በእናት ፍቅር፣በእናት እቅፍ፣በእናት ጉርሻ የማይናፍቅ ማን ነው?
ፎቶው
የወሰንሰገድ ገብረኪዳን ነው፡፡
እናት
ፍቅር ነች፣ሃገር ነች፣ ሰውን ሰው ያደረገች ፈጣሪ ነች፡፡የሰው ልጅ እንስሳዊ ባህሪ ተላብሶ ነው የሚወለደው፡፡ለማሰብ፣ ለመንቀሳቀስ፣
ከሰዎች ጋር ለሞኖር ወዘተርፈ የሚያስችለው አካል ብቻ ይዞ ይወለዳል፡፡እንዴት እንደሚጠቀምባቸው ግን አያውቅም፡፡በኮምፒተር ቋንቋ
የማያስብና ህሊና የሌለው አካል ብቻ ያለው ( a fully fledged hardware without software) ማለት ነው፡፡ኮምፒተሮች
ያለሶፍትዌር እንደማይሰሩ ሁሉ ሰዎችም ሶፍትዌር ያስፈልጋቸዋል...ልቦና፣ ህሊናና አእምሮ፡፡
የኮምፒተር
ሶፍትዌር ራሱ የሚፈበረከው በሰው ልጅ ነው፡፡ሃረድዌሩም በሰው ነው የሚሰራው፤ በኮምፒተር ባለሙያ፡፡ሃርድዌሩ በትክክል እንዲሰራ
ከተፈለገ ሶፍትዌር መጫን አለበት... ይግድ ነው፡፡የሰው ልጅም እንድያ ነው፡፡ለዛም ነው የህፃናት አእምሮ በነጭ ወረቀት የሚመሰለው፡፡ምንም
ዓይነት ስርዝ ድልዝ የሌለው ንፁህና ነጭ ወረቀት፡፡ተንኮል፣ምቀኝነት፣ፍቅር፣ጥላቻ ወዘተርፈ የሚባሉ ነገሮች ኋላ ነው የሚጫኑት፡፡የዚህ
ስራ ምርጥ ባለሙያ ደሞ እናት ነች፡፡
በአብዛኛው
ጊዜ እንደ ሰው እንደናስብ የምታስችለን እናት ነች፡፡ለዘጠኝ ወራት በማህፀኗ ተሸክማ፣አምጣ ወልዳ፣ ለሶስት ዓመታት አጥብታና አዝላ
የምታሳድግ እናት ነች፡፡የእናት ሚና ለአቅመ ሰብእ(አቅመ አዳምና አቅመሄዋን) እስክንደረስ ድረስ ይቀጥላል፡፡ሰውን ሰው ያደረገች
ፈጣሪ፡፡እናት የፍቅር ተምሳሌት(role model) ነች፡፡እናት የእናት፣የአባት፣የወንድምና የአባትም እናት ነች፡፡
ታድያ
ያለወንድም፣ያለእህት፣ያለአባት፣ያለጓደኛ ዓለም ምንድ ነች?ያለእነዚህ ነገሮች የሰው ልጅ ባይተዋር ነው፡፡ሃገር አልባ፣ዘመድ የለሽ፣
ፍቅር የሌለው ተቅበዝባዥ አውሬ፡፡ስለዚህ ሰውን ሰው ያደረገች እናት ነች፡፡የለወንድም፣ያለእህትና ያለጓደኛ ምን ዋጋ አለን! እናት
ዓለም ዓለምን ሰጠችን፡፡
የእናት
ፍቅር አድገን ተመንድገንም ቢሆን ይቀጥላል፡፡ለዛም ነው የእናት ፍቅር ሰጥታ የምትቀበል ሄዋንን ፍለጋ የምንባዝነው፤የምንኳትነው፡፡ለዛምነው
ያላገባ ወንደላጤ ዘልዛላ ነው የሚባለው፡፡አዎ! ለዛም ነው ያላገባ ወንድ ሃላፊነት ለመሸከም የሚያስችል ትክሻ የለውም የሚባለው፡፡ያላገባ
ወንድ ማለት እናት የሌለው ህፃን ልጅ ማለት ነው፡፡ይህ ነገር ለወንደ ላጤዎች ላይዋጥላቸው ይችላል፡፡ለባለትዳሮች ግን እጅግ በጣም
ግልፅ ነው፡፡ላጤዎችም ቢሆን ሲያገቡ ይገባቸዋል፡፡
ወንድምና
እህት የሌለው ሰው አለኝታና መከታ የለውም፡፡ በተለይም በድሮ ዘመን፡፡በድሮ ዘመን ወንድም የሌለው ሰው ማንም ደፍቶት ቢሄድ ጠያቂ
አልነበረውም፡፡እናት የወንድም ምንጭ ነች፡፡እናት መከታ ነች፡፡
እህት
የሌለው ሰውም እድያው ባዶ ነገር ነው፡፡እህት ታማክራለች፣እህት ታፅናናለች፣እህት እንደናት ትንከባከባለች፡፡በዚህ አጋጣሚ ማንም
ፊደል የቆጠረ ትግረዋይ የማይረሳት በትግርኛ ቋንቋ የተፃፈች ግጥም ጀባ ልበላችሁ፡፡ ማን እንደፃፋት አይታወቅም ግን ማንም ትግረዋይ
ያውቃታል፡፡ይሀውና!
ኣታ
ትግነዶ አንእስተይቲ ሓፍቲ
ሓጋይ
መስኖ ክረምቲ ብዓልቲ
ተጠመኻ
ተብልዕ ተስቲ
ተሓዘንኻ
ተማኽር ተዛቲ፡፡
የአማርኛ
ተመሳሳይ ትርጉሙ የሚከተለው ይመስላል፡፡
አንተየ
እህትስ የት ትገኛለች
በበጋ
መስኖ በክረምት ዋሻ ሆና ታስጠልላለች
ብትራብ
ታበላለች ታስጠጣለች
ብታዝንም
ታምክራለች ታፅናናለች፡፡
ማለት
ነው፤ ከሞላ ጎደል፡፡እናት የእህት ምንጭ ነች፡፡ሰውን ሰው ያደረገች ፈጣሪ፡፡ ፎቶውን አያችሁልኝ? እንደው በሞቴ ማን ነው እንዲህ
ተመስጦ ልጁን(የልጅ ልጁን) የሚያቅፍ? ሁሉን ነገር ትቶ በፍፁም ተመስጦና በፍቅር የሚያቅፍ ማን ነው? አዎ! እናት ነች፡፡እናት
የፍቅር ተምሳሌት!
እናት
የእውቅት ምንጭ ነች፡፡አዳምና ሄዋን ወደ ምድረ ኩነኔ ከመባረራቸው በፊት በኤደን ይኖሩ ነበር ይላል መፅሐፍ ቅዱስ፡፡ኤደን ምንጮችዋ
ማርና ወተት የሚያፈልቁ፣ፀሐይ የማትጥልቅባትኗሪዎችዋ ሁሉም በእጃቸው ሁሉም በደጃቸው ሆኖው የሚኖሩባት የቅድመ ዓለም የአዳምና ሄዋን
መኖርያ ነበረች፡፡በማሀሏ ከምትገኘው ክፉና ደጉን የምታሳውቅ እፀበለስ በስተቀር ሁሉም እንዲበለው ያሻቸውን እንዲያደርጉ ተፈቅዶላቸዋል...
አዳምና ሄዋን፡፡
ይሁን
እንጂ ልክ እንደ ህፃን ነበሩ ... ክፉና ደጉን ምታሳውቅ እፀበለስን አልቀመሰዋትም ነበርና፡፡እናታችን ሄዋን ግን አላስቻላትም
ቀጥፋ በላቻት፡፡የሰው ልጅም ከሊሂቃኖቹ ሶስተ ስላሴዎች እኩል አደረገችው፡፡እንደውም አዳምና ሄዋን ባይባረሩና እፀበለሷን ድጋሚ
ቢበሏት ንሮ ፊጣሪንም ሳይበልጡት አይቀሩም ነበር፡፡ግን አልሆነም፡፡አዳምና
ሄዋን ከኤደን ተባረሩ፡፡እውቀት ስንቀው፤ ከፈጣሪያቸው እኩል ሆነው፡፡
ታላቁ
ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ ሀዲስ በተባለው መፅሐፉ ‹‹ሄዋን
እፀበለስ ባትበላ ንሮ የሰው ልጅ ዝንጀሮ ሆኖ ይቀር ነበር›› ብሏል፡፡እውነት ነው፡፡እናት የሰው ልጅን ከዝንጀሮነት አዳናቸው፡፡መፅሐፉ እንደሚለው ሐጥያት አልሰራችም፡፡እንኳንም
እንክት አደረገችው!ሴቶች ከወንዶች በበለጠ አስተዋዮች፣ታጋሾችና ርኅሩሆች ናቸው የሚባለው እፀበለስን ቀደማ የበላቸው ሄዋን ስለሆነች
ይመስለኛል፡፡እናት የእውቀት ምንጭ ነች፡፡
ወዳጄ
ጋዜጠኛና ደራሲ ወሰንሰገድ ገብረኪዳን እናትን ስታከብረ የስው ልጅ በሙሉ እንዳከበርክ፣እንዳፈቀርክ ነው የሚሰማኝ፡፡ፈጣሪ ከፍ ከፍ
ያድርግለኝ፡፡
ለእናታችንም
ረዥም ዕድሜ ከሙሉ ጤና ጋር ይስጥልን፡፡

No comments:
Post a Comment