Thursday, July 11, 2013

የድሃ እርግማን ይት ይደርሳል?




አለቃየ በጣም አስቾኳይ ስራ ስለሰጠ በአንድ ሰዓት ውስጥ ሰርቼ ለማጠናቀቅ እየተጣደፍኩኝ ነው፡፡‹ኤክስኤል ሽት› ከፍቼ ወርሐዊ ርፖርት በማዘጋጀት ላይ ነኝ፤አለቃየ ከአለቆቹና ከሌሎች በለድርሻ አካላት ጋር ስብሰባ ይዞት ይቀርባል፡፡ለዛም ነው ‹‹ሪፖርቱ በአስቾኳይ እፈልገዋለሁ›› በማለት ጥብቅ ትእዛዝ የሰጠኝ፡፡በጣም ከመቸኮሌ የተነሳ አላሰብኩበትም፤ ይሆናል ብየ አለገመትኩምና ምንም አልተዘጋጀሁም፡፡ሙሉ ትኩረቴ ሪፖረቱን ተሎ ሰርቶ በመጨረስ ለአለቃየ በማስረከብ ላይ አድርጌያለሁ፡፡እናም የምሰራበት ኮምፒተር ‹ዩፒኤስ› የሌለው መሆኑን ረስቸዋለሁ፡፡የተሰጠ ስራ ለማጠናቀቅ ትንሽ ነው የቀረኝ፡፡በድንገት መብራት ድርግም አለ!!!የከፈትኩት ፋይል ‹ሴቭ› አላደረግኩትም ነበር፤ አብሮ ድርግም አለ!!!


አሁን ምን ማድረግ እችላለሁ? መብራት ሃይሎች ሆይ፣ አይናቹ ይጥፋ!!!



ትናንት አለቃየ በጣም ተበሳጭቶብኛል፤ ስብእናየን ከመሬት በታች የሚቀብር ስድብ ሰድቦኛል ‹‹ደንቆሮ!የደደቦች ደደብ! ድሮውንስ ድሃ መቼ ክብር ያውቅና…›› ያልሰደበኝ የስድብ ዓይነት አልነበረም፡፡የስራ መልቀቅያ በማስገባት መስራ ቤቱን ጥየ ለመጥፋት አስቤ ነበር፡፡ግን ወዴት? ጓደኛ፣ወገን ዘመድ የለኝም፡፡ ተከራይቼ ነው የምኖረው፡፡ስራ አጥ ሆንኩ ማለት ጎደና አደር ሆኛለሁ ማለት ነው፡፡ኦሆሆሆው! ነብስ አርፈሽ ተቀመጪ፡፡አለቃየ እውነቱን ነው፤ ‹‹ድሃ አማራጭ የለውም!››ነበር ያለኝ አይደል? በአሁኑ ጊዜ አንድ ሰራተኛ ለመቁጠር ማስታወቅያ ለሚያወጡ መስራ ቤቶች ስንት የስራ አመልካቾች ያመለክታሉ? ብያንስ አንድ ሽህ!፡፡
ስለዚህ ነገ በጥዋት ገብቼ ስራየን ሰርቼ በማጠናቀቅ አለቃየን ማስደሰት አለብኝ፡፡<<The boss is always right>>(አለቃ ሁሌም ትክክል ነው) ብሏል ፈረንጅ፡፡ገና ጥዋት ወፎች ሲንጫጩ ነበር የነቃሁት፤ የሞባይሌ ሰዓት ልክ 12፡00 ይላል፡፡ገላይን ለመታጠብ ወደ ‹ሻወር› ቤት ገባሁ፡፡አንዴ ገላየን ለቅለቅ ብየ ሳሙና አድርጌ አረፋ በአረፋ ስሆን ውሃው ጠፋ፤የቧንቧ መክፈቻው ባዞር ባዞር ደርቆ ቀረ!!!

ኤህ!!! የውሃና ፈሳሽ አገልግሎት ድርጅት የሎጥ ሚስትን የጨው አለት የደረገ አምላክ እንደ ድንጋይ የድርቃችሁ!!!

እችን ተራግሜ ገላየን በፎጣ አደርቅኩና ሳሙና ሳሙና የሚሸተው ሰውነቴን በድዮድራንት ሸውጄ ከቤት ወጣሁና ታክሲ መጠበቅ ጀመርኩ፡፡የሚመጡት ታክሶች ሁሉ ሙሉ ናቸው፡፡‹‹ትርፍ አንጭንም!›› እያሉ ጥለውኝ ይሄዳሉ፡፡የአንድ ታክሲ መንገድ በእግሬ ህጄ ታክሲ ለመሳፈር ከተሰለፈው ህዝብ ጋር ከኋላ ተሰለፍኩኝ፡፡ስልፉ በጣም ረዥም ነው፡፡ታስፋ ያስቆርጣል፡፡ለነገሩ በታዳጊ አገር እየኖሩ ምን ተስፋለና? ሰልፍ ይዤ ስጠብቅ…ስጠብቅ…ስጠብቅ ስዓቱ ረፈደ፡፡ተራ ደርሶን፣ ታክሲ ይዘን ጉዞ ጀምረናል፤ ነገር ግን ትራፊኩ ተጨናንቋል፤ ባሰብኩት ጊዜ ካሰብኩት ቦታ መድረስ አልቻልኩም፡፡

ኤህ!!! የመንገድና ትራንስፖርት ድርጅት ካሰባቹበት አትድረሱ!!!

 

ቤተሰቦቼ ክፍለ ሃገር ናቸው፡፡ሰሙኑን ስልክ አልደወልኩምና በጣም ናፍቀውኛል፡፡ዛሬ ግን እሁድ ነው ወደ ወንድሜ ብደውል ሁሉም በአንድ ቤት ተሰባስበው አገኛቸዋለሁ፡፡ስልኬን አንስቼ ወደ ወንድሜ ደወልኩ፡፡ ‹‹መስሮቹ ሁሉ ለጊዜው ተይዘዋል፤ እባክዎ ትንሽ ቆይተው ይሞክሩ›› የሚል የሴት ድምፅ ሰማሁ፡፡ይህ ድምፅ ብያንስ ሽህ ጊዜ ሰምቸው ይሆናል፤በዚህ ዓለም መስማት የማልፈልገው ድምፅ ቢሆንም ሌላ አማራጭ ስሌለሌኝ በድጋሚ ደወልኩ፡፡አሁንም ‹‹መስሮቹ ሁሉ ለጊዜው ተይዘዋል፤ እባክዎ ትንሽ ቆይተው ይሞክሩ›› የሚል ድምፅ ሰማሁ፡፡ብዙ ጊዜ ደግሜ ደጋግሜ ደወልኩና ከወንድሜ ጋር በስልክ ተገናኘሁ፡፡ከርሱ ጋር ትንሽ ካወራን በኋላ ከእናቴ ጋር እንዲያገናኘኝ ነገርኩትና እሺ ብሎኝ ሰላምታ ልውውጥ ጀመርን፡፡
‹‹ሄሎ! አደዋኒ ዓለመይ! ሃመይ እነአኺ?››
‹‹ይስፋውዋይ! ዳሕና ኢኻ? ሃመይ ንአኻ?››

‹‹ጥጥ…ጥጥ… ጥጥ›› ስልኩ ተቋረጠ!!! ኤህ!!! ኢትዮ ቴሌኮም አንጀትህ ይቆረጥ!!!

እነዚህ ችግሮች የተለመዱ ናቸው፡፡ገዢዎቻችን እንደ ችግር የሚቆጥሩዋቸው አይመስለኝም፤ ጭራሽ ረስትዋቸዋል፡፡ድሮ ‹‹ውሸት ሲደጋገም እንደ እውነት ይቆጠራል››  ሲባል እሰማ ነበር፡፡አሁን ደሞ ‹‹ችግሮች ሲደጋገሙ እንደ ድሎት የቆጠራሉ›› ሳይባል የቀረ አይመስለኝም፡፡የመገናኛ ብዙሃን አንድ ሰሙን ተንጫጭተው ጭጭ አሉ፡፡ገዢዎቻችንም ‹‹ችግሮቹን ከስረ መሰረታቸው ለመፍታት ጠንክረን እየሰራን ነው›› አሉና ጭጭ!!!
ችግሮች በተደጋገሙ ቁጥር የእርግማን ዶፍ እያወረድኩ እገኛለሁ፡፡ግን የድሃ እርግማን የት ይደርሳል?የትም አይደርስም፤ ወደራሱ ይመለሳል፡፡ ሰማይ ቀርቶ አራት ደብር ያለው ፎቅ ላይም መድረስ አልቻለም፡፡ለዛም ነው ከኔና ከመሰሎቼ እሮሮ ማሃል የማይጠፋው፡፡

No comments:

Post a Comment