ማክሰኞዎች ከሞሪ ጋር(Tuesdays with
Morrie)ሚች ኤልቦን(Mitch Albon)በሚባል አሜሪካዊ የስፖርት ጋዜጠኛ የተፃፈ መፅሐፍ ነው።የመፅሐፉ አጠቃላይ ይዘት በህይወት
ላይ ያጠነጥናል።በዚች ዓለም እንዴት መኖር እንዳለብን ያመክራል።
የመፅሐፉ ዋና ገፀባህርያት ሞሪ ሽዋሬዝና ሚች ኤልቦን
ናቸው፤በጣም የሚዋደዱ ተማሪና አስተማሪ።ሞሪ የሚች የድሮ የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ሲሆን ኤ.ኤል.ኤስ በሚባል መድሐኒት የሌለው በሽታ
እየተሰቃየ የሚገኝ ሽማግሌ ነው።ኤ.ኤል.ኤስ(Amyotrophic Lateral Sclerosis_ ALS)አእምሮ ምንም ሳይነካ ሌላው
አካል እንደ ጨው አሟሟቶና እንደ ዱቄት ፈጭቶ በሌሎች ላይ ጥገኛ በማድረግ ቀስበቀስ የሚገድል በሽታ ነው።
ሚች ግን ወጣት ነው።ህፃን እያለ ሙዚቃኛ የመሆን ህልም
ነበረው። ነገር ግን፣ ብር ለማግኘት ሲል የስፖር ጋዜጠኛ ሆኗል።ብር ሲያሳድድ ራሱንና ቤተሰቡን ረስቷል። ከ16 ዓመታት በኋላ ግን
ሞሪ በቀዛፊው በሽታ ተይዞ «ናይት ላይን» ከተባለ የቴሌቭዥ ጣብያ ጋር ቃለ መጠይቅ ሲያደርግ ሚች በድንገት ይመለከተውና ቤቱን
ድረስ በመሄድ ይጠይቀዋል።ከዛም የድሮ ወዳጅነታቸው ይታደሳል። ሚችና ሞሪ ሁሉ ጊዜ በሳምንት አንዴ መገናኘቱ ቀጥለውበታል፤ በዕለተ
ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ።
ማክሰኞ በመጣ ቁጥር ይገናኛሉ። ሞሪ የህይወት ተሞክሮው
ለሚች ያስተምረዋል። ሚች ይጠይቃል፣ ሞሪ ይመልሳል፤ ለአስራ አራት ተከታታይ ማክሰኞዎች።የሚች ድርሻ ያልገባው ነገር መጠየቅና ማስታወሻ
መያዝ ነበር።ይህ መፅሐፍ የዚሁ ውጤት ነው።በአስራ አራተኛው ማክሰኞ ሚችና ሞሪ ለዘላለሙ ተሰነባብቷል፤ ሞሪ ላይነሳ አንቀላፍቷ።
ሞሪና ሚች በአራተኛው ማክሰኞ የተወያዩበት
ርእስ በአማርኛ
ተርጉሜ አቅርቤዋለሁ።በዕለቱ የተወያዩት ስለሞት ነበር።ሞሪ እንዳለው፣«ሁሉም ሰው እንደሚሞት ያውቃል፣ነገር ግን ማንም አያምንበትም። ቢያምንበት
ንሮ በጥቃቅን ነገሮች ተወጥሮ ህይወቱን ሳያጣጥማት ባልሞተ ነበር።እንደምንሞት ካመንን ስለምንም ነገር አንጨነቅም፤ ዓለምን ሙሉ
በሙሉ እናጣጥማታለን» አዎ፣ አራተኛዋ ማክሰኞ የሌሎቹም መሰረት ናት።ነገ እንደምንሞት ከተነገረን ዛሬ ስለብር እንጨነቅም፤ከማንም
አንጣላም፤ከቤተሰባችን መለየት አንፈልግም።ተራራው፣ሜዳው፣ቅጠሉ፣ ድንጋዩ፣አፈሩ፣ውሃው… ሁሉም ነገር ብርቅ ይሆንብናል።የተፈጥሮ እንከንየለሽነት
እንረዳለን።ከዛም እያንዳንዷ ደቂቃ በአድናቆ፣በግርምት፣በስስት ሰለምንመለከታት ህይወታችን እናጣጥማታለን።
የአራተኛዋ መክሰኞትርጉም ከገባን በአስራ አራት ማክሰኞዎች
ስለተነጋጉሩባቸው ነገሮች ማወቅ አያዳገተንም።ለዛም ነበር አራተኛዋን ማክሰኞ ተርጉመን የቀረብናት።እችን መጣጥፍ ስንተረጉም በባህልና በትርጉም ውስን የሆኑ ቃላት ያጋጠሙን
ሲሆን አጠቃላይ ትርጉምና ከባህላችን ጋር ተቀናጅተው ትርጉም በሚሰጡ ቃላት ትረጉመናቸዋል፡፡ ሙሉ መፅሐፉ በእጄ ይገኛል(በእንግልዝኛ)፡፡
እርሶ ለማንበብ ፍላጎቱ ካልዎት ያለምን ውጣ ውረድ፣ ያለምንም ክፍያ በእጅዎ ይገባል፡፡
እስኪ ያአራተኛው ማክሰኞ በአማርኛ ያንብቡት፡፡
በአራተኛው ማክሰኞ ስለሞት እናወራለን
«በዚሁሐሳብእንጀምር»አለሞሪ፣«ሁሉምሰውእንደሚሞትያውቃል፣ነገርግንማንምአያምነበትም»በዛሬው ማክሰኞ የሞሪ ስሜት ነጋዴብጤ ያስመስልበታል።የቀኑ የመወያያ አርእስት ስለሞት
ነበር፤በማስታወሻየ ከዘረዘርኩዋቸው ነገሮች የመጀመርያው።ሞሪ እኔ ከመድረሴ በፊት፣ለማስታውስ እንዲረዳው በቁርጥራጭ ነጭወረቀቶች
ላይ ማስታወሻ ሞነጫጭሯል።የአሁኑ የተወላገደ የእጅፅሑፉ ከራሱ በስተቀር ማንም አንብቦ ሊረዳው አይችለም።የሰራተኞች ቀን እየደረሰ
ነው፤ትንሽቀናት ብቻ የቀረዋል፣በቢሮው መስኮት በኩል በረድፍ የተደረደሩ አሮንጓዴ ዛፎች ይታዩኛል፣በአስፓሎቱ ላይ የሚጫወቱ ህፃናት
ጭሆትም ይሰማኛል።ትምህርት ከመጀመሩ በፊት ያለችው የመጨረሻዋ የነፃነታቸው ሳምነት ናት።
በድትሮይት፣ የጋዜጣ ሰራተኞች የስራ ማቆም አድመኞች ትልቅ የሰላማዊ ሰልፍ በዓል ለማድረግ በዝግጅት ላይ ናቸው፣ማሕበራት ፀረ አስተዳደሩ ያላቸው ጠንካራ አንድነት ለማሳየት።በአውሮፕላን የበረራ ጉዞ ላይ እያሎሁ፣ ባለቤቷንና ሁለት ሴት ልጆቿን ተኝተው እያሉ ተኩሳ ስለገደለችው ሴትዮ አንበብኩኝ፤ «ከመጥፎ ሰዎች» ለመከላከል በሚል አጉል ሰበብ።ስለሆነም፣ በካሊፎርንያ የኦ.ጄ. ሲምፕሰን ፍርድ ቤት ዳኞች በጣም ታዋቂ ሰዎች እየሆኑ ነው።
በሞሪ ቢሮ ውስጥ ህይወት ቀጥላለች፣ መተክያ የሌላቸው ቀናት አንድ በአንድ ይኖግዳሉ።አሁን ለቤቱ ከተጨመረው አዲስ እቃ በትንሽ ጫማዎችን ራቅ ብለን አብረን ቁጭ ብለናልቸ፤ የአየር መተንፈሻ መሳርያ።የመሳርያው ከፍታ ጉልበት አከባቢ ይደርሳል፤ትንሽ መጠን ያለውና በቀላሉ ሊንቀሳቀስ የሚችል ነው።አንድ አንድ ለሊቶች፣ ሞሪ በቂ አየር መሳብ ሲያቅተው ረጅሙ ላስቲክ ቱቦ በአፍንጫው ያጣብቀዋል፤ በሁለቱ የአፍንጫው ቀዳዳዎች እንደ መዥገር ጥፍንግ በማድረግ።ሞሪ ከማንኛውም ዓይነት መሳርያ ጋር የመጣመሩ ነገር ስለጠላሁት፣ ሳናግረው ወደ እርሱ ላለማየት ሞከርኩ።
«ሁሉም ሰው እንደሚሞት ያውቃል»አለ በድጋሚ ፣«ነገር ግን ማንም አያምንበትም።በናምን ንሮ፣ነገሮችን ከአሁኑ በተለየ መልኩ እናከናውናቸው ነበር» በማለት አከለ።
እና ስለ ሞት ያለን አመለካከት ራስን የመሸወድ ያህል ነው?አለኩት።
«አዎን። ግን ደሞ ከዚህ የተሻለ አመለካከት አለ፤አንደ ምትሞት ማወቅና በማንኛውም ጊዜ ሞትን ተዘጋጅቶ መጠበቅ።የህኛው የተሻለ ነው።በዚህ መልኩ ነው በህይወት እያለን ከአኗኗራችን ጋር በይበልጥ ተቆራኝተን መኖር የምንችለው»
ለመሞት ከቶ እንዴት መዘጋጀት ይቻላል?
«የቡድሂዝምእምነትተከታዮችእንደሚያደርጉትአድርግ።በየቀኑ፣ ‘የምሞትበትቀንዛሬይሆን?ዝግጁነኝ? መስራትያለበኝነገርእየሰራሁኝነው? መሆንየምፈልገውንዓይነትሰውበመሆንላይነኝ?’ እያለችየምትጠይቅአንዲትትንሽየወፍበትክሻህላይአኑር»
ወፍዋአሁንያለችያህልፊቱንወደትክሻውአዞረና፣«ዛሬይሆንየምሞተው?» አለ።
ሞሪ ከሁሉም ሃይማኖቶች በነፃነት የህይወት ተሞክሮ ወስዷል።ከአይሁድ ቤተስብ ነበር የተወለደው፣ ነገር ግን በተወሰነ መልኩ በህፃንነቱ በደረሱበት ችግሮች ምክንያት ወጣት ሲሆን ወደ ተጠራጣሪነት እምነት ቀይሮ ነበር።የተወሰኑ የቡድሂዝምና የክርስትና እምነት አስተምሆሮዎችን በጣም ይደሰትባቸዋል። በባህል ደሞ አሁንም ድረስ የጁዳይዝም እምነት ቤተኛ ነው። ይህ ከተለያዩ እምነቶች የቀሰመው የህይወት ተሞክሮ ለዓመታት ካስተማራቸው ተማሪዎቹ ጋር የበለጠ ግልፅ እንዲሆን ረድቶታል።በህይወት ዘመኑ የመጨረሻ ወራት የሚናገራቸው ነገሮችም የሃይማኖት ልዩነቶች ሳይደርቱት የላቀ ስብእና እንዲኖረው አስችሎታል።ሞት እንዲህ የማድረግ ችሎታ አለውና።
«እውነቱንእኮ፣ሚች» አለሞሪ፣«አንዴእንደምትሞትካወቅክ፣እንዴትእንደምትኖርትማራለህ»
ራሴንነቀነቅኩኝ።
ሞሪ «አሁንምእደግመዋለሁ» አለናቀጠለ፣«አንዴእንደምትሞትካወቅክ፣እንዴትእንደምትኖርትማራለህ»
ፊቱበፈገግታበራ፣እኔምምንእያደረገመሆኑንገባኝ።በጥያቄዬሳያሸማቅቀኝየሚናገረውንበትክክልመገንዘቤንማረጋገጡነበር። ይህ ብቃቱ ነበር የጥሩ አስተማሪነቱ ምስጢር።
ከመታመምህ በፊት ስለሞት ብዙ አስበህ ታውቅ ነበር? ብየ ጠየቅኩት።
«በፍፁም።» አለ ሞሪ ፈገግ ብሎ፣«እንደማንኛውም ሰው ነበርኩ።አንዴ ሞቅ ሲለኝ ጊዜ ለጓደኛየ፣ ‘በህይወት ዘመንህ ከምታገኛቻው የእንድሜ ባለፀጎች እጅግ በጣም ጤነኛውእሆናሎሁ’በማለት ቃል ገብቼለት ነበር»
የስንት ዓመት እያለህ?
«በስልሳዎቹ የዕድሜ ክልል እያሎሁ»
እና ተስፋህ ብሩህ ነበር ማለት ነው?
«ለምንስአይሆንም? ቅድም እንዳልኩት፣አንድም ሰው እንደሚሞት አያምንም»
ነገር ግን እያንዳነዱ ሰው የሆነ ሰው በሞት ከዚህ ዓለም መለየቱን ያውቃል፣ አልኩት።ለምንድ ነው ታድያ ስለሞመት ማሰቡ ከባድ የሚሆኖው?
ሞሪ «ምክንያቱም፣» በማለት ማብራራቱን ቀጠለና፣« ሁላችንም ማለት ይቻላል በእንቅልፍ ልባችን እዚህም እዚያም የምንቅበዘበዝ ይመስላል።ዓለምን ሙሉ በሙሉ አናጣጥማትም፣ምክንያቱም ጊዜዊ የሁኑ ነገሮችን ስናሳድድ ህሊናችን ስተናል፣በከፊል አንቀላፍተናል… በሰመመን ነው የምንኖረው»
እናም ከሞት ጋር ፊት ለፊት መግጠም ይህን ሁሉ ይቀይራል?
«ኦው፣ በጣም።ያኔ ተራ የሆኑ ነገሮችን አሽቀንጥረን በመወርወር ለህይወት ወሳኝ ቢሚባሉ ነገሮች ላይ ብቻ ትኩረት እንሰጣለን።እንደምትሞት በትክክል ስትገነዘብ፣ነገሮችን በተለየ አቅጣጫ ትመለከታለህ»
በመቀጠልም«እንዴት እንደምትሞት በትክክል እወቅ፣ከዛም እንዴት መኖር እንደሚገባህ ትማራለህ» በማለት ተነፈሰ።
አሁን፣ እጆቹን ሲያንቀሳቅስ እንደሚንቀጠቀጥ አስተውያለሁ።የዓይን መነፅሩ በአንገቱ ላይ ተንጠልጥሏል፣ወደ ዓይኖቹ ከፍ ሲያደርገው ደሞ በጨለማ ውስጥ ላለው ሌላ የማይታይ ሰው ላይ ለማድረግ እንደሚሞክር ወደ ቅንጡ አከባቢ ይንሸራተታል።በጆሮዎቹ ላይ በማድረግ ስለረዳሁት«አመሰግናለሁ» በማለት አንሾካሾከ።እንደዛ ሳደርግ፣ እጄ ራሱን ነካውናፊቱ በፈገግታ ደመቀ።ስስ የሆነው የሰውነት ንክኪ ቅፅበታዊ ደስታ የሚፈጥር ነበር።
«ሚች።አንድ ነገር ልነግርህ እችላለሁ?» በደምብ እንጂ፣ አልኩት።
«አትወደውም ይሆናል» እኮ ለምን?
«በእርግጥ፣ እውነታው፣በትክሻህ ላይ ያለቸውን ድምፅ በትክክል ካዳመጥና በማንኛውም ጊዜ ልትሞት እንደምትችል አምነህ ከተቀበልክ ከዛ በኋላ ለህይወት ከፍተኛ ጉጉት ላይኖርህ ይችላል»
ራሴን በማስገደድ በትንሹ ፈገግ ለማለት ሞከርኩ።
«አሁን አብዛኛው ጊዜህን የመታጠፋባቸው ነገሮች - የምትሰራው ስራ ሁሉ - እርባና ቢስ መስሎ ሊታይህ ይችላል። ምናልባትም፣ለመንፈሳዊ ነገሮችን ትልቅ ግምት ትሰጥ ይሆናል» ሲለኝ፣ በአግራሞት መንፈሳዊ ነገሮች? ቢሚል ጥያቄ አምባረቅኩበት።
«‘መንፈሳዊ’ ምትልዋን ቃል አትወዳትም አይደል?አጉል መለማመጥ ይመስልሃል?»
መልካም፣አልኩ።
በዓይኑ ሊጠቅሰኝ ሞክሮ ሳይሳካለት ሲቀር፣ስሜቴን መቆጣጠር አቅቶኝ በሳቅ ፈነዳሁ።
«ሚች፣»አለ፣ አብሮኝ እየሳቀ፣«እኔም ጭምር ‘መንፈሳዊ ስልጣኔ’ ምን ማለት መሆኑን በትክክል አላውቀውም።ነገር ግን በመጠኑ የሚጎድለን ነገር ያለ መሆኑን አውቃለሁ።ቁሳዊ ከሆኑ ነገሮች ጋር ከልክ በላይ ተቆራኝተናል፤ ነገር ግን ሊያረኩን አይችሉም።የፍቅር ግንኙነትና በዙርያችን ያለው ዓለም በእጃችን እንደሆኑ አድርገን እናስባለን»
የፀሐይ ብርሃን በማስገባት ላይ ባለው መስኮት በኩል ወደ ውጭ አሻግሮ ተመለከተና ራሱን ነቀነቀ።« ያኛው ይታይሃል? በማንኛውም ጊዜ፣ አንተ ወደዛ ወጥተህ መሄድ ትችላለህ።ከአንዱ ስፍራ ወደ ሌላኛው ስፍራ
እንደ
ጥጃ ላይና ታች መቦረቅ ትችላለህ፤በደስታ ጨርቅህን ጥለህ እስክታብድ ድረስ።እኔ ግን እንደዛ ማድረግ አልችልም።ወደ ውጭ መውጣት አልችልም።መሮጥ አልችልም።እንዳልታመም ሳልፈራ ወደዛው ወጥቼ መሄድ አልችልም። ነገር ግን እውነቱን ልንገርህ? መስኮቱን ካንተ በላይ እኔ አደንቀዋለሁ»
ታደንቀዋለህ? ጠየቅኩት።
«አዎ።በየቀኑ በመስኮቱ በኩል ወደ ውጭ እመለከታሎሁ።በዛፎቹላይ የሚመጣው ለውጥ በማስተዋል፣ ንፋሱ በምን ያህል ጥንካሬ እየነፈሰ መሆኑን አውቅበታለሁ።ጊዜ በመስኮቱ መስታወት በኩል ስታልፍ በእውን እማያት መስሎ ይሰማኛል።እያለቀልኝ መሆኑን ስላወቅኩኝ፣ተፈጥሮን ለመጀመርያ ጊዜ ያየኋት ያህል በርሷ ተመስጫለሁ»
ካለ በኋላ ዝም ሲል፣ ሁለታችንም ለአፍታ ያህል በመስኮቱ በኩል ወደ ውጭ ተመለከትን።እሱ ያየውን ለማየት ሞከርኩኝ።ጊዜና ወቅት ለማየት ሞከርኩኝ፤ህይወቴ በኤሊ እርምጃ እየተጎተተ ሲያልፍ።ሞሪ ራሱን በመጠኑ አቀረቀረና ወደ ትክሻው አከባቢ ዘንበል አደረገው።«ዛሬ ነው፣ትንሽዋ ወፍ?»ሲል ጠየቀ።«ዛሬ ነው?»
«ናይት ላይን» ለሚባለው የቴለቪዥን ጣብያ ምስጋና ይግባውና በአንዱ ክፍለ ጊዜ በቴሌቪዥን ጣብያው ከታየ ወዲህ ደብዳቤዎች ከመላው ዓለም እየጎረፉለት ነው።ዝግጁ ሲሆን ጊዜ ቁጭ ይልና ደብዳቤዎቹን
ለጓዶኞቹና
ለደብዳቤ አፃፃፍ ክፍለ ጊዜ ለተሰባሰቡ የቤተሰቡ አባላት በቃሉ ያነበንብላቸዋል።
አንድ እሁድ ሮብና ጆን የሚባሉ ልጆቹ ቤት እያሉ፣ ሁሉም በመኖርያ ቤቱ ተሰባሰቡ።ሞሪ በተሽከርካሪ ወንበር ላይ ተቀምጠዋል፣በጣም ቀጫጭን እግሮቹ በብርድልብስ ተሸፍነዋል።ብርድ ሲሰማው፣ ከረዳቶቹ አንድዋ ከሃር የተሰራ ጃኬት በትክሻው ላይ ደረበችለት።
«የመጀመርያው ፊደል ምንድ ነው?» አለ ሞሪ።
አንድ የስራ ባለ ደረባው ከአንድ ስሟ ናንሲ የተባለች ኤ.ኤል.ኤስ የሚባል በሽታ እናትዋን የገደለባት ሴትዮ የተላከ ማስታወሻ አነበበለት።እናትዋን በማጣትዋ የተሰማት መሪር ሐዘንና ሞሪ በበሽታው ምን ያህል እየተሰቃየ መሆኑን እንደምታውቅ ለመግለፅ ነበር የፃፈችው።
«በጣም ጥሩ» አለ ሞሪ ማስታወሻው ተነቦ እንዳለቀ።ዓይኖቹን ጨፈነ።ቀጥሎም «እንዲህ በማለት እንጀምር»አለ፣« ‘ውድ ናንሲ ሆይ፣ስለናትሽ በፃፍሽልኝ ታሪክ ስሜቴ በጣም ተነክቷል።በምን ዓይነት ሁኔታእንዳለፍሽም ይገባኛል።በሁለቱም ክፍሎች፣ ሐዘንና ስቃይ ይፈራረቃሉ፤ የእናትሽ መታመምና ብሎም መሞት።በሐዘን የተገረፉትን አፅናናልን ማለቱ ለኔ መልካም ነበር፣ እናም ላንችም መልካም እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ’»
«ምናልባት የመጨረሻው መስመር መቀየር ሳያስፈልግህ አይቀርም» አለ ሮብ።
ሞሪ ለአፍታ አሰብ አደረገና፣« ትክክል ነህ። እንዲህ ባስተካክለውስ ‘በጥልቅ ሃዘንሽ ላይ የማዳን ስልጣኑን ማግኘት እንደምትችይ ተስፋ አደርጋሎሁ።’አይሻልም?»
ሮብ በመስማማት ራሱን ነቀነቀ።
« ‘አመሰግናሎሁ፣ሞሪ’ የሚለውን ፊርማ ጨምርበት» አለ ሞሪ።
ጄን ከተባለች ሴትዮ የተላከ ሌላ ደብዳቤም ተነቧል። በ«ናይት ላይን» የቴሌቪዥን ጣብያ ቀርቦ ባደረገው የቃለ መጠይቅ ክፍለ ጊዜ የመንፈስ ማነቃቃት ስላሳደረባት ለማመስገን ነበር የፃፈችለት፤ነብዪ የሚል ስያሜም ሰጥታዋለች።
«በጣም ላቅ ያለ ሙገሳ ነው» አለ አንድ የስራ ባለደረባው።«ነብዪ»
ሞሪ ፊቱን ኮስተር አድርጓል።በእውነቱ፣ በሴትዮዋ አገላለፅ አልተደሰተም።«ለክፍተኛ ሙገሳዋ አናመስግናት።አነጋገሬ ትርጉም ስለሰጣት ደስተኛ መሆኔንም ንገሩልኝ። ‘አመሰግናሎሁ፣ሞሪ’ የሚለው ፊርማየም እንዳትረሱ»
አንድ እናቱን በሞት ያጣ የእንግላንድ ኗሪም እናቱን በመንፈሳዊው ዓለም እንዲያነጋግርለት የሚማፀን ደብዳቤ ልኮለታል።ቦስተን ድረስ መጥተው ሊያገኙት የሚፈልጉ ጥንዶችም ፅፈውለታል።
ከድሮ ተመራቂ ተማሪዎች አንዷ የተላከና ከልክ በላይ የተንዛዛ ደብዳቤም ደርሶታል። ከዩኒቨርሲቲ ተመርቃ ከወጣች በኋላ ስለነበረው ኑሮዋን ያትታል።ስለግድያ ያወራል - አንድ ራስን የማጥፋትና ሶስት ሞተው የተወለዱ ሕፃናት።ኤ.ኤል.ኤስ የሚባል በሽታ እናቷን ስለገደለባት እርሷም በሽታው ተላልፎብኝ ይሆናል በሚል ስጋት እየተሰቃየች መሆኗን ይተርካል።ደብዳቤው አንድ ገፅ፣ሁለት ገፅ፣ሶስት ገፅ፣ አራት ገፅ እያለ ይቀጥላል።
ሞሪ ረጅሙና አስገራሚው ትረካ ተነቦ እስኪያልቅ ድረስ ቁጭ ብሎ ይከታተል ነበር።ንባቡ እንዳለቀ፣«እሺ፣ምን ብለን እንፃፍ?» አለ ሞሪ፣ ለስለስ ባለ ድምፅ።ብዱኑ ፀጥ ብሎ ነበር።በመጨረሻም ሮብ፣« ‘ስለረዥሙ ደብዳቤሽ እናመሰግናለን’ ብንላትስ?» በማለቱ ሁሉም ሳቁበት።ሞሪም ልጁን በስስት አየት አደረገውና ፊቱ ፈካ።
ከወንበሩ አጠገብ ያለው ጋዜጣ የአንድ የበቦስተን ቤዝቦል ተጫዋች ኳስዋን ከወረወረ በኋላ ፈገግ ብሎ የተነሳው ፎቶ ያሳያል።እኔ እንደማሰበው፣ ሞሪ በስቃዩ መሀል እያለ የአንድ እውቅ አትሌት ስም አሰታወሰ።
ሎ ግሬግን ታስታወሰዋለህ? ስል ጠየኩት።
«በስተድዮሙ ሲሰናበት ትዝ ይለኛል»
ስለዚህ፣ ዝነኛዋ መስመር ታስታውሳታለህ?
«የትኛዋ?»
ተውእንጂ። ሎ ግሬግ።«የያንኪዎቹ ኩራት»? በድምፅ ማጉያዎቹ የሚያስተጋባው ንግግር?
«እስኪ ንግግሩን አስታውሰኝ» አለ ሞሪ።
በተከፈተው መስኮት የሚገባው የቆሻሻ ማጓጓዣ መኪና ድፅ ይሰማኛል።አየሩ ወበቃማ ቢሆንም፣ ሞሪ እጅጌ ያለው ልብስ ለብሷል፣ በእግሮቹም ላይ
ብርድ
ልብስ ጣል አድርጓል። ቆዳው ገርጥቷል፣በሽታውም ተቆጣጥሮታል።
ድምፄን ከፍበማድረግ በስታድዮሙ ግድግዳዎች የሚያስተገባው የግሬግ ንግግር በማስመሰል፡«ዛ…ሬ በዓለም ላይ እጅግ በጣም እድለኛ ሰው እንደሆንኩ ይሰማኛል… »
ሞሪ ዓይኖቹን በመክደን ራሱን ግራና ቀኝ በቀስታ ንቅንቆ«እኽም፣ አዎ። እኔ ግን እንደዛ ማለቴ አልነበረም» አለ።
10Q OUR PIONEER ASFAW,IT IS AMAZING ! how can i write comment.... Mehari
ReplyDelete