናምን ነገር፡፡››
‹‹እንዴ!
በትራንስፖርት ችግር እየተሰቃየን እኮ ነው ያለነው፡፡ መኪና ያለንም ቢሆን የትራፊክ መጨናነቅ ስላለ እንዳሰብነው ወደፈለግነው ቦታ
በጊዜ መድረስ ተስኖናል፡፡›› አለች አንዷ ተሰብሳቢ፡፡‹‹ኸረ የታክሲና የመንገጆች መዘጋጋት ብቻ አይደለም ችግሩ፤የእግረኛ መንገድም
እኮ ተዘጋግቷል፡፡በእግር ለመጓዝም የቀጠና ስምሪት ሳይወጣ ይቀራል ትላላችሁ፡፡እንዴ! ጉድ እኮ ነው፤በእግር ለመንቀሳቀስም በሰልፍና
በፈረቃ ሳይሆ አይቀም፡፡››ስትል አከለች ሌላኛዋ፡፡
ሁለቱም
ሴቶች ከገስጥ ጋር በምንም መልኩ አይወዳደሩም...እነርሱ ንግግር የማሳመር ችሎታ አላቸው፤በተለይ የመጀመርያዋ ተናጋሪ፡፡ሁሌም ለመናገር
አፏን አቀባብላ የምትጠብቅ ብትመስልም የማዳመጥ ችሎታዋም ቢሆን ብዙ የሚታማ አይደለም፡፡እሩሱም ቢሆን የሚያደንቃት ይመስለኛል፤
የዓመት ዕረፍቱን ሲወስድ ውክልና የሚሰጠው ለእርሷ፡፡
‹‹አዎ፤
ይገባኛል፡፡መንገዶቹ ሁሉ ተዘጋግቷል ምናምን ነገር፤ነገር ግን እንድምንም ብላችሁ ቻሉት፡፡ግዴታ ሆኖብን ነው እንጂ እኛም እኮ ደልቶን
አይደለም በሰዓታችን ቢሮ የምንገኘው፡፡››አለ ሰብሳቢው ሲመለሰ፡፡ሰብሳቢው ገስጥ፣ የሚናገረው ሲጠፋበት በእናንዳንዱ ቃል ‹‹ምናምን ነገር››ና ‹‹እንትን›› እያከታተለ ነገር ያንዛዛል፡፡ሲናገር
ወደ ተሰብሳቢዎች አይመለከትም፤ በላፕቶፑ ላይ የፃፈው እያነበበና በወረቀት ላይ የሆነ ነገር አየሞነጫጨረ አቀርቅሮ ይንተፋተፋል...
ባትሪ እዳለቀበት ሬድዮ፡፡ለዛም ነው የተሰብሳቢዎቹ ስሜት መረዳት የማይችለው፡፡በቃ፤ እሱ ተደፍቶ ሲለፍፍ፣ ሌሎች በተመስጦ የሚያዳምጡት
ይመስለዋል፡፡
ተሰብሳቢዎቹ ግን በራሳቸው እሽክርክሪት ዓለምን ሲያዳርሷት ነበር፡፡አንዱ ነጭ ኖራ ወደ ተቀባው ግድግዳው ትኩር ብሎ ይመለከታል...ለእርሱ ብቻ የሚነበብ
ፅሑፍ ያለ ይመስል፡፡ሌላው በመስኮቱ መስታወት በኩል ወደ ውጭ ይመለከታል፡፡ሌሎቹ ደሞ ከአገጫቸው ጀምሮ እስከ ጉንጫቸው ያለውን
ፊታቸውን በመዳፋቸው ላይ አስደግፈው በእግሮቻቸው መካከል ያለውን ምንጣፍ ላይ በአግራሞት የሚመለከቱ ይመስላሉ፡፡
ገስጥ
የሚናገረው ሲጠፋበት ረዣዥም እጆቹን በደመ ነፍስ ማወናጨፍ ይጀምራል፡፡በዚህ መሃል ሳይታሰብ እጆቹ ፊትለፊቱ ካለው ጠረጴዛ ጋር
በሃይል ይጋጩና በሐሳብ ማዕበል ወድያ ወዲህ ይናጥ የነበረው ተሰብሳቢ እንዳአንዶቹ ከቀን ቅዠታቸው ይናጠባሉ ሌሎቹ ደሞ በድንጋጤ
በድን ይሆናል፡፡ገስጥ ግን አሁንም እንደ ተደፋ ‹‹ዋና ዋናዎቹ ፍረ ነገሮች እነዚህ ናቸው ምናምን ነገር፡፡ አስተያይት፣ጥያቄ ምናምን
ነገር ካላችሁ አሁን ማቅረብ ትችላላችሁ ምናምን ነገር፡፡የዛሬው እንትናችን ይህን ይመስል ነበር፤ ‹ቴንኪው›፡፡››በማለት ዲስኩሩን
ይቋጫል፡፡
ገስጥ
መናገር ስያምረው አንድ የበታች ሰራተኛ ጠርቶ መስማት እጅ እጅ እስኪለው ድረስ እኝ ይለዋል፡፡ለበዙ ዓመታት አብራው የኖረችው ጓደኛው
የእንጋባ ጥያቄ አቅርቦላት እምቢ እንዳለችና ከዛም እንደ ተጣሉ፤ የአዲስ አበባ ሴቶች ታማኝ እንዳልሆኑና ማንኛውም ወንድ መጠንቀቅ
እንዳለበት ምክር ይሰጣል፤ የህይወት ልምዱን ያካፍላል(እራሱ እንደሚያስበው)፡፡
ነገር
ግን ምሬቱን እየገለፀ እንጂ ምክር እየሰጠ መሆኑን የሚረዳለት የለም፡፡ እሱ ግን እንደ አዋቂና የሌሎች ችግር ለመፍታት የሚያስችል
ብቃት እንዳለው አድርጎ ነው ራሱን የሚቆጥረው፡፡ስለሆነም ሰብሳቢው ገስጥ፣ ክራይ ባይሰበስብም በእርግጠኝነት የእንቶ ፍንቶ ወሬ
ሰብሳቢ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment